ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ አርታኢ፤ ባሕሩ ዘውዴ 2015 ማውጫ መቅድም መግቢያ የፍሬዴሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ ሚስስ ሱዛን ሽቶልራይተር በሁለተኛው ዙር ዐውደ ጥናት ላይ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር የታሪክ እስረኛነት ወይንስ የታሪክን በጎም ሆነ ክፉ ኩነት ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ሕይወት ማሻሻያ ማዋል ? የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር I. ጽንሰ ሐሳባዊና ታሪካዊ ዐውድ ዶ / ር ተካልኝ ወልደ ማርያም የሕዝብና የቁሳቁስ እንቅስቃሴዎች፣ አንቀሳቃሾችና አካላዮች በኢትዮጵያ፤ ጽንሰ ሐሳባዊና ታሪካዊ ንባቤ II. ውህድና ቅይጥ ማንነት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ በቅይጥ ማንነት ላይ የተመሠረተ አገረ መንግሥት አስፈላጊነት (The Case for a Composite Nation-State) ዶ / ር ቴዎድሮስ ዘውዱ ውህድ ማንነትና ብሔራዊ መግባባት III. የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ታሪካዊ ትስስርና መስተጋብር ዶ / ር ደረጀ ሂነው የሕዝቦች መስተጋብር ተለዋዋጭነት ከዐባይ ወንዝ በስተደቡብ (1880-2008) ዶ / ር ዴሬሳ ዴቡ የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ታሪክ በጊቤ፣ ጎጀብና ዲዴሳ ሦስት ማዕዘን ( ጂማ ዞን ) ዶ / ር ከፍያለው ተሰማ ሰሙ የባሌ ኦሮሞና ሶማሌ ብሔረሰቦች የመስተጋበርያ ሀገር በቀል ተቋማት ሚና ዶ / ር ረታ ዱጉማ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ዶ / ር ዘላለም ተፈራ በዘመናት መካከል የሚለዋወጥ የሕዝቦች ግንኙነትና ማኅበራዊ መስተጋብር በምሥራቅ ወለጋ IV. ሃይማኖታዊ መቻቻልና ባህላዊ ተዛምዶ ዶ / ር አህመድ ሐሰን የሃይማኖቶች አብሮነትና ብዝኃ ሃይማኖተኝነት በኢትዮጵያ ከ 19 ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ ዶ / ር አሰፋ ባልቻ ወሎ፡ የአብሮነት፣ የሠላም እና የእምነቶች ተግባቦት ቀንዲል V. ከተሜነትና የንግድ ልውውጥ ዶ / ር ሺመልስ ቦንሳ ከተሞች፣ ከተሜነትና፣ የብዝሃ አገር ግንባታ በኢትዮጵያ ዶ / ር አልማው ክፍሌ አዲስ አበባ፤ የመቻቻልና የመከባበር ኅብረ ብሔራዊ የአብሮነት ከተማ ዶ / ር ግርማ ነጋሽ የአፍሪካ ገበያዎች ለተግባቦትና ለፖለቲካ መስተጋብር፤ ከአንዳንድ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ገበያዎች የተገኙ ዕይታዎች VI. ማንነትና የፖለቲካ ሥልጣን ዶ / ር አውግቸው አማረ በኢትዮጵያ የሕዝቦች መስተጋብርና ትስስር ልምድ የኦሮሞ ሕዝብን የሚመለከቱ አንዳንድ ጉዳዮች ዶ / ር ደቻሳ አበበ የኦሮሞ አማራ ገበር ማህበረሰብ መፈጠር፤ ራስ ጎበና እንደ ተወላጅና እንደ አራማጅ ዶ / ር ገረመው እስከዚያው ደጃዝማች ቱሉ እና ደጃዝማች ወሬኛ ዋሾ፤ አጭር ታሪካዊ ዳሰሳ ( ከ 1690 ዎቹ እስከ 1760 ዎቹ ) ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፤ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት የጽሑፍ አቅራቢዎች አጫጭር መረጃ መቅድም ኢትዮጵያ ረጅምና ደማቅ ታሪክ ያላት አገር ናት። በዚህም ስንኮራ ቆይተናል። ባንፃሩ ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክ የፖለቲካ ግብግብ አውድማ እየሆነ መምጣቱ ለሁላችንም ገሃድ ነው። በ 1983 የተደረገው የሥርዓት ለውጥ ከዚያ በፊት የተገለሉና የተጨቆኑ ብሔረሰቦችን መብት በማስከበር ረገድ ዐቢይና አዎንታዊ ሊባል የሚችል ሚና ተጫውቷል። በኦፊሲዬል ደረጃም መፈክሩ ‹‹ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ›› ወይም ‹‹ አንድነት በብዝኃነት ›› ሆኗል። ነገር ግን አሁን በግልፅ እንደመናየው፤ ገኖ እየወጣ ያለው አንድነቱ ሳይሆን ብዝኃነቱ ነው። ስለሆነም አገራችን በዘውጋዊና ክልላዊ ግጭቶች ስትናጥ ቆይታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየባሰ መጥቶ የአገሪቱ ኅልውና አጠያያቂ የሆነበት ደረጃ ደርሷል። ጊዜ በወለደው አርቲፊሻል የነባርና መጤ ተቃርኖ ለአያሌ ዓመታት አብረው የቆዩ ኢትዮጵያውያን በጠላትነት መፈረጅ ጀምረዋል። ሰዎች ለረጅም ዘመናት ከኖሩበትና አንዳንዴም ከተወለዱበት ቀዬ ከመፈናቀልም አልፈው በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በአሁኑ ጊዜ ከአካባቢ ወጥቶ መንቀሳቀስ ብርቱ ፈተና እየሆነ መጥቷል። በአፄያዊው ዘመን በዩኒቨርሲቲ አገልግሎት መርሀ ግብር የተሠማራንባቸው እንደ ደምቢ ዶሎ ያሉ ከተሞች፣ በዘመነ ደርግ ለሠፋሪዎች ጎጆ የቀለስንባቸው እንደ መተከል ያሉ አውራጃዎች የማርስን ያህል ርቀውን ይገኛሉ። ታሪካዊ ሐቁ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው። የታሪክ ሰነዶችና ማስረጃዎቸ የሚያመለክቱን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ክልሎች፣ ምንም እንኳን የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ ባሕርያትና ተቋማት ቢኖሯቸውም፣ በብዙ መንገድ እርስ በርስ የተሳሰሩና የተጋመዱ እንደነበሩ ነው። በአገሪቷ ውስጥ 80 የሚያህሉ ብሔረሰቦች ቢኖሩም፣ የቋንቋ ሊቃውንት በአራት ዋና ዋና የቋንቋ ቤተሰቦች ይመድቧቸዋል። የገዥው መደብም በአንድ ብሔረሰብ የታጠረ ሳይሆን ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጣ ነበር። በተለይም ከአማራ፣ ኦሮሞና ትግራይ የፈለቁ ግለሰቦች በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች የገዥ መደብ አካል ሆነዋል። የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት መሠረት የሆነችው የአክሱም ስም ራሱ ‹‹ አክ ›› የሚለው የአገው ( ማለትም ኩሻዊ ) ቃልና ስዩም የሚለው ሴማዊ ቃል ጥምረት ነው። ትርጉሙም ‹‹ የውሃ ሹም ›› ማለት ሲሆን ውሃው የሚያመለክተው እስካሁንም በከተማው ጉልህ ሥፍራ ያለውን ኩሬ ነው። የቅርቡ ታሪካችንን ስናጤን ደግሞ ኦሮሞዎች ከአማሮች፣ ጉራጌዎችና ሌሎችም ብሔረሰቦች ጋር ተጋምደውና ተሳስረው ኖረዋል። በዚህ መድበል በተካተተው አንድ መጣጥፍ በዝርዝር እንደምንመለከተው፤ ወሎ የትስስርና መስተጋብር ተምሳሌት ሆና ቆይታለች። ሸዋም እንደዚሁ አማሮች፣ ኦሮሞዎችና ጉራጌዎች ተጋብተውና ተዛምደው የኖሩባት ጠቅላይ ግዛት / ክፍለ ሀገር ነበረች። እንደዚሁም በፖለቲካው፣ በወታደራዊ ገድሉ፣ በምሁራን አምባና በስፖርቱም ሆነ በኪነቱ ያሉን ብሔራዊ ጀግኖችና አርአያ ሰቦች ከሁሉም ብሔረሰቦች የተውጣጡ ናቸው። ከአፄ ዮሐንስ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ከራስ አሉላ እስከ ራስ ጎበና፣ ከገብረ ሕይወት ባይከዳኝ እስከ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ ከጥላሁን ገሠሠ እስከ ባሕታ ገብረ ሕይወት፣ ከመንግሥቱ ወርቁ እስከ ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ ከአበበ ቢቂላ እስከ ምሩፅ ይፍጠር፣ ከደራርቱ ቱሉ እስከ ለተሰንበት ግደይ። በምግብ ረገድም ብሔረሰባዊ መሠረት ያላቸው ምግቦች በሂደት አገራዊ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ረገድ የኦሮሞን ጨጨብሳ፣ የአማራን ዶሮ ወጥ፣ የትግራይን / የኤርትራን አ ( ሐ ) ምባሻ እና የጉራጌን ክትፎ መጥቀስ ይቻላል። በኅብረ ብሔራዊ ትስስር የተሞላው ታሪካዊ ሐቅ በተለይም አገራዊ ምክክር መድረክ ተቋቁሞ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንቅስቃሴ በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት ጎልቶ ሊወጣ ይገባዋል። የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ከተቋቋመበት ዓላማዎች አንዱ ታሪክና የታሪክ ትምህርት ለብሔራዊ መግባባት ስለሚውልበት ሁኔታ ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። በታሪካችን ብዙ ግፎች መፈፀማቸውን የታሪክ ባለሙያዎች አይክዱም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የአገራችን ኅልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ በመሆኑ ( ገደል አፋፍ በመድረሳችን ማለትም ይቻላል ) ከልዩነቶቻችን ይልቅ ለአንድነታችን፣ ካለፈው ይልቅ ለአሁኑ፣ አጽንኦት መስጠት ይጠበቅብናል። ስለሆነም ነው ማኅበሩ ምሥረታውን ለማብሰር ግንቦት 16 ና 17 ፣ 2014 ባካሄደው የሁለት ቀን ዐውደ ጥናት ‹‹ ታሪክ ለብሔራዊ መግባባት ያለው ሚና ›› የሚለውን ርዕስ የመረጠው። በዚህም ርዕስ በተለይ በታሪክ አፃፃፍና አረዳድ ሥነ ዘዴ ላይ የሚያጠነጥኑ ስምንት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ነበር። በዚህ ዐውደ ጥናት ከታሪክ ተመራማሪዎች በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት ባልሥልጣናት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሙያ ማኅበራትና የወጣቶች ተወካዮች ተገኝተው ነበር። ክንዋኔው ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ለማግኘት በቅቷል። በዚህ ዐውደ ጥናት አማካይነት ለሕዝብ ልናስተላልፍ የፈለግነው መልእክት፤ ታሪክ አሁን እየመሰለ እንደመጣው የችግሩ ሳይሆን የመፍትኄው አካል እንዳልሆነ ነው። ከዚያም ይህንኑ ፈለግ በመከተል ማኅበሩ ‹‹ ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ ›› በሚል ርዕስ በሦስት ዙር የተካሄደ ዐውደ ጥናት አዘጋጀ። በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ነጋ የተከፈተው የመጀመሪያው ዙር በነሐሴ 10 ቀን፣ 2014 ዓ . ም . የተደረገ ሲሆን፤ ሁለተኛው በመስከረም 24 ፣ 2015 ዓ . ም . ፣ ሦስተኛው ደግሞ በኅዳር 6 ፣ 2015 ዓ . ም ተደርገዋል። በነዚህ ተከታታይ ዐውደ ጥናቶች በጥቅሉ 18 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ጽሑፍ አቅራቢዎቹ የተውጣጡት ዐሥራ ስድስቱ ከዘጠኝ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ( አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ሀሮማያ፣ ጂማ፣ ኮተቤ፣ መዳ ወላቦ፣ ወሎ እና ወለጋ ) ሲሆኑ፤ ሁለቱ ደግሞ ከሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ናቸው። የቀረቡት ጽሑፎች የተለያየ ርዕስ ያላቸው ቢሆኑም በአምስት ዋና ዋና ርዕሶች ይመደባሉ። እነሱም፡ የብሔረሰቦች ትስስርና መስተጋብር፣ የውህድ ማንነት ችግርና የቅይጥ ማንነት አስፈላጊነት፣ ሃይማኖታዊ መቻቻልና ባህላዊ ተዛምዶ፣ ከተሜነትና የንግድ ልውውጥ እና ማንነትና የፖለቲካ ሥልጣን ናቸው። በተለየ በመጀመሪያው ዘርፍ የቀረቡት ጽሑፎች በታሪክ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ምን ያህል የተሳሰሩና የተጋመዱ እንደነበሩ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ታሪካዊ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ፤ አሁን የሰፈነው ግጭትና መገዳደል እንዴት ሊመጣ ቻለ የሚለው ጥያቄ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያብሰለስለውና መልስ ሊያገኝለት የሚገባ ነው። የብዙ የዐውደ ጥናቶቹ ታዳሚዎች ጥያቄ እነዚህ ጠቃሚ ጽሑፎችና ውይይቶች በአንድ ቀን መርሀ ግብር ተከናውናው ያበቃሉ ወይ የሚል ነበር። ይህንን በመገንዘብም ጽሑፍ አቅራቢዎቹ ስብሰባው እንዳለቀ ጥናታቸውን ከሦስት ገጽ ባልበለጠ ጨምቀው እንዲያቀርቡልን ጠየቅን። ይህ በተለይ ለታሪክ ጸሐፊዎች ቀላል ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ሁሉም ጥየቄዎቻችንን በፀጋ ተቀብለው በተቆረጠው ቀነ ገደብ ጭብጦቻቸውን አስገብተውልናል። ከዚያም አስፈላጊው አርትኦት ተደርጎላቸው ታትመው እነሆ ለዕይታ ቀርበዋል። ለሕዝብ ትምህርትን፣ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ደግሞ ጠቃሚ ግብኣትን ይሰጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በመጨረሻም እነዚህን ተከታታይ ዐውደ ጥናቶች ለማካሄድና ብሎም የጥናታዊ ጽሑፎቹን ጭብጦች በዚህ መልክ ለሕዝብና ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንዲሆኑ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገልንን የፍሬዴሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን፣ በተለይም ዳይሬክተሯን ሚስ ሱዛን ሽቶልራይተር እና የፕሮግራም ዳይሬክተሩን ዶ / ር በለጠ በላቸውን በማኅበሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። ባሕሩ ዘውዴ ( ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ) የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የ ፍ ሬዴ ሪክ ኤ በር ት ፋው ንዴ ሽን የ ኢት ዮጵ ያ ተ ጠሪ ሚ ስስ ሱ ዛን ሽቶ ል ራ ይ ተ ር በሁ ለተ ኛው ዙር ዐው ደ ጥ ና ት ያ ደረጉ ት የ መ ክፈ ቻ ንግግር Distinguished Guests, Dear Participants, Ladies and Gentlemen, Good Morning. On behalf of FES, please allow me to welcome you all to this second round of national consultative workshops on the broader theme of building national consensus in Ethiopia. It gives us great pleasure to partner with the Association of Ethiopian Historians(AEH) in addressing one of the key elements in the ongoing effort to transform the political landscape in this country. In these workshop series, we aspire to address comprehensively basic tenets of“Interdependence and Interactions in Ethiopian History ”. The plan is to initiate a high-level and deeply informed exchange of views among stakeholders on the matter of consensus building and the all-inclusive political settlement in the country. It has now become clear that for a country like Ethiopia, with complex and diverse socio-political traditions, the past matters significantly. Any attempt to move forward, therefore, necessitates the proper understanding and contextualization of the factors that have been shaping proceedings in the past. We are partnering with the Association of Ethiopian Historians not for the sake of talking about past irregularities or achievements in the country. Rather, the overall exercise hinges on the now and the immediate future. Informing the ongoing political transformation process through the mechanism of dialogue and other parallel initiatives is among the main priorities of these activities. In this regard, I am sure that the FES-AEH partnership is going to bring about fruitful results in the next months and years. We are planning to avail the synopses of the presentations at the three successive workshop to the wider audience by the end of this year. This way we make sure that the message of interdependence and interactions within the framework of national consensus building would be properly communicated to relevant bodies. Before concluding my brief remarks, please allow me to thank the organizers, paper presenters, the moderators and participants who invested time and energy in making this workshop a reality. I wish you fruitful deliberations. Thank you! የታሪክ እስረኛነት ወይንስ የታሪክን በጎም ሆነ ክፉ ኩነት ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ሕይወት ማሻሻያ ማዋል ? የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር ክቡራትና ክቡራን ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ክቡራትና ክቡራን የዚህ አውደ ጥናት አዘጋጆች የተከበራችሁ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር አባላት እንደምን አደራችሁ፤ ይህን ስብሰባ እንድከፍት ስጠየቅ፤ ግብዣውን ልቀበል አልቀበል በሚል ለረጅም ጊዜ ነበር ያሰብኩበት። ታሪክ እንደ አንድ የዕውቀት ዘርፍ፤ ዘርፉ ባስቀመጣቸው የትንተና መለኪያዎች ላይ በመመስረት ዕውቀት እየዳበረ የሚሄድበት፤ በጥንቃቄ በሚሰሩ ጥናቶች እውነት ከሐሰት፣ ወሳኝ የታሪክ ኩነቶች ከአዘቦት የሕይወት እንቅስቃሴዎች የሚለዩበትና ሁለቱም የታሪኩ ሙሉ አካል የሚሆኑበት፤ ማኅበረሰቡ ያለፈባቸውን መጥፎም ሆኑ ጥሩ ወሳኝ የታሪክ ሂደቶች፣ ያለፈውን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ከነኝህ ታሪኮች በመማር የዛሬውንና የወደፊቱን ትውልድ ሕይወት ለማሻሻል የሚረዳን ዕውቀት የምንቀስምበት መስክ ነው። ይህ መሆኑ ቀርቶ፤ ማኅበረሰብን በስሜት በመጋለብ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የፈለገ ማንም ጥራዝ ነጠቅ፣ የራሱን እምነት ለመሸጥ ሲል የሚመቸውን ብቻ እየነቀሰ እያወጣና እያጋነነ የፖለቲካ ጢብ ጢብ የሚጫወትበት የጨርቅ ኳስ በሆነበት ሀገርና ዘመን፤ የታሪክ ነገር፣ ያውም የመንግሥት ኃላፊነት ላለበት ሰው፣ በሩቁ የሚሸሸው ጉዳይ ቢሆን የሚገርም አይደለም። ግብዣውንም ለመቀበል ስወስን እንደ አንድ የመንግሥት ባለሟል ወይንም የፖለቲካ ድርጅት መሪ እዚህ ላላችሁ ምሁራን “ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ” ሳይሆን ለዕውቀት ክብር እንዳለው አንድ የቀድሞ አካዳሚክ፣ የበለጠ ደግሞ የሀገሩ ሁኔታ እንደሚያገባውና እንደሚያሳስበው አንድ ዜጋ፣ በጉዳዩ ላይ ተጠንቅቄ እንዳስብ ግብዣው ስለገፋፋኝ፤ የታሪክ ባለሙያም ባልሆን በዚህ የዕውቀት መድረክ ላይ እኔ ያለኝን ሐሳብ ለማንሸራሸር፤ ይበልጥ ደግሞ ታሪክን ሥራዬ ብለው ከያዙ ባለሙያዎች ለመማርም ዕድል ስለሚሰጠኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ስብሰባውን ሙሉ ለሙሉ ለመሳተፍ ዕድል ካላገኘሁ በስብሰባው የሚቀርቡትን ጽሑፎች አግኝቼ ለማንበብ ዕድል አገኛለሁ የሚል ተስፋ አለኝ። ዘመናችን በታሪክ ዙሪያ ለሚደረግ ምክንያታዊ ውይይት የሚመች ስላልሆነ ጉዳዩን “ በምን አዳረቀኝ ” ግዴለሽነት ለጥራዝ ነጠቆች የምንተወው፣ ወይንም ነገሩን ስለሸሸነው ትን ብሎ የሚጠፋ ችግር አይደለም። የታሪኩን ሐቅ ምንነት ወይንም የዚያን ሐቅ ትንተና በሚመለከት ከሚኖር ስምምነትም ይልቅ ( ለምሳሌ አጼ ምኒልክ ጥሩ መሪ ነበሩ ወይስ አልነበሩም ?) ስለ ታሪክ ራሱ ምንነትና ከአሁን ሕይወታችን ጋር ሊኖረው ስለሚገባው መስተጋብር፤ ይበልጥም ደግሞ የዛሬ የፖለቲካ ሕይወታችንን በተመለከተ ታሪክ ሊኖረው ስለሚገባው ሚና ግልጽ የሆነ አረዳድ ከሌለ፤ የዛሬውን ሕይወታችንና በተለይም የወደፊቱን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ለማበላሸት ያለው አቅም ቀላል አይደለም። ታሪካችን የዛሬውንና የወደፊቱን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ይወስነዋል ? እስከምን ድረስ ? ወይንስ የተፈጠርንበት አካባቢ ነው ዕጣ ፈንታችንን የሚወስነው ? ወይንስ ተቋሞች ናቸው ?... ወዘተ (history as destiny? Geography as destiny? Institutions as destiny?) የሚለው አካዳሚያዊ ክርክር ገና መቋጫ ያላገኘ፣ ምናልባትም ሙሉ ለሙሉ መቋጫ የማይኖረው ክርክርም ሊሆን ይችላል። ለጊዜው ታሪክ ላይ ብናተኩር፤ ያለፈው ታሪክ ነው ዕጣ ፈንታችንን ላንዴና ለሁሌ የሚወስነው ( የታሪክ እስረኞች ነን ?) ወይንስ የዛሬውንና የወደፊቱን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ከታሪክ ተገቢውን ትምህርት ወስዶ የመወሰን ኃላፊነት የአሁኑና የወደፊቱ ትውልድ ነው የሚሆነው ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ታሪክ በተወሰነ ደረጃ የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት ከሆነ፤ ሁሉም ትውልድ በዘመኑ ካለው ዕውቀት ተነስቶ የታሪኩን አቅጣጫ የመወሰን ዕድል ካለው፤ ዋናው ጥያቄ የሚሆነው በዚህ ሂደት ያለፈው ትውልድ ታሪክ ምን ያህል ሚዛን ቢደፋ ነው ትክክለኛው ልኬት የሚሆነው ? የሚለው ጥያቄ ይሆናል ማለት ነው። ይህ እንግዲህ ጉዳዩን የበለጠ ላለማወሳሰብ የሰው ልጅ ካለፈባቸው የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ በየትኛው የታሪክ ዘመን የተፈጸመው ታሪክ ነው አሁን ላለው ሁኔታ ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው የሚለውን ጉዳይ ለዚህ ውይይት ያክል ትተነው ነው። ይህን ስል ግን “ ትክክለኛው አረዳድ ” በሚለው ላይ የታሪክ ምሁራን ራሳቸው ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ ለማለት አይደለም። ታሪክ ያለፈ አንድ ነገር የመሆን አለመሆኑን እውነትነት መግለጽ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በዋናነት የዚያን ኩነት ትርጉምና አንድምታ የሚተነትን በመሆኑ ያንን ታሪክ የሚጽፈው አንድ የታሪክ ሰው የሚያይበት መነጽር ስለዚያው እውነት ከሚጽፍ ሌላ የታሪክ ሰው ጋር የተለየ ሊሆን ይችላል። ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች። አንደኛው በመጀመሪያ ያ የተባለው የታሪክ ኩነት በተፈጸመበት ወቅት በአካባቢው የነበረና ጉዳዩን ከሰነደው ሰው አመለካከት በመጣ መዛባት። በጊዜው ሁኔታውን የሰነደውና ለወደፊት የታሪክ ተመራማሪዎች መነሻ የሆነውን ሰነድ ያዘጋጀው ሰው፤ በጊዜው በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሆኑት ብዙ ኩነቶች ውስጥ አንዱን መርጦ ይህ ለታሪክ አስፈላጊ ስለሆነ ይሰነድ ሲል፤ ወይንም ይህ ሰው ይህን ሥራ እንዲሠራ ኃላፊነት የሰጠውን አካል ( ብዙ ጊዜ የነገሥታት ባለሟሎች፤ ወይንም የሃይማኖት ወኪሎች ) ጥቅምና ፍላጎትን ማዕከል አድርጎ ሲሰንደው፤ ይህ በራሱ በሰነዱ ላይ የተቀመጡትን ኩነቶች ሐቀኝነት፤ ወይንም በትንተናው ልከኝነት ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ሁለተኛ ስለሁኔታው ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚጽፉት የታሪክ ምሁራን የሚጽፉበት ሁኔታ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የራሳቸውን የውስጥ አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆኑ ስለማይቀር ነው። እውነተኛ “ ሳይንሳዊ ” የታሪክ ጥናት ዘርፍ በታሪክ ሰናጆች ላይ ወገንተኛነት ( bias ) ሊኖር እንደሚችል በመገንዘብ ከተለያዩ ሰናጆች የቀረቡለትን በማመሳከር ወደ ሚዛናዊ አረዳድ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል የሚረዱ የጥናት አካሄድ መርሆች ( methodology ) ቢያስቀምጥም እንኳን ከብዙ ዘመን በኋላ የሚጻፍ የታሪክ ጽሑፍ በጸሐፊዎቹ በራሳቸው የውስጥ እምነት ግፊት ምክንያት ያጋደለ ትንተና ሊያቀርቡ የሚችሉበት ዕድል በጣም የሰፋ ነው። በነዚህና ሌሎችም ብዙ ተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ ሐቁን ብቻ ለማውጣት በሚፈልጉ እውነተኛ የታሪክ ምሁራን ዘንድ እንኳን በአንድ የታሪክ ኩነት ላይ የተለያዩ አረዳዶች ቢንጸባረቁ በፍጹም የሚገርም አይሆንም። ቢያንስ ግን ለሙያቸው እውነተኛ የሆኑ የታሪክ ምሁራን ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተቀብለው እነኝህን ልዩነቶች በተጨማሪ ጥናቶችና በሰከነ ምክንያታዊ ውይይት ለማቀራረብ፤ ይህም ባይቻል ሙያው በሚሰጣቸው ክህሎት እያዳበሩ፤ ልዩነቶቹን ይዞ ለቀጣይ ጥናቶችና ውይይቶች ከነኝህም ውይይቶች የበለጠ ለመማር ይዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል። የታሪክ ምሁራን ሙያችውን ረስተው በታሪክ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ አክቲቪስቶችን ወይንም ባለሥልጣኖችን ሲከተሉ ወይንም ጎራ ለይተው ከምሁራዊ ውይይት ወጥተው እንደአክቲቪስት ጭቃ መቃባት ሲጀምሩ ወይንም ደግሞ የሶሻል ሚዲያ ብሽሽቅን ፈርተው ለእውነት መቆም ሲያቅታቸውና አንዳንዴም ሆን ብለው ሰትን ሲያስተጋቡ፤ ያኔ ኅብረተሰብ ከታሪክ ምሁራኖች የሚጠቅሙና ወደፊት ሊያስኬዱት የሚችሉትን ትምህርቶች ሳያገኝ ይቀራል፤ ሲከፋም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መለስተኛ አለመግባባቶች ላይ የበለጠ ነዳጅ ያርከፈክፋሉ። እውነትን በሚፈልጉና ለሙያቸው ክብር ባላቸው ባለሙያዎች ዘንድ እንኳን በታሪክ ትንታኔና አረዳድ ላይ ልዩነት መንጸባረቁ የማያስገርም ከሆነ፤ ታሪክን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም፣ ያውም ሆን ብሎ ሰዎችን “ በተበደልኩ ” ስሜት ውስጥ በመክተት በማኅበረሰብ ውስጥ ልዩነትና መቃቃርን ለመፍጠሪያነት ለመጠቀም ለሚፈልጉ ኃይሎች፣ ታሪክ ትልቁ የማደናገሪያቸው መሳሪያ መሆኑ አይቀሬ ነው። ታሪክን ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙ ኃይሎች ማኅበረሰቡን ለማደናገሪያነት ከሚጠቀሙበት መንገድ አንዱና በተደጋጋሚ የሚታየው “ ቁንጽልነት ” ነው። የታሪኩን ሙሉ ስዕል ለማየት ከመሞከር ይልቅ ከታሪኩ ላይ ለራሳቸው የሚፈልጉትን ብቻ ቆንጽሎ አውጥቶ፤ የነሱን አላማ የማይደግፈውን ከታሪኩ ሰርዞ የማቅረብ አባዜ ነው። ይህ “ የግማሽ እውነት ” ስዕል ሰሚውን ለማሳሳቻ “ ከሙሉ ውሸት ” ይልቅ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ይታያል፤ ስለዚህም ብዙ ጊዜ በፕሮፓጋንዳ ስራ ላይ ሲውል እናየዋለን። ታሪክ ጥቁርና ነጭ አይደለም። በታሪክ የምንዘክራቸው ኩነቶች በጥሩነት የምናነሳቸው ብዙ ነገሮች የሚኖሩትን ያህል፤ ብዙ አስከፊ የሚባሉ ድርጊቶችም ይፈጸማሉ። ይህ ያንድ ሀገር ታሪክን የሚመለከት ሳይሆን ከሞላ ጎደል ሁሉንም የሰው ልጆች ታሪኮች የሚመለከት ጉዳይ ነው። በታሪክ አቀራረብ ላይ የቁንጽልነት ችግር ግን ሆን ተብሎ “ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ” የሚደረገው ብቻ አይደለም። በተወሰነ ደረጃ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተያያዘ ካልተጠነቀቅን ጭንቅላታችን ዕውነታውን ሙሉ ለሙሉ እንዳናይ የሚጋርዱን ሌሎችም ነገሮች አሉ። ከነኝህ ውስጥ ከዛሬው ውይይት ጋር የሚያያዘውንና የሥነ አዕምሮ ተመራማሪዎች “ በተመረጡና በቅርብ በጭንቅላታችን በምናስታውሳቸው ምሳሌዎች ላይ በመመርኮዝ አጠቃላይ እውነት ጋ የመድረስ ግፊት ”( the availability heuristic/bias ) የሚባለውን ለአብነት ማየት እንችላለን። ይህ ችግር በጣም ጎላ ብለው የሚታዩና ስሜታችንን የሚነኩ ኩነቶች፤ የዚያን ዓይነት ስሜት ከማይሰጡን ያዘቦት ኩነቶች ይልቅ በጣም በተደጋጋሚና በብዛት የሚከሰቱ አርጎ የማየት የሥነ አዕምሮ ግፊት ነው። ለምሳሌ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በየቀኑ በሰላም ከቤቱ ወጥቶ እየገባ፤ በዜና የምንሰማው ስለ ሰላሙ ሳይሆን ባብዛኛው በዕለቱ ስለተፈጸሙ ወንጀሎች ሲሆን ( በተወሰነ ደረጃ ቤት በሰላም ከገባው ሰው ይልቅ ስሜት ቀስቃሽ “ ወሬ ” የሚሆነው እሱ ስለሆነ ) በከተማችን / ባገራችን በጣም ብዙ ወንጀሎች በየቀኑ የሚፈጸሙ ይመስለናል። የየትኛውንም በታሪክ ጸሐፊዎች የተጻፉ የሰው ልጅ ታሪኮች ወይንም በተለምዶ የምንሰማቸውን “ አፈ ታሪኮች ” ብንመለከት አብዛኛው የሰው ልጅ ታሪክ ሰላም ትንሽ ትንሽ የተርከፈከፈበት ጊዜያት ያሉት፣ ግን ባብዛኛው የሰው ልጅ ጊዜውን በጦርነት ላይ ያሳለፈ ነው የሚመስለው። ዕውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። የሰው ልጅን የረጅም ጊዜ ታሪክ ላየ፤ የሰው ልጅ ብዙውን ጊዜውን በሰላምና የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ በሚያደርጋቸው ጥረቶች፣ ግን ደግሞ ትንሽ ትንሽ ጦርነት የተርከፈከፈባቸው ጊዜያት ነበሩ። የታሪክ ጸሐፊዎች የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ሕይወት መጻፍ ሳይሆን የሚፈልጉት “ ወሳኝ የሚባሉ ኩነቶችን ” መዘገብ ስለሆነ እነኝህ ወሳኝ ኩነቶች ደግሞ ባባዛኛው ከጦርነት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ፤ ስለታሪክ የምንሰማቸውና የምናነባቸው ብዙ ነገሮች ስለሰላም ሳይሆን ስለጦርነት የሚያወሩ፤ ስለ የዕለት ተዕለት ለኑሮ የሚደረግ ትብብር ሳይሆን ስለ ግጭቶችና መስፋፋቶች የተጻፉ ናቸው። ነገር ግን አብዛኛውን የሰው ልጅ የሥልጣኔ ታሪክ ካየን፤ ሕይወትን ለማሻሻል የሚደረጉ የዕለት ተዕለት ትግሎች ናቸው ከተሻለ የአስተራረስ ዘዴ ወደ ዘመናዊ እርሻ፣ ከሰውና የእንስሳት ጉልበት መጠቀም ወደ ሜካኒካል ጉልበት፣ ባጠቃላይ አሁን ላለንበት አራተኛው የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደረሱን። ምንም እንኳን ለጦርነት ሲባል የተደረጉ ምርምሮች ለሌሎች የቴክኖሎጂ ዕድገቶች አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ባይካድም። 1 በዚህ የውይይት መርሀ ግብር እኔ እስከገባኝ ድረስ በደንብ እንዲወሳ የፈለጋችሁት ( ለጉባዔው ካዘጋጃችሁት መነሻ ጽሁፍ እንዳየሁት ) ይህንን ቁንጽል የሆነ የታሪክ አተያይ ለማረም ያለመ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ መጥፎ ብቻ ሳይሆን በጣም ብዙ ጥሩ ነገሮች እንዳሉትም ለማመላከት ያለመ ይመስላል። በተለይ አሁን ባለንበት “ የልዩነትና የማንነት ” ፖለቲካ በነገሠበት፤ ወሬውና ውይይቱ ሁሉ ( ውይይት ከተባለ ) ስለማንነትና በማንነት ዙሪያ ስለሚከሰቱ “ በደሎች ” በሆነበት ጊዜ 2 የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን በነኝህ የተለያዩ ማንነቶች ውስጥ ስለነበሩ ብዙ አዎንታዊ መስተጋብሮች ( በዘውጌ ማኅበራት መካከል የነበሩ የባህል ልውውጦችና መቀያየጦች፤ የጋብቻ ትስስሮችና መዋለዶች፣ የቋንቋ መሳለጦች፣ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች ተሳትፎ፣ የመኖሪያ ቦታዎች በስደት መቀያየር፣ በሃይማኖቶች መካከል ስለነበረው መቻቻል፣ ጠንካራ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስሮች ... ወዘተ ) በጽሞናና በምክንያት ላይ ተመስርቶ መወያየት፤ ካሉን ልዩነቶች ይልቅ ብዙ የምንጋራቸው ነገሮች መኖራቸውን ለማሳየት ይጠቅማሉ። በዚህም በማኅበረሰባችን ውስጥ የሚታየውን ውጥረት ለማብረድ የሚረዳ አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው። ታሪካችንን በስፋት ማየት ከቻልንና በታሪክ የማኅበረሰባችን አብዛኛው ጊዜ ያለፈው ከጦርነት ውጭ ባሉ የዕለት ተዕለት የሕይወት ትግሎች ላይ መሆኑንና እነኝህ የሕይወት ትግሎች ደግሞ አይደለም ባንድ ሀገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ የዘውጌ ማኅበረሰባት፣ ብዙ ድንበር ዘለል የሆኑ ትብብሮች፣ ሁሉንም በጋራ የሚረዱ መጠቃቀሞች ( ለምሳሌ በንግድ አንዱ የማያመርተውን ከሌላው እየሸመተ የኢኮኖሚ ሕይወቱን የሚያሻሽልበት ወይንም በአካባቢው ያልለመደውን ያመጋገብ ዘዬ ከሌላው ቀስሞና የሱንም ለሌላው እያሳየ የባህል ሀብታም የሚሆንበት፣ ከግንኙነት ብዛት የተለያዩ ቋንቋዎች እየተጨፈለቁ አንድ የመግባቢያ ቋንቋ የሚወለድበት ... ወዘተ ) ፣ በጋራ የሚደረጉ እራስን ከሩቅ ጠላት ወይንም ከተፈጥሮ አደጋ ለመታደግ የሚደረጉ ትብብሮች የሚፈጥሯቸው የአንድ ዕጣ ፈንታ ተጋሪ የመሆን ቅርበት የሚታዩባቸው፣ መሆናቸውን ማሳየት ከቻልን፤ የማኅበረሰባችንን ትኩረት ከልዩነት ወደ አንድነት፣ ከመናቆር ወደ መተሳሰብ፣ ከመጣላት ወደ መፋቀር፣ ከሌላው ውድቀት ለመጠቀም ከመዳከር ወደ ጋራ ብልፅግና ለመሄድ ወደ መተባበር እንመልሰዋለን። በዚህ ደግሞ ሁላችንም ( እንደ ግለሰብ፣ እንደ የወል ስብስብ፣ ብሎም እንደ ሀገር ) እንጠቀማለን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ይመስላል። ይህን መልዕክት ደግሞ በባዶ ፕሮፓጋንዳ ላይ በመመሥረት ሳይሆን በዕውቀት ላይ፤ በቁንጽል በሚታዩ አንዳንድ የጦርነትና የግጭት የታሪክ ኩነቶች ላይ ብቻ በማተኮር ሳይሆን በአብዛኛው እውነት መሆኑ በሚታወቀው የሕዝቡ የዕለት ተዕለት የሰላምና የትብብር መስተጋብር ላይ የታሪክ መነጽራችንን በማነጣጠር እናገኘዋለን የሚል አንድምታ ያለው መልዕክት ነው። እኔ የዚህን የዐውደ ጥናት ዓላማ ሙሉ በሙሉ እደግፈዋለሁ። እንደዚሁ ከላይ የጠቀስኩት ዓይነት ሌላ ተጨባጭና ተግባራዊ የሚሆን ማኅበራዊ ጥቅም ባይኖረው እንኳን፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ የሆነ እውነትንና ዕውቀትን የመፈለግ የውስጥ ግፊት አለበት ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም በምክንያታዊነት ዕውቀትንና እውነትን የመፈለግ ጥረት ሁሌም የሚበረታታና ለሰው ልጅ ሥልጣኔ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ፤ ሰውን ከሌላ እንስሳት የሚለየውም ይህ ክህሎቱ ነው። ሰው ለመኖርና ራሱን ለማስቀጠል ከተፈጥሮ ተጠቃሚነት ተሸጋግሮ የተፈጥሮን ምስጢሮች ዐውቆ ዓለማችንን የተቆጣጠረውም በዚህ የማሰብ ችሎታው ነው ( እግረ መንገዱን በተፈጥሮ ላይ ብዙ ጥፋቶችንም አጥፍቶ ) ። በርግጥም ልዩነቶችን በማስፋት ማኅበረሰብን ወደግጭት ለመክተት የሚጥሩ መሰሪዎችን ዓላማ በታሪክ ዕውቀት ላይ በተመሠረተ ምክንያታዊነት ለማክሸፍ መሞከር የሚበረታታ ጥረት ነው። ፍርሃቴና ጭንቀቴ ግን፤ የተጣመመ የታሪክ አረዳድን ማስተካከል ብቻውን ከገባንበት የህልውና አጣብቂኝ ያወጣናል ወይ ? ይህስ በራሱ በቂ ነው እንኳን ብንል የገባንበት ችግር የዚህ አይነት የታሪክ አረዳድን የማስተካከል የረጅም ጊዜ ስራ እስክንሰራ ጊዜ የሚሰጠን ነገር ነው ወይ ? የሚለውን ሳስብ ነው። በነኝህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ጥቂት ብዬ ላብቃ። 1 በዚህ ላይ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ኑሮን ማሳየት የታሪክ አንድ አስፈላጊ አካል መሆኑን በፈረንሳዩ የታሪክ ምሁር ፈርናንድ ብራውዴል የሚመራው Annales school የታሪክ ትምህርት ክፍል ይህንን የሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ማዕከል ያደረገ የተለየ የታሪክ አቀራረብ ( social history ) ጀምረው የታሪክ ትምህርትን በበጎ መልኩ ወደዚያ አቅጣጫ መርተውታል። 2 ይህ በደልን የማጮህ አባዜ ጫፍ ደርሶ፤ ባሁኑ ጊዜ “ የዘር ማጥፋት በደል ”( genocide ) ደረሰብኝ የማይል ዘውጌ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለ አይመስልም። በመጀመሪያ አሁን ያለንበትን የህልውና ችግራችንን ስመለከተው ዋና ችግሩ አለ ብዬ የማምነው የኢትዮጵያን ሥርዓተ መንግሥት በምን መነሻ መርህ ( bedrock principle ) ላይ ብናቆመው ነው ለአብዛኛው ሕዝብ ሥርዓተ መንግሥቱ ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል ብሎ እንዲቀበለውና በዚህ መነሻ መርህ ላይ የተመሠረተን የመንግሥት ሥርዓት ተቀባይነት የሚሰጠው ? የሚለው ያልተመለሰውና በቂና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውይይት ከማድረግ የምንሸሸው ጥያቄ ነው። ቀድሞ የነበረው ሥርዓተ መንግሥት እኔን በተለየ ማንነቴ ምክንያት በድሎኛል የሚል የወል ስብስብ፤ ሥርዓተ መንግሥቱ በምን የእኩልነት መርህ ላይ ቢታነጽ ነው እንዲህ ዓይነት በደሎች ወደፊት በኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በማንም ላይ እንዳይደርሱ ማድረግ የሚችለውና የተረጋጋ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ሊሰጠን የሚችለው የሚለውን ወሳኝ የፖለቲካ ሥርዓት ጥያቄ መመለስ መቻል ነው። ይህን ጥያቄ መመለስ ቀላል ነው እያልኩ አይደለም። ግን ጥያቄውን በተገቢው መልክ ከጠየቅን መልሱን ለማግኘት ቢያንስ ግማሽ መንገድ ሄደናል ማለት ነው። መልሱን የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ብቻቸውን የሚመልሱት ሳይሆን፤ ከራሳችንም ታሪክ ውጭ ካሉ የሰው ልጅ ዕእውቀቶችና ልምዶች አዳቅለን፤ ዛሬ የሰው ልጅ ከደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ አንጻር መዝነን፤ እነኝህ ላለመስማማታችን ምክንያት ናቸው የምንላቸው በደሎች ለወደፊቱም እንዳይመጡ የሚያስችለን መዋቅራዊ መጠበቂያዎች ስናበጅለት ነው መልስ ልናገኝለት የምንችለው። ይህን መመለስ ካልቻልን፤ በታሪክ ላይ የሚነሱትን አለመስማማቶች በሆነ መንገድ ብናስታርቃቸው እንኳን ዋናውን ጥያቄ ለመመለስ ለምናደርገው ጥረት አስፈላጊ ግብአት ይሆኑልን እንደሆነ እንጂ ( ለምሳሌ በዋናው ጥያቄ ላይ የምናደርገውን ውይይት ከመናቆርያነት አውጥተው ምክንያታዊ የሆነ ምክክር እንድናደርግ ) በራሳቸው አይመልሱልንም። ስለዚህ የመጀመሪያው ሥራ የፖለቲካ ሥርዓታችንን ዘመኑን የዋጀና በጠንካራ የእኩልነት መርህ ላይ የቆመ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ዛሬ የአመለካከት ችግር ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሥርዓቱን ምንነት አሁን ከሚሰጣቸው ጥቅም ጋር ብቻ እያያያዙ፤ ይህን ጥቅማቸውን ላለማጣት፣ አገርንም ቢያጠፋ እንኳን፣ ባለ አቅማቸው ለመታገል የተዘጋጁ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች በመኖራቸው ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ሥርዓቱ በምን መሠረታዊ መርህ ላይ ይቁም ለሚለው የአስተሳሰብና የመርህ ውይይት የታሪክ ምሁራን ከሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ጋር በጋራ የመምከርና መፍትሄ የመጠቆም ኃላፊነት እንዳለባቸው ተቀብለን፣ ችግሩ የተግባራዊ የፖለቲካ ትግልም የሚጠይቅ መሆኑን አውቀን፣ ይህን የመርህ ጥያቄ መሬት ለማውረድና ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሰፊ የሆነ የፖለቲካና የሕዝብ ግንኙነት ሥራም እንደሚፈልግ ለማመልከት ነው። ከዚህ ጋር የተያያዘው ሁለተኛው ጉዳይ ከጊዜ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። በረጅሙ አስበን፤ የተረጋጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ የሆነው በሰዎች አስተሳሰብ ላይ የሚሠራው ሥራ እንደሆነ እንኳን ብንስማማ ( ለምሳሌ በትምህርት ሥርዓታችን መዳከምና ብዙ ያልተላመጡና በጊዜያዊ የፖለቲካ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶች ለልጆቻችን ለረጅም ጊዜ መስጠታችን አሁን ለገባንበት የማንነትና የሞራል ድቀት ቀውስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ብናምን ) ፤ ይህንን የአስተሳሰብ ለውጥ በማህበረሰብ ደረጃ ለማምጣት ረጅም ጊዜ የሚወስድብን እንደሆነ ጥያቄ የለውም። አንድ ሙሉ ትውልድ ሊወስድብን ይችላል። ግን አገራችን አሁን ላለችበት ቀውስ የዚህ ዓይነት የረጅም ጊዜ መፍትኄ ከመሞቷ በፊት ይደርስላታል ወይ ? የሚለው የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። በረጅም ጊዜው መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እየተሰሩም ግን በዋናነት ተግባራዊ የሆኑ፣ አደጋው ከቁጥጥር እንዳይወጣ ለመከላከል የሚወሰዱ ጠንካራ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የደህንነት ውሳኔዎችና ሥራዎች መኖራቸው የግድ ይሆናል። በሌላ አነጋገር ጊዜው የሚጠይቀው በአመለካከት ላይ የሚሠሩ የረጅም ጊዜ ሥራዎች እየተሠሩም፤ በመካከለኛና ባጭር ጊዜ መሠራት ያለባቸውን የፖለቲካ፣ የሕዝብ ግንኙነት፣ የኢኮኖሚ ሕይወትን የሚያሻሽሉ፤ ለማኅበረሰቡ ከሙስናና ከአድልዎ የጸዳ የአስተዳደርና የዳኝነት ሥርዓት መዘርጋት፤ እንዲሁም የሀገርንና የሕዝብን ደህንነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች አዳብሎ መሥራትንም ይፈልጋል። ለዚህ ነው የገጠመን ችግር የተወሳሰበ ስለሆነ መፍትኄውም ጥንቃቄንና በጥልቀት ማሰብን የሚጠይቀው። ይህ ደግሞ የተለያዩ ክህሎቶችን የሚጠይቅ፤ ሰፋ ያለ የሕብረተሰብ ክፍል ሊቀላቀላቸውና ሊተባበርባቸው የሚያስፈልጉ ሥራዎች ናቸው። ስለዚህም የታሪክ ምሁራን “ የኔ ጉዳይ የጎበጠውን የታሪክ አረዳድ ለማቃናት መሞከር ” ነው ብለው በሙያቸው ብቻ ታጥረው ሳይቀመጡ፤ እንደ ዜጎች ይህንን አደጋ ለመከላከልና ብሎም ቀልብሶ ሀገራችንን በተረጋጋ የፖለቲካ መሠረት ላይ ለማቆም የሚደረገውን ጥረት ማገዝና ሁነኛ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ታደርጋላችሁ ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምናለሁም። ከፊታችን የሚጠብቀን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ይህን ዕድል ለሁላችንም ይሰጠናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በብልኽነት እንጠቀምበት። አመሰግናለሁ ! I. ጽንሰ ሐሳባዊና ታሪካዊ ዐውድ የሕዝብና የቁሳቁስ እንቅስቃሴዎች፣ አንቀሳቃሾችና አካላዮች በኢትዮጵያ፤ ጽንሰ ሐሳባዊና ታሪካዊ ንባቤ ዶ / ር ተካልኝ ወልደማርያም ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረውን የሰውና የቁሳቁስ እንቅስቃሴ ዋና ዋና ገጽታዎች የሚዳስስ ሲሆን፤ ከነዚህ እንቅስቃሴዎች በተያያዘ የአንቀሳቃሸነት እና የአካላይነት ( ወይም ገዳቢነት ) ሚና የተጫወቱ ኃይሎችን አፈጣጠርና እድገት እንዲሁም የአስተሳሰብና የድርጊት መገለጫዎች ይቃኛል። እንደመንደርደሪያ ያገለግል ዘንድ የጽሑፉ የመጀመሪያ ክፍል በተለያየ የጊዜና የቦታ አውድ ውስጥ ‹‹ ሰው ›› እና ‹‹ ቁሳቁስ ›› በሚባሉት ተንቀሳቃሸ አካላትና ‹‹ አንቀሳቃሽ ›› እና ‹‹ አካላይ / ገዳቢ ›› ተብለው በተጠቀሱት አድራጊ አካላት መካከል ሊኖሩ የሚችሉትን ልዩነቶችና ተያያዥነት በሚያመላክት መልኩ ጽንሰ ሐሳባዊ ገለጻ ያደርጋል። ይህም ገለጻ የሚያተኩረው እንደ ጊዜውና ቦታው ሁኔታ ሰውና ቁሳቁስ አንቀሳቃሸና ተንቀሳቃሸ ብቻ ሳይሆኑ ( ለምሳሌ እንደባሪያ ንግድ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ) ተጨፍልቀው አንድን አካል የሚገልጹ መጠሪያዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ እንደዚሁም ‹‹ አንቀሳቃሸ ›› ና ‹‹ አካላይ / ገዳቢ ›› የሚባሉት አካላት ብዙ ጊዜ የሚለያዩና ተቃራኒ ኃይሎች ቢሆኑም የማይለያዩበትም ጊዜና ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል በማስገንዘቡ ላይ ነው። የጽሑፉ ሁለተኛ ክፍል የዚህን ጉዳይ ታሪካዊ ዳራ እንድንረዳና እንድንመዝን የሚያስችሉንን የኢትዮጵያ ታሪክ ምዕራፎች ? ‹‹ ቅድመ ዘመናዊ ›› እና ‹‹ ዘመናዊ ›› ብሎ በመለየትና ለየዘመናቱም አግባብነት ባላቸው የመረጃ ምንጮችና ፋና ወጊ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ በመመርኮዝ የሚከተሉትን ዋና ዋና ግኝቶች ያስቀምጣል። 1 ኛ ) ከ 19 ነኛው መቶ ዓመት መገባደጃ በፊት በነበረው ‹‹ ቅድመ ዘመናዊ ›› የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ፣ ሀ ) የሕዝብም ሆነ የቁሳቁስ እንቅስቃሴ ባልተገደበና በማያ ë ርጥ ሁኔታ ሲካሄድ በመቆየቱ የአካባቢያችን ታሪክ ዓይነተኛ መገለጫ ብቻ ሳይሆን ዋነኛ ማጠንጠኛም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለ ) የሕዝብም ሆነ የቁሳቁስ እንቅስቃሴዎችን ምክንያቶች፣ አቅጣጫዎችና መዳረሻዎች በዋነኝነት ሲወስኑ የቆዩት የአካባቢው ሥነ ምኅዳራዊ እውነታዎችና የሰውና የተፈጥሮ ሀብት ስርጭቶች ናቸው። የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ( ለምሳሌ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ውሃና የግጦሽ ሳር እጥረትና እነዚህ ያስከተሏቸው ግጭቶች ) የእንቅስቃሴውን አቅጣጫዎች መጠንና ፍጥነት ሲለዋውጡት ቢቆዩም፤ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በእንቅስቃሴው ያልተነካና ያልተነካካ አካባቢ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሐ ) የታሪክም ሆነ የሌሎች የጥናት መስኮች ምሁራን ትኩረት ሲያደርጉባቸው ከቆዩት ታላላቅ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ይልቅ ዓይነተኛ ሚና የነበራቸው ትናንሽ የሕዝብ ክፍሎችና ቡድኖች በአስገዳጅ የኑሮ ሁኔታዎችና ፍላጎቶች ምክንያት ያደረጓቸው እንቅስቃሴዎች ነበሩ። በተመሳሳይም የቁሳቁስን እንቅስቃሴ በተመለከተ ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር የተያያዙ የምርት መገልገያዎች፣ አልባሳት፣እንደዚሁም የአዝርዕትና የእንስሳት ዝርያዎች ዝውውር ብዙ ትኩረት ከተደረገባቸው የረጅም የንግድ መስመር ሸቀጦች ዝውውር ያልተናነሰ ሚና ነበረው። መ ) የእንቅስቃሴዎቹን ሂደትም በተመለከተ የመረጃ ምንጮቻችን የሚያመለክቱት የመፈቃቀድም ይሁን የግፊት፣ የድርድርም ይሁን የሽግሽግ መልክ ሊኖረው የሚችል ሆኖ በአንድ ጊዜ ሳይሆን ዘለግ ያለ ጊዜ ወስዶ ደረጃ በደረጃ የተከናወነ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል ዝምድናንና ጎረቤታዊ ትስስርን በሚፈጥር መልኩ የተከናወነ መሆኑን ነው። በውጤቱም ረገድ እንደዚሁ የተለያየ ገጽታ የነበረው ሲሆን፤ በተለይም ከረጅም ጊዜ ዘርፈ ብዙ መስተጋብር በ  ላ ‹‹ ነባር ›› እና ‹ መጤ › በሚባሉ ወገኖችና ቁሳቁስ መካከል የሚኖረው ጊዜያዊ ልዩነት እየቀነሰና በአብዛኛውም እየጠፋ በአንድነቱ የሚገለጽ ሕዝብ ትስስር ታሪክ መገለጫ መሆናቸውን ነው። ሠ ) ከነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጥቂቶቹ በኃይልና በግጭት የተከናወኑ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን ቡድኖች ወይም ክፍለ ሕዝቦች በተናጠልና በራስ ተነሳሽነት የሚያደርጓቸው ነበሩ። በዚህም ምክንያት ሦስተኛ ወገን አንቀሳቃሾች ( ማለትም የተደራጁ የመንግሥት ወይም የጦር ኃይሎች ) የነበራቸው አስተዋጽዖ የተወሰነ ነበር። 2 ኛ ) በ 19 ነኛው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ በጀመረውና ከ 20 ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ በ  ላ በጎለበተ መልኩ በተንሰራፋው ‹‹ ዘመናዊ ›› ብለን በምንጠራው የኢትዮጵያ ታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በብዙ መልኩ በቀደመው ምዕራፍ ውስጥ ከነበረው በተለየ ሁኔታ የሕዝብም ሆነ የቁሳቁስ እንቅስቃሴዎች በኃይል፣ በትእዛዝና በተደራጀ የሦስተኛ ወገኖች ፍላጎቶችና ውሳኔዎች ላይ ተመሥርተው የሚደረጉ እየሆኑ መጥተዋል። ለዚህም ሂደትና ዝንባሌ ማዕቀፍ ከሆኑት ታላላቅ ክስተቶችና ኩነቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ነበሩ። ሀ ) በተደራጀና በጦር ኃይል በጎለበተ እርምጃ ከፍተኛ የግዛት ማስፋፋት እንቅስቃሴዎች መካሄዳቸው፤ ለ ) እነዚህን የመስፋፋት እንቅስቃሴዎች ተከትሎ የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት መገለጫ ድንበሮችንና የአገር ውስጥ አስተዳደራዊ ወሰኖችን የማካለል ሂደት በሰፊው መካሄዱ፤ የሆነው ዓለም አቀፋዊ ሐ ) ተጠያቂነት የሌለበት፣ አሳታፊ ያልሆነና በእጅጉ የተማከለ የአስተዳደርና የውሳኔ አሰጣጥ ጊዜ እየጎለበተና እየተንሰራፋ መምጣቱ፤ እና ሥርዓት ከጊዜ ወደ መ ) ከፍተኛ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዙና የሚያበረታቱ፣ በ ‹‹ ዕቅድ ›› እና በ ‹‹ ፕላን ›› የሚመሩ፣ ሳይንሳዊ አመለካከትንና ባለሙያነትን የተንተራሱና በተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች የታገዙ የሕዝብን መኖሪያ ቦታዎችና አኗኗርን ለመለወጥ የታለሙ ብዙ ፕሮጀክቶች መከናወናቸው ናቸው። ከላይ በሀ ) ክፍል ከተጠቀሰው በስተቀር ሌሎቹ ክንዋኔዎች እጅግ በገነነና በከረረ መልኩ ጎልተው የታዩት በወታደራዊና ሶሺያሊስታዊው መንግሥት ዘመን ነበር። በተለይ በዚህ ዘመን የተከናወኑት አስገዳጅ የሰፈራና የመንደር ምሥረታ እንቅስቃሴዎች ሕዝብን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከማስከፈላቸውም በላይ የመገፋትና የመጨቆን ስሜት በተፈጠረባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በኩል የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን መውለዳቸው አልቀረም። እንዲያውም ተመጋጋቢ በሚመስል መልኩ በማናለብኝነት ሲካሄዱ የቆዩት ሕዝብንና ቁሳቁስን የማንቀሳቀስ ድርጊቶች በጎለበቱ ቁጥር፤ ተቃውሞዎቹም እንደዚሁ እየጎለበቱ ከመምጣታቸውም በተጨማሪ የብሔርተኝነት ቅርጽና ይዘት እየያዙ መምጣታቸው ታይቷል። ከ 1983 ቱ የመንግሥት ለውጥ በ  ላ የታየው አዲስ ሥርዓት በመሠረታዊነት ቀደም ብሎ ከነበረው ሥርዓት በአወቃቀሩና በቅርጹ እንጂ በይዘት ብዙም የተለየ አልነበረም። ዓይነተኛ መገለጫው በ ë ን ë ወይም በብሔር ልዩነቶች ላይ የተመሠረቱ አዳዲስ ድንበሮችን ማካለልና በነዚህ ‹‹ ክልል ›› ተብለው በተሰየሙት እርከኖች ላይ የመንግሥትን ሥልጣን መሰብሰብ እንጂ በመላ አገሪቱ አዲስ የሥልጣን ቀመርና አሠራር ማስፈን አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በተለይም የኢ . ሕ . አ . ዴ . ግ መራሹን መንግሥት በተቃውሞ መዳከም ተከትሎ፣ የሚታየው በግጭቶች የተመላ ያልተረጋጋ ሁኔታ የሚያሳየውም እነዚህ ክልላዊ ድንበሮች በሰው እንቅስቃሴ ረገድ የሚጫወቱት የገዳቢነት ሚና የቁሳቁስ ወይም የሀብት እንቅስቃሴን በተመለከተ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በተመለከተ ገና ያልተ ë ጨ ክርክርና ትግል በመካሄድ ላይ የሚገኝ መሆኑን ነው። የጽሑፉ የመደምደሚያ ክፍል አሁን በግልጽ ከሚታየው የፖለቲካዊ ኤኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ይቻል ዘንድ ቢታሰቡና ቢደረጉ መልካም ነው የሚላቸውን ቁም ነገሮች ያስቀምጣል። ከነዚህም ውስጥ ከጥናቱ ርዕሰ ጉዳይና ጭብጦች በመነሳት በተለይ በአጽንዖት የሚያሳስበው፤ በቅርብ ጊዜው የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ታሪካችን ውስጥ በቂ ግምትና ትኩረት ያልተሰጣቸውን ሕዝባዊ ትስስሮችና መልካም ግንኙነቶች አጉልቶ የሚያወጣና በመንግሥታዊ መዋቅሩም ሆነ በዋና ዋና የሕዝቦች ግንኙነትና የሀብት ስርጭት ጉዳዮች ላይ የሕዝቡ ፍላጎትና ድምፅ እንዲሰማ የሚያደርግ አሳታፊ የውክልና ሥርዓት ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ነው። ይህም የውክልና ሥርዓት የሚፈለገውን ውጤት ያመጣ ዘንድ ከክልሎች ባሻገር ሕዝቡ በመስተጋብር በሚኖርባቸው እንደ ዞን እና ወረዳ ባሉ የታችኞቹ የመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ይመክራል። ይህም በአጭሩ የሕዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ በመፍቀድ፣ በማስቻልና በማነቃቃት የፓለቲካዊ አኮኖሚ ሥርዓቱን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ማለት ነው። II. ውህድና ቅይጥ ማንነት በቅይጥ ምንነት ላይ የተመሠረተ አገረ መንግሥት አስፈላጊነት (The Case for a Composite Nation- State) ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥትነት የገጠመው ተግዳሮት ሌሎች አገሮችም ያለፉብት ክስተት ይሁን እንጂ፤ ለችግሩ ወቅታዊ መፍትኄ ባለመፈለግ ወደ አደጋነት እንዲያድግ ጊዜ በመውሰድ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለየት ያደርገዋል። ይህ ችግር በከፊል በዜጎቿ ስንፍና በወቅቱ አስፈላጊውን ሥራ ለመሥራት ትጋትና ብቃት ስለጎደለ ታዝሎ ለዘመናት የቆየ ውዝፍ ሥራ ነው። በተለይ የ 20 ኛው ክፍለ ዘመን ከገባ በኋላ የጥንታዊቱን ኢትዮጵያ አገረ መንግሥትነት ለማዘመን የተደረጉት ሙከራዎች አዝጋሚና ሸንጋይ (superficial) ነበሩ የሚያስብል ነበር። ግማሽ ምዕተ ዓመት አገሯን ለመምራት ዕድል ያገኙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገሪቱን ከነበረችበት ሁለንተናዊ ኋላ ቀርነት አውጥተው ለ 20 ኛው ክፍለ ዘመን ቢያበቋትም፤ መሠረታዊ የምንላቸውን መዋቅራዊ ለውጦች ለማምጣት ተነሳሽነታቸውም ሆነ ድፍረታቸው ውስን ነበር። ለግል ሥልጣናቸውና ለግል ክብራቸው እጅግ ቀናተኛ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ትኩረታቸው የግል ዝናቸውን ከመገንባቱ እንጅ ኢትዮጵያን ዘመናዊ በሆኑ ተቋሞች አዋቅሮ መደላድሉ የፀና አገረ መንግሥት መገንባቱ ላይ አልነበረም። ባጭሩ ዘመኑ ይጠይቅ የነበረው ወሳኝ የአገረ መንግሥቱን ማዘመን ሥራ አልተሠራም። በዚህ አዝጋሚ፣ በወቅቱ አረዳድ “ ኋላቀር ” ፣ የሆነ ሥርዓት የተበሳጨው አዲስ ትውልድ ምኞቱ ከመቆርቆር ይመንጭ እንጂ ችግሩን እፈታበታለሁ ብሎ የተከተለው የጥድፊያ መንገድ ችግሩን ይበልጥ አወሳሰበው። የትውልዱ ዐይን ያረፈው አቋራጭ መንገድ ፍለጋ ላይ ስለነበር ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣልናል ብሎ ባመነው የማርክሲስት ርዕዮት ተጠለፈ። የእነ ጆሴፍ ስታሊንን “ የብሔር ጥያቄ ”( On the Question of Nationalities ) እንደ ዳዊት ደገመ። አዘምናታለሁ ብሎ የተነሳላትን አገረ መንግሥትነት በማጣጣል ትኩረቱ ሥር ነቀል ለውጥን መመኘት ላይ ሆነ። ፅንፍ አቋም ተሓድሶን እንደ ነውር ስለሚቆጥር አገሯ የነበራትን ትሥሥሮች አዳብራ፣ ገንቢ እሴቶቿን ተጠቅማ አስተማማኝ ወደ ሆነ ለውጥ እንዳታመራ ሁሉም ተሽሮ ከዜሮ ለመነሳት ጥድፊያ ተጀመረ። ያድናል ተብሎ ለአገሯ የቀረበው መድኃኒት እያደር ሕልውናዋን መፈታተን ጀመረ። ይህ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥትነት ጥያቄ ላይ አዲሱ ትውልድ ያሳየው ደንታ ቢስ (reckless) አዝማሚያ ይበልጥ አደገኛ ሆኖ የቀረበው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ( ሕወሃት ) በ 1983 ዓ . ም . ሥልጣን እንደያዘ ነው። ሕወሃት ትውልዱ በየዋህነት ያቀነቅነው የነበረውን ሐሳብ መሰሪ በሆነ መንገድ በመተግበር የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ መንግሥትነት ባሕሪ በመሸርሸር፣ አገሯ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዝምድናቸውን እንዲያፀኑ ሳይሆን በልዩነቶቻቸው ዙሪያ እንዲደራጁ አደረገ። ለዘመናት የተገነቡ ግንኙነቶች እየፈረሱ ሕዝቦች እንዲጠላሉና በየቀያቸው እንዲመሽጉ ተደረገ። ሁሉንም ያገናኙ የነበሩ የአብሮነት ትርክቶች አዲስ በተፈጠሩ ነጣጣይና የቁርሾ ትርክቶች ተተኩ። በሌላ አገሮች ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የሕወሃት መሪዎች የሚገዙትን አገር እያራከሱ፣ የሚገዙትንም ሕዝብ እያናከሱ የነሱን ጠባብ ዓላማ ማስፋፋቱን ተያያዙት። “ የሰው አገሩ ምግባሩ ” ይባል የነበረው የሰዎችን የትም ተንቀሳቅሶ የመኖር ብሂል ሽረው “ መጤ ” እና “ ተወላጅ ” የሚል ታርጋዎችን ከመለጠፍ አልፈው እነዚህን ልዩነቶች የሕግ ሽፋን በመስጠት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች በአንድ አካባቢ የመኖር ዕድላቸው ገደብ ተጣለበት። መሬትን የሚጠቀሙበት በላዩ ላይ የሰፈሩ ግለሰቦች መሆኑ ቀርቶ “ የብሔርና ብሔረሰቦች ” አፅመ ርስት ይሆናል በማለት አገሯን በሙሉ የጎሳ ደሴቶች (tribal enclaves) አደረጉት። የታደሉ አገሮች ጠባብ ከሆነ የዘውግ (ethnic) አወቃቀር ሰፊ ወደ ሆነና ግዙፍ ጉዳዮችን ወደሚያስፈፅመው አገረ መንግሥትነት (nation state) አድገዋል። እኛ አገር የተከሰተው ተፃራሪው ነው አገረ መንግሥቱን እያፈረሱ የዘውግ የበላይነትን ማንገሥ። አንድ ትውልድ ለሚሆን ዘመን ያለማቋረጥ የተሰበከው እንዴት የአንድ አገር ዜጎች እንደምንሆን ሳይሆን የነበሩትን ቀጭን ትስስሮች በጣጥሰን እንዴት ለየቅላችን መቆም እንዳለብን ነበር። ወንድም ወንድሙ ላያ እንዲነሳ ተቀስቅሷል። የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በጋብቻ መተሣሠራቸው በአደባባይ ተነውሯል፤ በዚህ ጋብቻ ውጤት የሆኑት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን “ ዲቃላ ” የሚል ማጣጣያ ስም እየተለጠፈባቸው ከዚህም ሆነ ከዚያ እንዳይሆኑ ያለውን ጫና በየቀኑ የምንታዘበው ሐቅ ነው። ሕዝቡ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የተበዳደለው በደል ካለ ይቅር እንዲባባል ሳይሆን የሚገፋፋው ለበቀል እንዲነሳ ነው። “ መጤ ” እና “ ተወላጅ ” የሚሉ መለያ ቅፅሎች ዓላማቸው ክፍፍሉን ዘላለማዊ ማድረግ ነው። አሁን ላይ እያየነው ያለው ያ ለአንድ ትውልድ ዘመን የተረጨው መርዝ እየፈጠረ ያለውን ቀውስ ነው። ቀን በቀን የምናያቸው በሕዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ ሰቆቃዎች የጭካኔውን መጠንና ባሕሪ አመልካች ናቸው። በዘውግ ላይ የተመሠረቱ ፖለቲካ አወቃቀር አራማጆች “ መጀመሪያ ተለያይተን በኋላ ላይ በመፈቃቀድ እንሰባሰባለን ” ይበሉ እንጅ የ 30 ዓመት ተሞክሯችን ያረጋገጠው ተፃራሪውን ነው። መሬት ላይ እያየን ያለው መፈቃቀዱና መፈቃቀሩ እየጠፋ ጥርጣሬውና ጥላቻው እያደገ ነው። ሕዝቦችን በዘውግ (ethnicity) ላይ በተመሠረተ ክፍፍል አስተዳደር ማደራጀት ለብዙዎቹ እርካታ ያስገኛል ተብሎ ነበር። በተግባር ግን የበለጠ ትርምስ፣ ሰቆቃና ብስጭት ሲፈጥር ነው የሚታየው። ችግሩ አንዱን ቀዳዳ ሲደፍኑት ሌላ ቀዳዳ እየፈጠረ በወንፊት ውሃ ለማቋት እንደመሞከር እየሆነ መጥቷል። ዛሬ የዚህ ቡድን የክልልነት ጥያቄ ተመለሰ ሲባል በጎኑ አራት አምስት የክልል እንሁን ጥያቄን እየወለደ ሄዷል። የክልሉ ጥያቄ ፋታ እየነሣ በላዩ ላይ አንዱ ዞን አምስት ካልሆን፣ ወረዳው ዞን ልሁን፣ ቀበሌው ልዩ ወረዳ አድርጉኝ የሚል መጨረሻ የሌለው፣ መቸም ተመልሶ የማያልቅ አዙሪት ውስጥ ተገብቷል። የዚህ ሁሉ ቀውስ ዓይነተኛ ምንጩ ሆን ተብሎ ክፍፍልን እንጂ ኅብረትን ታሳቢ ያላደረገው ሕገ መንግሥት ነው። ሕገ መንግሥቱ አቀራረፁ የመበተንን ሐሳብ የሚያበረታታ ከሆነ በታቀደለት ጐዳና መጓዙ አይቀሬ ነው (the constitution incentivizes fragmentation) ። ሕገ መንግሥቱ ለእያንዳንዱ የዘውግ ልሂቅ የየራሱን ዘውድ ያረጋግጥለታል። በተግባር ይህ የሚሳካው የዘውጉ አባላት የሚኖሩበት አካባቢ ከሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች የፀዳ እንደሆነ ነው (ethnic cleansing) ። ይህም በመሆኑ እያንዳንዱ የዘውግ ልሂቃን በሌላው ላይ በጎ ያልሆነ አመለካከት ያዳብራሉ (the image of the negatively significant other) :: የራሱን መጠቀም የሚያየው በሌሎች መከልከል አንፃር ነው (zero sum game) ። በመሆኑም ድንበሩን ማንም እንዳይደፍረው ከልሎ ያስቀምጣል :: ድንበር የመሬትም፣ የሥልጣንም መሠረት ስለሚሆን የየዘውጉ ልሂቃን ድንበራቸውን ከሌላ ይከላከላሉ፣ ያስፋፋሉ፤ ብሎም ወደ ግጭት ይገባሉ። ክልሉ የግላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ መጤ ናቸው የሚሉትን ማባረር አለባቸው። የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የልሂቃኑን ምንነትም ሆነ ጥቅማቸውን በዘውጋቸው ዙሪያ ስለወሰነው ልሂቃኑ መተዳደሪያቸውን የሚመሠርቱት በዚህ ዙሪያ ነው። እንጀራቸው ነውና ይሞቱለታል፣ ይጋደሉበታልም። ከዚህ አዙሪት እንዴት እንውጣ ? Albert Einstein እንዳለው “ አንድን እንደማይሠራ የተሞከረን ነገር ደጋግሞ መሞከር የዕብደት ምልክት ነው ” ። ይህ ማለት አዙሪቱን ለመስበር እዚህ ያደረሰንን መንገድ በጥሞና በመመርምር አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ ነው። ቀዳሚውና ሕልውናችን ፈተና ውስጥ የጨመረው ችግር በአገረ መንግሥትነቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች መሆናቸው ከታወቀ ለዚህ ችግር ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አገረ መንግስት (nation-state) እንደ ማንኛውም ማኅበራዊ ስብስብ ሰው ሰራሽ (human construct) ነው። ሰው ሠራሽ ከሆነ ሰው የሠራው እኛም አያቅተንም እና በሚያጠፋን መንገድ ሳይሆን በሚጠቅመን አኳኋን ልንቀርፀው እንችላለን። ይህ የቤት ሥራ ለነገ ተብሎ የሚዘገይ አይደለም። ታሪክ እስካሁን ያረጋገጠው ሐቅ ቢኖር ለፀናና የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት መሠረቱ የአገረ መንግሥት መቋቋም ነው። ከዚህ ጋር አብሮ ልብ ልንለው የሚገባ ሐቅ አገረ መንግሥትነት በድንገትና በአንድ አጋጣሚ ወቅት የሚፈጠር ክስተት ሳይሆን ብዙ ልፋትና ብዙ ዋጋ የሚጠይቅ ከዚያም አልፎ ኃይልና ጭካኔ ያጀበው የጦር እንቅስቃሴ ውጤት ነው። አሁን ተሳካላቸው የምንላቸው አገረ መንግሥቶች በዚህ ሂደት የተፈጠሩ ናቸው። ታዋቂው የጀርመን አገረ መንግሥት መስራች Otto von Bismarck እንዳለው “ አገረ መንግሥት ሲመሠረትና sausage ሲሠራ ቀርቦ መመልከት ያቅለሸልሻል፤ መጨረሻ ውጤቱ ግን ይጥማል ” ። እንዲህ ባለ ጥረት የተገነባውን አገረ መንግሥት ንዶ ሌሎች ተፎካካሪ የዘውግ መንግሥቶችን ለመመሥረት መሯሯጥ ምጡንና ስቃዩን እንደገና መመለስ ይሆናል። የሠለጠነውና ገንቢ የሆነው ዘዴ ሌሎች የደከሙበትን አፍርሶ ከዜሮ መጀመር ሳይሆን፤ እንዴት ያለውን አሻሽለን ለሁላችንም እርካታ በሚሰጥ መንገድ እናደራጀው የሚል ነው። ለውጥ የሕልውና ዋስትና ነው። ሕይወት ቀጣይነት የሚያገኘው ያለማቋረጥ በሚደረግ የለውጥ እንቅስቃሴ ነው። መለወጥ ያልቻሉ፣ ራሳቸውን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ማስማማት ያቃታቸው እንሰሳትና እፀዋት ጠፍተዋል። ሕይወት በተሓድሶ ቀጣይነቱን እንደሚያረጋግጥ ሁሉ፤ ሰው ሰራሽ የሆኑ ተቋማትም እንዲሁ ራሳቸውን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር በማስማማት፣ በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት እየታደሱ ይበልጥ ይጎለብታሉ፤ ቀጣይነታቸውንም አስተማማኝ በሆነ መሠረት ላይ ይገነባሉ። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥትነት ከጊዜው ጋር እንዲስማማ፣ ለአብዛኛዎቹ ዜጎች የበዛ እርካታ መስጠት እንዲችል፣ ቀጣይና ትርጉም ያለው ለውጥ ማካሄድ ያስፈልገዋል። የየትውልዱ ፍላጎት በተለወጠ ቁጥር፣ ዘመኑም አዳዲስ ተግዳሮቶች ይዞ ሲመጣ አገረ መንግሥቱ አዲሶቹን ፍላጎቶች የሚያስተናግድበት መዋቅራዊ ስልት እንዲኖረው ያሻል። በተለያየ የታሪክ ወቅት ዛሬ እኛን እንደገጠመን ዓይነት የምንነትን ጥያቄ የተጋፈጡ አገሮች ነበሩ። እነሱ ይህን ጥያቄ ያስተናገዱበትን ስልት ብናጤነው ጠቃሚ ትምህርት እናገኝበታለን። አገረ መንግሥታችን በምን ዓይነት ምንነት እንመሥርተው ? አገሩስ የማን ነው ? በመካከላችንስ ምን ዓይነት ዝምድና አለ ? የሚሉ ጥያቄዎች ካናወጧት አገሮች መካክል አንዷ አሜሪካ ነበረች። ይህ ጥያቄ ሲብላላ ቆይቶ በ 19 ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ ግጭት መርቷቸው ነበር። በመጨረሻም ከቀረቡት ክርክሮች መካከል ለብዙዎቹ አርኪ መስሎ የታየውና በተሻለ ስብዕና ላይ የተመሠረተው ሐሣብ “ አሜሪካ የዚህ ዘር፣ ወይም የዚያ ዘር አገር ሳትሆን ከየትም ይመንጩ፣ ከየትም ይምጡ አሁን ምድሯ ላይ የሚኖሩት የቅይጥ ሕዝቦች አገር ናት ” (a composite nation-state) የሚለው ነበር። ይህ ቅይጥ ማንነት (composite identity) ሰውን በሰውነቱ እንጂ በዘሩ ወይም በዘውጉ ምንነት የማይመዝን፣ ሰዎች ራሳቸውን የሚገልፁት ከሌላው በሚለያቸው ማንነት ሳይሆን ከሌላው ጋር በሚያዛምዳቸው የጋራ ግንኙነትና የጋራ ጥቅም ይሆናል። ሁሉም የሚጋሯቸው የጋራ ጥቅሞች ማለት እንደ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት ያሉ እሴቶች ለዚህ ዝምድና መጥበቅ ዋስትናዎች ናቸው። በነዚህ እሴቶች ላይ የተመሠረተ ዜግነት ይበልጥ አቃፊ፣ ይበልጥ ሰብዓዊ ነው። በአንፃሩ ጠባብ ምንነት ላይ አገረ መንግሥታችንን እንመሠርታለን የሚሉ ኃይሎች የሚሰባሰቡት ሌሎችን በማግለል፣ ከሌላ ዘውግ አባላት ጋር አለን በሚሉት ልዩነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሕዝቦችን እርስ በርስ የሚያናክስ፣ የዘር ማንአህሎኝነትን የሚያበረታታና ለግፍና ለሰቆቃ እርምጃዎች በር የሚከፍት ነው። ከቅልቅል ነፃ የሆነ፣ በፀዳ የዘውግ ዘር ምንነት ላይ የተመሠረተ ብሔረ መንግሥት (nation-state) እንመሠርታለን ብለው የተነሱ ኃይሎች በሰው ልጅ ዘር ላይ የፈፀሙትን ግፍ በሂትለር የተመራው የናዚዎች ቡድንና Afrikaners ተብለው ይጠሩ የነበሩት የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ ነጮችን መመልከት ይበቃል። በተናጠል የዘውግ ምንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ስብስብ በተፈጥሮው በሌሎች ኪሳራ ራሱን ማጎልበት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ለሁሉም ስጋት ከመሆን አያልፍም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ገና አገረ መንግሥትነቱ ሲጠነሰስ ጀምሮ በቅይጥ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በመሆኑ አሁን ከብዙ ዘመናት በኋላ ፍች እንፈፅም፣ የተቀላቀለውን እንለያየውና ነጠላ ማንነት ይንገሥ ከተባለ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስና ጥፋት ለመገመት አያስቸግርም። ኢትዮጵያን ከቀውስ ለመታደግ በቅይጥ ማንነት ላይ የተመሠረተ አገረ መንግሥትነትን የሚያጐለብት ተሓድሶ ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰራጨው የዘውግ ፖለቲካዊ ትርክት በኢትዮጵያውያን መካከል ለዘመናት የቀጠለውን የሕዝብና የባሕል መቀላቀል በበጎ ዐይን አይመለከተውም። ሕዝቦች በማይታረቁ ቅራኔዎች ጎራ እንደተሰበሰቡ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ይህን ትርክት ቀረብ ብለን ስንመረምረው የጐሣ ልሂቃን ሆን ብለው የቅራኔውን ትርክት ለነሱ በሚያመች መንገድ ቀርፀው ያሰራጩት የፈጠራ ቅራኔ እንጅ መሬት ላይ የሕዝቡን አብሮነት የሚከለክሉ፣ በተቃርኖ የቆሙ የፖለቲካ አመለካከቶችን አናይም። የጐሣ ልሂቃን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋነኛ ቅራኔ በአሐዳውያንና በፌደራሊስቶች መካከል ያለው ግብ ግብ ነው የሚል ትርክት አላቸው። በተግባር ግን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የፌደራልን ሥርዓት አልቀበልም የሚል፣ ወይም የድሮው ሥርዓት ይመለስልኝ ብሎ የሚታገል ኃይል እንደሌለ ይታወቃል። ስለዚህ “ አሓዳውያን ” የሚባለው ታፔላ እንዲሁ ሌሎችን ለማስበርገግና በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ የዜግነት ስሜትን ለማጥላላት ሆን ተብሎ የተፈበረከ ትርክት ነው። ይህ የተሳሳተ ትርክት መሬት ላይ የሌለ ቅራኔ ስለመሆኑ የማያሻማ ግንዛቤ ከተወሰደበት አንድ ጥቁር መጋረጃ ተገለጠ ማለት ነው። በመጨረሻም ባሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የአገረ መንግሥት ተሓድሶ ማን ያስፈፅመው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።፡ አስተማማኙ ኃይል የጉዳዩ ባለቤትና የዕዳው ተሸካሚ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ግን የዚህን ሕዝብ ጥረት አሰባስቦ ውጤት ለማስገኘት አጋፋሪ ያስፈልገዋል። የአገረ መንግሥት ተሓድሶ ግዙፍ ፕሮጀክት ስለሆነ ወደድንም ጠላንም ዕቅዱን ለማሳካት በመንግሥት እጅ ብቻ የሚገኘውን አቅም (resource) መጠቀም ይጠይቃል። መንግሥት ይህን ጉዳይ ለማስፈፀም መቻሉንና መፍቀዱን የሚጠሉ ሊኖሩ ይችላሉ። ግን አማራጩ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ሊሰመርበት ይገባል። በሐቅ ከተነጋገርን ምርጫው በጊዜው ያለውን መንግሥት ማስወገድ ወይም ከርሱ ጋር መሥራት ነው። አሁን ባለንበት የተጣበበና የተዘበራረቀ ሁኔታ ላይ መንግሥትን ለማስወገድ መሞከር የሚፈጥረውን ቀውስ መገመት አያስቸግርም። ይህን ሁሉ ችግር ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን የዜጎች ጥረት ማተኮር ያለበት መንግሥት ወደ ቀናው ጎዳና እንዲገባ፣ ኢትዮጵያውያንን ከሚያራርቁ ፖለቲካ ሻጥሮች ራሱን አፅድቶ፣ ገንቢ በሆነ ራዕይ ታንፆ ተሓድሶውን እንዲመራ መበረታታት አለበት። ይህ ገዥዎቻችንን የማብሰል፣ የማግባባትና ገንቢ ወደ ሆነው አቅጣጫ የመሳቡ ጥረት በእልክና በመገፋፋት ሳይሆን አዎንታዊ (positive) በሆነ ጫና ላይ መመሥረት አለበት። የሥነ አዕምሮ ጠበብት (psychologists) ይህን አቀራረብ (the nudge factor) ይሉታል፤ የሌሎችን ባሕሪ ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመሳብ የምንጠቀምበት ለስላሳ ግን ፍሬያማ ዘዴ ማለት ነው። ትክክለኛውን ጫና (pressure) በመጠቀም የጎበጠውን እንጨት እንደምናቀናው ሁሉ ሚዛኑን የጠበቀ ጫና በማሳደር የመንግሥት መሪዎችን ወደ ትክክለኛ ተግባራቸው መመለስ ይቻላል በሚል ዕምነት የተመሠረተ ነው። ውህድ ማንነት እና ብሔራዊ መግባባት ዶ / ር ቴዎድሮስ ዘውዱ ረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ወጎችና ባህሎች ተቀርፆ፣ ተገምዶና ተቆራኝቶ የተሠራ የጋራ እሴት ነው። እነዚህም የትስስርና የመስተጋብር እሴቶች ለኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን የሚያቻችሉበት ምቹ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወቶች ፈጥረውላቸዋል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እና የአስተዳደር ክፍሎችን የጋራ ቤታቸው አድርገው ሲመለከቱትና ሲኖሩበት የቆዩ መሆኑን ታሪክ በገሀድ ይመሰክራል። የውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች ለዚህ ታሪካዊ ጉዞ ዐይነተኛ ማሳያ ናቸው። ስለሆነም ከሳሎን ቤት እስከ አደባባይ ቤተሰባዊና ሀገራዊ ትስስር ሲያጠናክሩ ቆይተዋል። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ነባራዊ የትስስርና የመስተጋብር እሴቶችን በጠመንጃ ኃይል ያኮሰሰው፣ ያራከሰውና የደመሰሰው ኢሕአዴግ በ 1987 ዓ . ም . ባወጀው ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከነባራዊ የቦታ፣ የሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውጪ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች ሕገ መንግሥታዊ እና ክልላዊ ውክልና እንዳይኖራቸው ተደርገዋል። ስለሆነም የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት የውህድ ማንነት ያላቸውን ግለሰቦችና ቤተሰቦች ለሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አጋልጧል። ሥነ ልቦናዊ አንድ ሰው ሕይወቱን በተገቢ መንገድ ለመምራት የሥነ ልቦና ጥንካሬ ያስፈልገዋል። የሥነ ልቦና መቃወስ የደረሰበት ግለሰብ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ፣ ለወገንና ለሀገርም ሸክም ነው የሚሆነው። ይህንን ሳይንሳዊ ሐቅ በመፃረር የኢህአዴግ ሕገ መንግሥትና ክልላዊ መዋቅር የውህድ ማንነት ያለውን ግለሰብ ከራሱ ማንነት ጋር እንዲጋጭ ተደርጎ የተቀረፀ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ውህድ ማንነት ያለው ግለሰብ ማንነቱን የሚገልፅበት መንገድ በክህደት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ሕገ መንግሥቱና ክልላዊ መዋቅሩ ስለሚያስገድድ ነው። ለምሳሌ በ 2002 ዓ . ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ከቀበሌ መታወቂያ ለማውጣት በሞከርኩበት ጊዜ ለሙከራዬ የተሰጠኝ ምላሽ ውህድ ማንነቴን የሚያስክድ ነበር። ለቀበሌው ሹም የእናቴና የአባቴን ማንነት በሚገልፅ መንገድ መመዝገብ እፈልጋለሁ በምልበት ጊዜ ይህ አሠራር ለመታወቂያ መስፈርት እንዳልሆነ ተነገረኝ። የተሰጠኝ ምርጫ ውህድነቴን ክጄ በነጠላ ማንነት፣ ማለትም በአባቴ በኩል፣ የብሔር ማንነቴን ማስመዘግብ ነበር። ይህ ዓይነት አሠራር ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ አድርሶብኛል። እናትክን ካድ፣ ማንነትክን ካድ ማለት አንድን ግለሰብ ለከፍተኛ የሥነ ልቦና መዛባት ይዳርጋል። ስለሆነም አሁን ያለው ሕገ መንግሥታዊና ክልላዊ አደረጃጀት እስኪስተካከል ድረስ ውህድ ማንነት ያለው ግለሰብ በከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ስለሚገኝ አስቸኳይ ሕገ መንግሥታዊና ክልላዊ ለውጥ ያስፈልጋል። ማኅበራዊ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34/3“ ቤተሰብ የኅብረተሰብ መሠረታዊ መነሻ ነው። ከህብረተሰብና ከመንግስት ጥበቃ የማግኘት መብት አለው ” ይላል። በዚህ አንቀጽ መሠረት ቤተሰብ በሰዎች ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በማያሻማ ሁኔታ ተገልጿል። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የውህድ ቤተሰቦች የተሰጣቸው ምርጫ የመሰንጠቅ ዕድል ብቻ ነው። ማለትም የውህድ ቤተሰብ በሕገ መንግሥቱ ውክልና ለማግኘት ከእናት ማንነት መነጠል አለበት። ይህ ዓይነት ክልላዊ አደራጃጀትና ሕገመንግስታዊ አሠራር የውህድ ቤተሰቦችን የሕግ ከለላ ያፈርሳል። በተጨማሪም የዚሁ ሕገመንግሥት አንቀጽ 35/3“ ሴቶች በበታቸኝነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው ” ይላል። ሆኖም ግን ሕገ መንግሥቱ የተፃፈው እናቶች የማንነት መገለጫ የሚሆኑበትን መብት በመደፍጠጥና በመፋቅ ነው። የዚህ ኢሰብአዊ አሠራር ዓይነተኛ መገለጫው በውህድ ቤተሰቦች ላይ የደረሰው የመሰንጠቅና የመፍረስ ጫና ሆኗል። ይህ ኢሰብአዊ አሠራር እስኪታረም ድረስ የውህድ ቤተሰቦች ብቸኛ ምርጫቸው መሰንጠቅ ሆኗል። ፖለቲካዊ በ 1987 ዓ . ም . ሕገ መንግሥት መሠረት ፖለቲካዊ ውክልና በማንነት አማካይነት ብቻ ነው የሚመጣው። ማለትም አንድ ግለሰብ የዚህ ወይም የዚያ ብሔረሰብ አባልነቱን ካልገለጸ ክልላዊ ሆነ ሕገ መንግሥታዊ ውክልና ሊኖረው አይችልም። የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የነጠላ ማነነት እና የውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች መኖሪያ እንደሆነች ይጠቁመናል። ይህንን ታሪካዊ ሐቅ ያላገናዘበው ሕገ መንግሥታዊና ክልላዊ አደረጃጀት ሀገሪቱን ለነጠላ ማንነት ብቻ ነው አሳልፎ የሰጠው። በዚህ መሠረት ውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች በሕገ መንግሥቱና በክልላዊ መዋቅር ፓለቲካዊ ውክልና ተነፍገው ኢትዮጵያን በባይተዋርነት እንዲመለከቷት ተገደዋል። ይህ ኢሰብአዊ አሠራር በፍጥነት ካልታረመ ኢትዮጵያ የበደል ማዕከል ሆና እንደምትቀጥል ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ የጋራ ቤት ሆና እያለች የኢሕአዴግ አሠራር ውህድ ማንነት ያላቸውን ሰዎች የሚያገል መንግሥታዊ መዋቅር ዘርግቶ የሕዝብ ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቋቁሟል። ይህ ኢሰብአዊ አሠራር በፍጥነት ካልታረመ አገራችን ኢትዮጵያ የመከራ ቋት መሆኗ አይቀሬ ነው። ኢኮኖሚያዊ አንድ ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሠርቶ በልቶ በሰላም ለመኖር የኢኮኖሚ አቅም እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ኢሕአዴግ ባሰፈነው አሠራር መሠረት አንድ ግለሰብ በማንነቱ ምክንያት የኢኮኖሚ በደል እንደሚደርስበት ያደረግኩት ጥናት አመልክቷል። ለምሳሌ በ 2011 ዓ . ም ባደረግኩት የመስክ ጥናት ብዙ ውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች ሙሉ ማንነታቸውን ደብቀው በነጠላ ማንነት ራሳቸውን በማስመዝገብ የሥራ ዕድል ማግኘት እንደቻሉ ገልጸውልኛል። በዚህ አሠራር መሠረት ነጠላ ማንነት ያላቸው ሰዎች የኢኮኖሚያ አቅማቸው የደረጀ ይሆናል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ግን የውህድና የነጠላ ማንነት ያላቸው ሰዎች ሀገር በመሆኗ ውህዶች ያለአግባብ ማንነታቸውን ክደው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ኢሰብአዊ አሠራር ነው። ስለዚህ ውህዶች በኩራትና በነፃነት በኢትዮጵያ እንዲኖሩ ሕገ መንግሥታዊ እና ክልላዊ አደረጃጀቱ አካታች መሆን አለበት። ከላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ የትስስር እና የመስተጋብር ውጤት ነች። እነዚህ የጋራ እሴቶቻችን የሚገባቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቦታ በፍጥነት ካልተሰጣቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመፍረስ አትድንም። በውህድ ማንነት ዙሪያ ያደረግኩት የዶክትሬት ጥናት ይህንን ታሳቢ በማድረግ 11 ማረሚያ መንገዶች አስቀምጧል። በተጨማሪም ክልላዊ መዋቅሩ አካታች እንዲሆን 7 ማረሚያ መንገዶችን ጠቁሟል። 3 የ 1987 ዓ . ም . ሕገ መንግሥትን ስሕተት ለማረም ከላይ የቀረቡትን ትንተናዎችና ምክረ ሐሳቦች የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በጥሞና ተመልክቶ በፍጥነት መልስ እንዲሰጥባቸው ካልተደረገ የውህድ ማንነት ያላቸው ሰዎች ከሀገራቸው ገለልተኛ ሆነው፣ ራሳቸውን ክደው፣ እናታቸውን ርቀው በሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሚኖሩ በግልጽ መታወቅ አለበት። 3 “The Plight of Mixed Ethnic People in Ethiopia: Exclusion, Fragmentation and Double Consciousness”(York University, 2022). III. የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ታሪካዊ ትስስርና መስተጋብር የሕዝቦች መስተጋብር ተለዋዋጭነት ከዐባይ ወንዝ በስተደቡብ (1880-2008) ዶ / ር ደረጀ ሂነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አራቱን የወለጋ ዞኖችን የሚያጠቃልለው ምዕራብ ኢትዮጵያ የበረከት እና የእርግማን ምድር ሆኖ ቆይቷል። የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት እና ልዩ ልዩ የሥነ ምህዳር እና ለልማት አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ስላለው የበረከት ምድር ያደርገዋል። ክልሉ ግዙፍ የደን ሥነ ምህዳር እና እምቅ የግብርና ሀብት፣ እንዲሁም የወንዞች ሸለቆዎችን ( ማለትም፣ አባይ፣ ዳቡስ ፣ ዲዴሳ ፣ አንጋር ፣ ፊንጫኣ ፣ ዋማ እና ሌሎችን ) ያካትታል። እንዲህ ዓይነቱ የክልሉ የተፈጥሮ ስጦታ የብሔራዊ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት አድርጎት ቆይቷል። ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ትሩፋት ( በተለይም የውጭ ምንዛሪ በማመንጨት ረገድ ) የቡና ምርት እና የወርቅ ማዕድን ማዕከላትን መጥቀስ ይቻላል። በተለይም ክልሉ ለግብርና ምርት የሚውል በቂ ለም መሬት አለው። በተጨማሪም ይህ ክልል በክፉ ቀን ( ለምሳሌ እ . አ . አ . በ 1888-92 ፣ በ 1984/85 እና በ 2003/4 ተደጋጋሚ የድርቅ እና ረሃብ ወቅት ) ለተራበው ሕዝብ እንደ መተንፈሻ አገልግሏል። ሆኖም፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ በተለይ በቅርቡ፣ ይህ የአገሪቱ ክፍል የግጭት እና የመፈናቀል ማዕከል እየሆነ ነዉ። ሁለቱም ክስተቶች በዋነኛነት ክልሉ ከሁለቱ የሱዳን ግዛቶች ጋር ባለው ቅርበት ምክንያት ውስጣዊ እና ዓለም አቀፋዊ ገጽታዎች ነበራቸው። በቅርብ ጊዜ ሁለት እርስ በርስ የሚቃረኑ ክስተቶች በክልሉ ተስተውለዋል። የመጀመርያው በአባይ ወንዝ ላይ የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለክልሉ፣ ለሀገሪቱ፣ ብሎም በአጠቃላይ ለሰፊው የአፍሪካ ቀንድ የዕድገት ተስፋ ፈንጥቋል። በጥበብና በትብብር ጥቅም ላይ ከዋለ ግድቡ በአንድ በኩል ልማትን ለማፋጠን እና በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ላለው ግንኙነት የሰላም መሠረት የመሆን ትልቅ አቅም ይኖረዋል። በአንፃሩ፣ በዚህ ክልል የተከሰቱት ገዳይ ግጭቶች ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል፣ ለንብረት ውድመት እና ለሌሎች ተያያዥ ጉዳቶች መንስዔ ሆነዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አጎራባች ወረዳዎች ከመስከረም 2010 ዓ . ም . ጀምሮ ያለው ግጭት እና በቅርቡ በመተከል የተከሰተው “ ብሔር ተኮር ” ግጭት አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው። ይህ ክስተት ምክንያታዊነት የጎደለውና ሊቆጠር የማይችል ጉዳት ያስከተለ በመሆኑ በክልሉ እና ምናልባትም በአጠቃላይ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ በጣም መጥፎ ትዝታ ሆኖ ሊቆይ ይችላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምሥራቅ ወለጋ በሚኖሩ በኦሮሞ እና በአማራ ተወላጆች መካከል ተመሳሳይ ግጭት ተፈጥሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ ይህ ግጭት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ችግሮቹ ከ 19 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ ሕዝቦች በአካባቢያዊ ተቋሞቻቸው አማካኝነት የተቀናጁ ግንኙነቶችን የሚያደርጉበት እና እርስ በርስ የመደጋገፍ እና አብሮ የመኖር እሴቶች እንዲቀለበሱ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች እንድንመረምር ያሳስበናል። በክልሉ የሚኖሩ ሕዝቦች በአብሮነት፣ በመረዳዳት፣ በመከባበር መኖር የሚያስችላቸው ማኅበራዊ ተቋሞች መሥርተው ለዘመናት አብረው ለመኖር፣ ለመተባበር እና ብሎም ለመዋሃድ ችለዋል። በዚህ ረገድ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ማህበራዊ ተቋሞች እንደ ጉድፋቻ፣ ጋብቻ፣ ሚቹ ወይም ዲባንታ፣ ጋሉ ( መሸሸጊያ ) ፣አባሊጂ እና ሃርማ ሆዳ ( ጡት ማጥባት ) ያሉ የመዋሃድ መሳሪያዎች ሲሆኑ፣ ሌሎችም ብዙ ዓይነት የኢኮኖሚያዊ ትስስር መሳሪያዎች ነበሩ። ባለፉት ዘመናት ሃይማኖትን ጨምሮ እነዚህ ማህበራዊ ተቋማትና እሴቶች ትብብርን እና ውህደትን አረጋግጠዋል። ከምንም በላይ በኦሮሞ፣ በጉሙዝ፣ በበርታ፣ በአማራ፣ በትግሬ፣ በአገው እና በሌሎችም መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት እንዲኖር አድርጓል። እንዲህ ያለው ማኅበራዊ ግንኙነት በአስቸጋሪ ጊዜያት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አጋርነትን አስገኝቷል። ለአብነትም በ 1880 ዎቹ በደጃዝማች ሞሮዳና የናይሎ ሳሃራን ሕዝቦች መካከል የተደረገው መሐላ፣ በ 1950 ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአባ ጦኔ እና የአካባቢው ኦሮሞዎች መካከል የተደረገው ስምምነት፣ በ 1990 ዎቹ መጨረሻ፣ 2004 ፣ እና 2007/8 በ ‹‹ ጉሙዝ ኦሮሞ ›› እና በ ‹‹ ኦሮሞ አማራ ›› መካከል የተደረጉ ግጭት ፈቺ ስምምነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ይሁን እንጂ የአካባቢ እና ማዕከላዊ መንግሥታት እና ሌሎችም ተዋናዮች ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉ ጣልቃ በመግባት ነባር የሕዝቦች ግንኙነትን ተፈታትነዋል። በ 19 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የሱዳን ፍላጎት እና የቤላ ሻንጉል፣ የሌቃ እና የጎጃም ገዥዎች ፍላጎት፣ እንዲሁም የማዕከላዊው መንግሥት ተሳትፎ በአካባቢው አለመግባባቶችን ፈጥሯል። ጣልያኖችም ከ 1936-41 በነበራቸው የከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት የሕዝቦችን ትብብርና መደጋገፍ ረብሸው ነበር። ደርግ በስግሰጋ፣ ሰፈራና በሌሎችም የልማት ስትራቴጂዎች አማካይነት የብሔረሰቦችን ውህደት ቢያስፋፋም፤ በአንድ በኩል ነባሩን እና አገር በቀል የሆነውን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን በመሸርሸር፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ሰፋሪዎችን ተጠቅሞ የአካባቢውን ተቃውሞ በመቆጣጠር ማኅበራዊ ውሕደቶችን አዛብቷል። ባለፉት አምስት ዐሠርት ዓመታት ውስጥ በክልሉ የሰፋፊ እርሻ እና የማዕድን ቁፋሮ መስፋፋት፣ እንዲሁም ሰፈራ ያመጣው የሕዝብ ቁጥር መጨመር የሀብት ውድድር እና የወዳጅነት ለውጥ ፈጥሯል። በተጨማሪም የተሳሳተ የፌደራሊዝም ግንዛቤና አተገባበር፣ የተሳሳተ ትርጉም ለራስ እና ለሌሎች ( ‹‹ ነባር ›› እና ‹‹ መጤ ››) መስጠት ፣ የሥልጣን እና የሀብት መዳረሻ ብሔር ተኮር መሆኑ በሕዝቦች መካከል ያለውን አለመግባባት አባብሷል። በድኅረ -1991 ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ( የመሬት ፉክክር፣ የአማራ ፍልሰት፣ መደበኛ ያልሆነ የመሬት ድርድር እና የውል መጣስ ) ፣ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ( እኩል ያልሆነ የሥልጣን ድልድል ) ፣ ማህበረ ባህላዊ ( የአማራ ባሕላዊ ጎሰኝነት፣ የሌሎች ብሔረሰቦች የተጎጂነት ስሜት ) እና የሥነ ምህዳር ቀውስ ( በአማራ ሰፋሪዎች ከልክ ያለፈ የደን ሀብት ወድሟል መባል ) በክልሉ የግጭት መንስኤዎች ነበሩ። ከ 1990 ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የማኅበራዊ እና የፖለቲካ ልሂቃን፣ ባለሀብቶች እና ሌሎችም ተዋናዮች የግጭቶቹ መሐንዲሶች ነበሩ። ከላይ የጠቀስናቸው የማህበራዊ ተቋማት ማሽቆልቆል ተዋናዮች የተለያየ ማህበራዊ መነሻ ባላቸው ሕዝቦች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ዕድል ፈጥሯል። የግጭቱ መሠረታዊ መንስኤዎች ሳይፈቱ መታለፋቸዉ የፖለቲካ ምህዳሩ ግጭቶች በየጊዘዉ እንዲፈነዱ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ብሔር ተኮር ግጭቶች በክልሉ ሰፊ የሆነ የጸጥታ ችግር ፈጥረዋል። ይህም በአከባቢዉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና በአጠቃላይ የሀገር ግንባታ ላይ ስጋት ደቅኗል። በመሆኑም በክልሉ ውስጥ በሕዝቦች መካከል መተማመንን እና መግባባትን ለመፍጠር የተዋናዮችን ጣልቃ ገብነት መገደብ፣ የሀገር በቀል ተቋማትን ማነቃቃት፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ግንኙነት ማሳደግ፣ የሀብት አስተዳደርን ማጠናከር እና በወጣቶች ልማት ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ታሪክ በጊቤ፣ ጎጀብና ዲዴሳ ሦስት ማዕዘን ( ጅማ ዞን ) ዶ / ር ዴሬሳ ዴቡ ከ 1830 ዎቹ እስከ 1890 ዎቹ በጅማ አባ ጅፋርና የም ንጉሣዊ መንግሥታት መካከል ሲካሄዱ በነበሩ ጦርነቶች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የየም ምርኮኞች ወደ ጅማ በባርነት ተወስደው ለቤተ መንግሥትና ለባላባቶች ተከፋፍለዋል። ነገር ግን ቀስ በቀስ ባሳዩት የሥራ ትጋትና ታማኝነታቸዉ ነፃ ከመውጣትም አልፈው “ አባ ” የሚለዉን የክብር ማዕረግ በማግኘትና የተለያዩ የሥልጣን እርከን በመያዝ እስከ ቤተ መንግሥት አጋፋሪነት ለመድረስ በቅተዋል። በዚህም ምክንያት የአከባቢው የሸነን ጊቤ ኦሮሞዎች የሞችን ሐቀኛና ታማኝ ቦራና ( አንጋፋ ) ይሏቸዋል። የየም የእጅ ባለሙያተኞች መንገድን ጨምሮ በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች በጣም ታዋቂዎች ናቸው። የጅማ ንጉሥ ዳግማዊ አባ ጅፋር (1875-1934) 4 በመጨረሻ የሥልጣን ዘመናቸው ታመው አልጋ ላይ በቀሩ ጊዜ የራሳቸዉ ንጉሣዊ ቤተሰብና ጎሳ ( ድጎ ) እንኳን ሲሰለቿቸው የሞች በደንብ ተንከባክበው ስላስታመሟቸውና ስላገለገሏቸዉ ንጉሡ ለየሞች “ ዘራችሁ ይብዛ፣ ሀብት ንብረቴን ( መሬቴን ጨምሮ ) ውረሱ ” ብለው ምርቃታቸውን ስለለገሷቸው በቤተ መንግሥቱ አካባቢ እስከ አሁን ድረስ በብዛት ሰፍረው ይገኛሉ። ከቤተ መንግሥት አከባቢም በተጨማሪ የሞች በሶኮሩ፣ ጥሮ አፈታ፣ ኦሞ ናዳ፣ ኦሞ ቤየም፣ መንቾ፣ ዴዶ፣ ቀርሳ፣ ሠቃ ጨቆርሳ፣ ሸቤ ሶምቦና ማና ወረዳዎች ውስጥ በተላያዩ ጊዜያት ሰፍረዋል። በዚህም የተነሳ ወደ ሰባ አምስት ከመቶ የሚሆን የየም ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ የሚኖረው በየም ልዩ ወረዳ ሳይሆን በጅማ ዞን ዉስጥ እንደሆነ ይገመታል። የሸነን ጊቤ ኦሮሞና የም ግጭት አፈታት ስልቶቻቸዉ፣ ስማቸዉም ሆነ አተገባበራቸው ተመሳሳይ ነው። ዝቅተኛዉ ሚላ / ሉኮ የሚባል ሲሆን ከሁለት እስከ አምስት በሚሆኑ ቤተሰቦች መካከል የሚከሰቱትን አለመግባባቶች ለመፍታት ያገለግላል። ሸኔ ደግሞ ከአምስት በላይና ከሃምሳ በታች የሆኑ ቤተሰቦችን ጉዳይ መወሰን ይችላል። ሬጂ በትንሹ የሃምሳ ቤተሰቦችን ጉዳይ መበየን ይችላል :: ጦጎ በሬጂ እልባት የላገኙትን ጉዳዮች ተመልክቶ ካልቻለ ወደ ኩሬ ያሳልፋል። ጅጋ / ቱሊ አራት መቶና ከዚያ በላይ የሆኑ አባ ወራዎችን ጉዳይ በበላይነት በመምራት የመጨረሻውን ፍርድ ይሰጣል። በጋብቻ፣ ቋንቋና ሃይማኖት መወራራስ ምክንያት የሞችን ከኦሮሞ መለየት በጣም ያዳግታል። በየሞች የሴቶች ግርዛት ክልክል ነዉ። የየም ወንድ የተገረዘችን ሴት ካገባ አስር ሰንጋዎችን በማረድና በቁመቱ ልክ በሆነ የእሳት ነበልባል ላይ በመዝለል ይቀጣል። ነገር ግን ያገባትን ሴት ለመፍታት አይገደድም። የየም ሴት ከተገረዘች ከየም ውጭ እንጂ ከየም ዉስጥ ባል ለማግኘት ትቸገራለች። ስለዚህ በኦሮሞ ወንዶችና በየም ሴቶች መካከል ሰፋ ያለ የጋብቻ ትስስር ሲተገበር ኖሯል፣ አሁንም ቀጥሏል። ከየም ሕዝብ ውስጥ ሃያ ከመቶው አፋን ኦሮሞ ብቻ የሚናገር ሲሆን ስልሳ ከመቶው የምናኖና አፋን ኦሮሞን ይናገራል። በድንበር አከባቢ የሚገኙ ኦሮሞዎችም የምናኖን ይናገራሉ። በቋንቋዎቹ ውሰጥ ያሉትን የቃላት መመሳሰል ከሚከተለዉ ሰንጠረዥ መረዳት ይቻላል። ቁጥር Afaan Oromo 1. Akkam 2. Ashamaa 3. Ayyaana 4. Gambaala 5. Ittoo 6. Mammaaksa Yamnano Akan Ashamni Ayyana Gamala Eto Mamaka የአማርኛ ትርጉም እንዴት ነው ? ጤና ይስጥልኝ የበዓል ቀን የቤት በር ወጥ ምሳሌያዊ አነጋገር English Translation Hi! How are you doing? Holiday Door Wat(sauce) Proverb 4 ቱሉ ወይም ሞሐመድ ዳኡድ ኢብን ኢብራሂም በመባልም ይታወቃሉ። 7. Mi’iraamaa 8. Nagaa 9. Oduu 10. Qoosaa 11. Qajeeloo 12. Qarsaa 13. Arbii 14. Kamisa 15. Jimaataa 16. Xinnaa 17. Guddaa Mi’era Naga Odu Kosa Kajelo Karsa Arbi Kamisa Jimato Tina Guda በደል / ጭቆና ሰላም ዜና / ወሬ ቀልድ ሰኞ ማክሰኞ ረቡዕ ሐሙስ ዐርብ ቅዳሜ እሑድ injustice Peace News Joke Monday Tuesday Wednesday Thursday Friday Saturday Sunday ከፍቾዎች ከኦሮሞ ጋር ስርወ መንግሥታዊ የጋብቻ ትስስር ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም መሠረት የሊሙ እናሪያ ንጉሣዊ መንግሥት መሥራች የሰጴራ ጎሳ መሪ ቦፎ ( አባ ጎሞል ወይም አባ ሀቡቃ )(1800-1825) እራሳቸዉ የሲጋሮ ጎሳ መሪ ኦዳ አኒዬ ልጅ የነበረችዉን ሞርመለዌን ሲያገቡ አልጋ ወራሻቸው የነበረውን ታላቅ ልጃቸውን ኢብሳን ደግሞ የከፋ ንጉሥ ልጅ ከነበረችው ጌኔ ሚንጂቲ ጋር አጋብተዋል። በኋላም ኢብሳ ( አባ ባግቦ ) በአስተዳደር ዘመናቸው (1825-1861) የከፋ ንጉሥ ካሞ ገኤ ሻሮቾ እኅትን በተጨማሪ አግብተዋል። በሌላ በኩል የጅማ ንጉሥ ዳግማዊ አባ ጅፋር ጌኔ ሚንጂቲን አግብተዋል። ከ 1920 ዎቹ እስከ 1980 ዎቹ ብዙ ቁጥር ያላቸው ከፍቾዎች ጎጀብን ተሻግረው ቡና አምራች ወደሆኑት የሸነን ጊቤ ወረዳዎች ( ጌራ፣ ጎማ፣ ማና፣ ሊሙ ኮሳ፣ ሊሙ ሰቃ እና የመሳሰሉት ) በቡና ለቀማ ወቅቶች ( ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ) በጉልበት ሠራተኝነት ለመሥራት ሰፍረው አብዛኞቹ እዛው ቀርተዋል። ከእነኚህም ብዙዎቹ ወንዶች ስለነበሩ ከሌሎች ብሔሮች፣ ይልቁኑም ከሙስሊም ኦሮሞዎች፣ ጋር ተጋብተው ሙስሊም ሆነዋል። በአፋን ኦሮሞና በከፍናኖ ቋንቋዎች መካከልም የቃላት መመሳሰል የሚንጸባረቅ ሲሆን ለምሳሌ ጌኔ ( ንግሥት ) ፣ ኣቶ ( አተር ) በሀለቱም ቋንቋዎች ተመሳሳይ ናቸው። ከ 1870 ዎቹ እስከ 1920 ዎቹ በሲራራ የንግድ መስመር አማካይነት በዴዶና መንቾ ወረዳዎች በኩል ብዙ የዳውሮና የኮንታ ተወላጆች ጎጀብን ተሻግረው ወደ ሸነን ጊቤ ይመጡ ነበር። ለዚህም ተጨባጭ ማስረጃ በዚያን ጊዜ ተሰይሞ እስከ አሁን ድረስ በዚያው ስያሜ የቆየው የጅማ ከተማ ደቡባዊ መውጫ ( ዳውሮ ) በር ነው። በተጨማሪም በጅማ የነበሩት ባሪያዎች በብዛት ይመጡ የነበሩት ከነዚህ አካባቢዎች ነበር። የባርነት ሥርዓት በአዋጅ ከተሻረ በኋላም ነፃ የወጡት በተለያዩ የጅማ ከተማ ቀበሌዎችና አቅራቢያዎች ሰፍረዋል። በተጨማሪም በባላባቶች ከትውልድ አከባቢያቸው በመገፋት፣ እንዲሁም በሕዝብ ብዛት የትውልድ አካባቢያቸው መሬት በመጣባቡና በመራቆቱ የተነሳ ወደ ጅማና ሊሙ አውራጃዎች በመፍለስ በቤት ሠራተኝነት፣ በግንባታና በቡና ለቀማ ላይ ተሰማርተው በተለይም ከ 1920 ዎቹ በኋላ ትልቅ የሰው ኃይል ለመሆን በቅተዋል። በመቀጠልም ዳዉሮ ኮንታዎች ጅማ ከተማን ጨምሮ በሰፈሩበት ሁሉ ከኦሮሞ ጋር በመቀላቀል የቋንቋቸው ዘይቤና የአነጋገር ቅላፄ በአከባቢው በሚነገሩ በሌሎች ቋንቋዎች፣ በይበልጥም በአፋን ኦሮሞና አማርኛ፣ ላይ ተፅእኖ ሲያሳድር ይስተዋላል። በአጠቃላይ በጊቤ ጎጀብና ዲዴሳ ሦስት ማዕዘን ( ጅማ ዞን ) የሚገኙት የኦሮሞ፣ የም፤ ዳውሮ ኮንታና ከፍቾ ማኅበረሰቦች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሕይወት ዘርፎቻቸው ጥልቅ የሆነ ስብጥርና ትስስር ሲያካሂዱ ኖረዋል። የማኅበረሰቦች የመደጋገፍ እሴቶች በአትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ከማጎልበት አንፃር፤ የባሌ ኦሮሞና ሶማሌ ብሔረሰቦች የመስተጋበርያ ሀገር በቀል ተቋማት ሚና ዶ / ር ከፍያለው ተሰማ ሰሙ በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ሀገር መሆኗን የሚያጎሉ፣ የማኅበረሰቦችን የእርስ በርስ መስተጋብራትን የሚያሳልጡ በርካታ ሀገር በቀል ሥርዓቶች ይገኛሉ። እነዚህም ሥርዓቶች በባህላዊ ተቋማት ይተገበራሉ። ተቋማቱም በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሥርዓቶችና ባህሎች ውስጥ ታቅፈው እስከ አሁን ይገኛሉ። የየባህላዊ ሥርዓቶቹ ተቋማት ደግሞ ተጎራብተው፣ ወሰን ተጋርተውና አብረው የሚኖሩትን ሕዝቦች በሰላም፣ በደስታና በችግር ጊዜያት ለጋራ ጥቅም( Common Good ) እና ለአብሮነት፤ በፈቃደኝነት፣ በውይይትና በመግባባት ላይ በመመሥረት ያስተሳስራሉ። የመረዳዳትን፣ የጉርብትናና የዝምድናን ወግ በመፍጠር እያደርም ልማድና ባህል ሆነው ሲገለገሉባቸው ለዘመናት ኖረዋል። በባህላዊ ሥርዓቶቹ አከዋወን ሂደትም የሁሉም ተሳታፊ ወገኖች ይሁንታና ግንዛቤ የሚያሻ በመሆኑ ተቀባይነት ነበራቸው። ነገር ግን ይህ ሲባል በመካከላቸው ግጭት ተከስቶ አያውቅም ማለት አይደለም። ይልቁንስ ከግጭቶች መበራከት የተነሳ ማኅበረሰቦቹ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች እንዲያንፁ፣ ግጭቶቹን ለመካከላክል የፀጥታ መጠባበቂያ ኅብረቶች( Security alliances ) እንዲያደራጁና ጠንከር ያሉ የካሳና የቅጣት ሕጎች እንዲፈጥሩ ያደርጉ ስለነበረ የማኅበረሰቦቹ መስተጋብር አካል ነበሩ። ሰላማዊ ግንኙንቶችም ሆኑ ግጭቶች የሚመሩት በእነዚሁ የመስተጋብር ተቋማትና ሕጎች ነበር። ለዚህም ይመስላል በባሌ በሚኖሩ የኦሮሞና የሶማሌ ብሔረሰቦች ዘንድ ተመሳሳይነት ያላቸው ( ለምሳሌ እንደ ጋብቻ፣ ጉዲፈቻ፣ ሞጋሳ / ሺግት፣ መገንታ፣ ጉማ / ዲያ ውለተኝነት ) የመሳሰሉ የርስበርስ መስተጋብር ትውፊታዊ ሥርዓቶች በባህላዊ ሕግ ተሠርተው ለረጅም ዘመናት ሲተገበሩ የኖሩት። ጋብቻን እንደማሳያ ብንመለከት በከፊል ቆላማና በቆላማ አውራጃዎች የሚኖሩት የባሌ ኦሮሞና ሶማሌ ጎሳዎች በውስን እርሻና ይበልጡን ደግሞ እንሰሳት በማርባት አስቸጋሪውን የአየር ጠባይና ሥነ ምኅዳር ተቋቁመው በመኖር ሂደት ውስጥ ለረጅም ዘመናት ተዛምደው የሚኖሩበት የመስተጋብር ማኅበራዊ ተቋም ነው ። በዚህም የተነሳ ማኅበረሰቦቹ ( ለምሳሌ እንደ ራይቱ፣ ዳዌ፣ ጉራ፣ ጊሪራና ሰረር በመሳሰሉት የአርሲ ኦሮሞ ጎሳዎች፤ እንዲሁም እንደ ሀዊያ፣ ገሪና ከረንሌህ በመሳሰሉት የሶማሌ ጎሳዎች ) የባህልና የቋንቋ መወራረስ በመጎልበቱ የጋራ ማንነት ያላቸው እስከ መምሰል የደረሰበት ሁኔታ በግልፅ ይታያል። እነዚህን ማኅበረሰቦች በሁለት ክልሎች ከፍሎ ለማስተደደር ይደረግ በነበረ ጥረት ሳቢያ የተከሰቱት ተደጋጋሚ ግጭቶችና መፈናቀሎች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። እስከ ዛሬም እየተከሰተ ነው። የጋብቻ ትስስሩ ለሁለቱም ወገን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ጥቅሞችን ያስገኛል። የሰው ሀብትን ያሳድጋል። በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ወቅትም ሀብትን በመጋራት ጊዜውን እንዲያሳልፉ ያስችላቸዋል። እንዲሁም በእምነት፣ በአርብቶ አደሮች ወጎችና ልማዶች በጋብቻ ትስስራቸው ይደምቁበታል። በመሆኑም ጋብቻ ለሁለቱም ወገኖች ፈርጀ በዙ ጥቅም ያለው የመስተጋብር ተቋም እንደ መሆኑ፤ ሂደቱም በድርድርና በስምምነት የሚሠራና ሽልማትም ቅጣትም የሚያስከትል የተከበረ የመስተጋብር እሴት ነው። መገንታ የሚባለው የመስተጋብር አይነት ደግሞ በባሌ ውስጥ በርካታ የኦሮሞና የሶማሌ ማኅበረሰቦችን የሚያስተሳስር በችግር ወቅት የሚደጋገፉበት ሀገር በቀል ተቋም ነው። ለምሳሌ አንድ የሶማሌ የንዑስ ጎሳ ክፍል ወደ መረጠው የአርሲ ጎሳ መሪዎች ዘንድ በሁለቱም ጎሳዎች ዘንድ የተከበሩ ሽማግሌዎችን በመምረጥ የላኪውን ማንነትና ከልብ የመነጨ የዝምድና ፍላጎት ለመግለፅ “ በሕይወትም በሞትም መገንታ ውሰዱን ” ብሎ ይልካል። ጥያቄው የቀረበለት ጎሳም አድረን እንምከር በማለት አስተናግዶ ቀጠሮ ሰጥቶ ሽማግሌዎቹን ይመልሳል። ጥያቄውም ተመክሮበት ከተፈቀደ የመገንታ ትስስር ሥርዓት ይፈፀምና ሁለቱ የመገንታ ወንድማማቾች በመሆን ይደጋገፈሉ። በተለይም ድርቅና ሰው ሰራሽ ችግር ሲያጋጥም የሶማሌ ጎሳ ክፍሎች ከመላው ቤተሰባቸውና እንስሳዎቻቸው ጋር በመገንታቸው ጎሳ ክልል ውስጥ በመስፈር ለአጭር ጊዜ ወይም ለብዙ ዓመታት መኖር ይችላሉ። በዚህ መሠረት በ 1940 ዎቹ በርካታ የአማዴን ኦጋዴን ጎሳ ንዑስ ጎሳዎች ( ሬሮች ) በዴካ ራይቱ አርሲ ኦሮሞዎች ዘንድ መገንታ ገብተው እስከ አሁን ይኖራሉ። በተመሳሳይ የአጁራን ሶማሌ ንዑስ ክፍሎች በዳዌ ኦሮሞ፣ የከረንሌ ሶማሌ ጎሳዎች በሰረር አርሲ ኦሮሞዎች እንዲሁም የገሪ ሶማሌ ክፍሎች ደሎ በሚኖሩት የከረዩ አርሲ ኦሮሞዎች በመገንታ ባህል በመተሳሰር ይኖራሉ ። ከዚህም በተጨማሪ ሀርማ ሆዳ ( የጡት ልጅነት ) ፣ ገይና ( በሶማሊኛ ውርስ ልጅነት ) እንዲሁም በጉዲፈቻም በርካታ በኦሮሞ፣ በሶማሌና በወንዞች ተፋሰስ ተጠግተው በደለል እርሻ ሥራ በሚተዳደሩ የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የመደጋገፍ ባህላዊ ተቋማት በስፋት መኖራቸው ይታወቃል። በተለይም በቆላማው የባሌ አውራጃዎች ውስጥ ማኅበራዊ መስተጋብር ጥንታዊና የጎለበተ መሆኑንና እስከ አሁንም ያለመቋረጡን ከሚያስረዱት ነባራዊ ምሰክሮች መካከል በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና፣ ትውፍታዊ ሥፍራዎች ይገኙባቸዋል። ለምሳሌ እንደ ድሬ ሼክ ሁሴን ጥንታዊ መስጊድ፣ ከርጁል እና የሶፍኡመር ዋሻ መስጊድ አርዳ ተሬ፣ ኦዳ ሮባ፣ ኦዳ መደ ወላቡ የገዳ ሥርዓት ማዕከላት፤ እንደ ኤልዋቅ፣ ኤልከሬ፣ ኤልሰዌና፣ ኤልቃቸን እና ኤልጎል የመሳሰሉት ተፈጥሯዊ መድሃኒትነት ያላቸው ሆራዎች ( በማዕድናት የበለፀጉ የውሃ ጉርጓዶች ) የአርብቶ አደርነት ባህላዊ ሥርዓቶች የተሰራባቸው ትውፊታዊ ስፍራዎች መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል። ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ሀገር በቀል የማኅበረሰቦች መስተጋብር ተቋማትን በማሳለጥ ረገድ አዎንታዊ ሚና የተጫወቱ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመጥቀስ ያህል፤ ተመሳሳይ የአርብቶ አደርነት አኗኗር ባህል( Pastoralism ) ፣ የእስልምና እምነት፣ ተመሳሳይ ከባባያዊ ሥነ ምህዳርና የቋንቋ መቀራረብ እንዲሁም ከማዕከላዊ መንግሥት አንፃር ተቀራራቢ አቋም ያላቸው መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪም በዚህ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በአባ ገዳዎች ( አባ ቢያዎች ) ፣ በጎሳ መሪዎች፣ ኡጋዞች፣ በኡላማዎችና በየቡርቃዎች ኢማሞች ስር በየባህላቸው የመተዳደር ታሪክ አላቸው። የዳበሩ የሽምግልና ( የሽር ) ሥርዓቶች ስላሉ በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮች ይታዩ ነበር። በመሆኑም በማኅበረሰቦች ዘንድ ተቀባይነት በነበራቸው ሕጎች ( ሴራዎችና ሔራዎች ) መሠረት የመደጋገፍ ባህል ጥበቃ ነበረው። በፀጥታውም ረገድ ከሰፈር አንስቶ እስከ መላው ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ድረስ ኅብረት በመፍጠር ጭቆናን ሲታገሉ ኖረዋል። ለምሳሌም የኩሉብ፣ የጃጋሂር፣ የዶምቡርና የሶውራ ንቅናቄዎችን መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ ንቅናቄዎች ወቅት ለረጅም ዘመናት በአካባቢው ማኅበረሰቦች ዳብሮ የቆየው የመደጋገፍ ባህል በኦሮሞ፣ በሶማሌ፣ በሲዳማዎችና በወንዞች ሸለቆዎች ውስጥ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል መተማመንና ኅብረት ለመፍጠር ረድቷል። በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት የመደጋገፍና የመስተጋብር አሳላጭ ተቋማት ማኅበረሰቡ በሚያምንባቸው ተዋናዮችና አሳታፊ በሆኑ መድረኮች የሚተገበሩ በመሆኑ ተቀባይነት ነበራቸው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅትም በአገራችን እንደ አንድ የጋራ ማኅበረሰብ የሚያጋጥሙ ጉዳዮችና ችግሮች ከሕዝቡ በመነጩ ተቋማትና ሥርዓቶች፣ ከሕዝቡ በሚወጡና በታመነባቸው ተዋናዮች ጥቅምና ጉዳቱ በራሱ በማኅበረሰቡ ዕውቅና ከተቸራቸው በመወየያት ሀገራዊ መግባባት የመፍጠር ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ሲጠቃለልም ከባሌ የኦሮሞና የሶማሌ አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ታሪክ የምንማረው ቅቡልነት ያለው እሴት፣ ተቋምና ግልፅ የሆነ ሂደት መግባባት እና ዘላቂነት የሚኖረው መሆኑን ነው። ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብር በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ዶ / ር ረታ ዱጉማ በዚህ ጥናት ዉስጥ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሕዝብ በዋናናነት የሚያጠቃልለው ሐረሪን፤ ኦሮሞን፤ ሶማሊን፤ አርጎባንና አፋርን ሲሆን፤ በተጨማሪም ከ 19 ኛዉ መቶ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች መጥተው የሚኖሩትንም ያካትታል። እንደሚታወቀው የሐረርን ከተማ ከበዋት የሚኖሩት የኖሌ፣ ጃርሶ፣አላ፣ ኦቦራ፣ ኢቱና አኒያ ኦሮሞ ጎሳዎች ሲሆኑ፤ በስተምሥራቅ የሐረር ኮረብታማ ስፍራዎች የሚኖሩ የጊሪ፣ የሃበር አወል፣ የባርትራ፣ የቡርሱብ ሱማሊ ጎሳዎች ከከተማዉ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው። 1. የንግድ ትስስር ሐረርና አከባቢዋ ለብዙ ዘመናት ኢትዮጵያ የንግድ ቁሳቁሶችን ወደ ዉጭና ወደ አገር ዉስጥ የምታስገባበትና የምታስወጣበት፤ ብዙ የንግድ መስመሮች የሚያልፉባት ስፍራ ነበረች። ሪቻርድ ፓንክረስት በግንብ የታጠረችዉ ሐረር “… ብዙ የንግድ መስመሮች የሚገናኙበት የአፍሪካ ቀንድ ማዕከል ነበረች ” ብሎ ገልጿታል። አብዛኛው የደቡብ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የንግድ ቁሳቁሶች ወደ ውጭ የሚላኩት በዘይላና በርበራ ወደቦች ነበር። ዘይላና በርበራ ወደቦች ከሐረር፣ ከሸዋ፣ ከአርሲ፣ ከጉራጌ፣ ከባሌ፣ ሃዲያ፣ ከመሃል አገርና እስከ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጊቤ ድረስ እንዲሁም ከዐረቢያ ወደቦችና ከምዕራብ ህንድ ጋር የንግድ ትስስር ነበሯቸው። በ 19 ኛው መቶ ዓመት የጂቡቲና የታጁራ ወደቦች መቋቋም ለአከባቢው የንግድ መስተጋብር መጠንከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከ 16 ኛዉ መቶ ዓመት ጀምሮ ሐረሪዎችና ኦሮሞዎች ሰላማዊ የንግድ ትስስርን ፈጥረዋል። በተለይም ኦሮሞዎች ከሐረር ከተማ የጥጥ ልብስ፣ ጨው፣ የብረት መገልገያ መሳሪያዎችና ሉሎችንም ዕቃዎች ከሐረሪ ነጋዴዎች ይገዙ ነበር። ሐረሪዎች ደግሞ ኦሮሞዎች የሚያቀርቡትን የእህል ምርትና የእንስሳት ውጤት ለንግድ ሥራቸው ይፈልጉታል። ይህ ሁኔታ በሐረሪና ኦሮሞ መካካል የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር ትልቅ በር ከፍቷል። በ 19 ኛዉ መቶ ዓመት ሐረር ዙርያ ያለው ኦሮሞ ለሐረር ገበያ የሚያቀርበው የነጠረ ቅቤ፣ ወተት፣ ቡና፣ ትምባሆ፣ ሱፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ አጃ፣ ምሥርና የቁም ከብት የመሳሳሉትን ሲሆን የሶማሊ ጎሳዎች ደግሞ የቁም ከብቶች፣ ቆዳና ሌጦ፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ሙጫ፣ የነጠረ ቅቤና የሰጎን ላባ ሐረር ገበያ በማምጣት ይሸጡ ነበር። የአርጎባ ማኅበረሰብም የእርሻ ምርቶችና የዕደ ጥበብ ልብስ ለገበያ ያቀርቡ ነበር። በ 1880 ዎቹ፤ ከሐረር ከተማ ውጭ የሚገኙ እንደ ጃልዴሳ፣ ወረቢሌ፣ ቦባሳ፣ ጎሮ ጉቱ፣ ገፍራ ቀላ፣ ፉኛን ቢራ ያሉ የገበያ ማዕከሎች የሐረሪ ነጋዴዎች ዕቃዎችን ከኦሮሞና ከሶማሊ የሚገዙበትና ከውጭ የሚመጡትን ጨርቃጨርቅ፣ መዳብ፣ ዚንክ፣ የሐር ክር፣ አጃ፤ ስኳር፣ ብርጭቆ፣ ሩዝ ለአገሬው ሕዝብ የሚሸጡበት ሥፍራ ነበሩ። ከባሕር ጠረፍ ከሚነሱት ሁለት የንግድ መስመሮች አንደኛዉ ከዘይላ ወደብ ተነስቶ በኢሳ ሶማሊ አካባቢ አልፎ በጃልዴሳና ኖሌ ኦሮሞ አድርጎ ወደ ሐረር ከተማ የሚገባ ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ደግሞ ከበርበራ ወደብ ተነስቶ በደርሚ መስመር አድርጎ የገደቡርሲን አገር አቋርጦ የሚሄደው መስመር በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል። የኢሳ እና የገደቡርሲ ጎሳዎች በአባን የሚመራ ቡድን አደራጅተዉ የሐረሪና የሌሎች ነጋዴዎችን ደህንነት በመጠበቅ በባህር ጠረፍ እና በተራራማው ክፍል መካከል በግመል በማጓጓዝ ከዚህ አገልግሎት ጥቅም ያገኙ ነበር። የጃርሶ እና የኖሌ ኦሮሞዎች ዕቃዎቹን ከሶማሊዎቹ ጃልዴሳ ላይ ተቀብለዋቸዉ እስከ ሐረር ከተማና መሃል አገር ድረስ ያጓጉዛሉ። ይህም በብዙ ሕዝቦች መካከል ጠንካራ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር ረድቷል። ከ 1830 ዎቹ በኋላ ሐረሪዎች በታጁራ ሸዋ የንግድ መስመር አድርገው የአልዩ አምባ ገበያን ይጠቀሙ ነበር። በአልዩ አምባ ገበያ የሚጠቀሙት አማራ፣ ኦሮሞ፣ ይፋት ( አርጎባ ) ፣ ሐረሪ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ጉራጌ፣ ከፋ እና የእናሪያ ሕዝብ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ዕቃዎችን ለገበያ በማቅረብ ይገበያዩ ነበር። በአልዩ አምባ ገበያ ከሚገበያዩት ነጋዴዎች አንድ አራተኛ የሚሆኑት ሐረሪና አፋሮች ነበሩ። በተለይም በሐረር እና ሸዋ መሪዎች መካከል ስለንግድ መስመር ደህንነት መረጃ ይለዋወጡ ነበር። የሸዋ ነገሥታት አልዩ አምባ ለሰፈሩት የሐረሪ ንግድ ማኅበረሰብ አባላት ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። እንደዚሁም ሐረር ከተማ ለሰፈሩት ከአማራና ከሸዋ ለመጡ ለ 3000 ያህል ነጋዴዎች የሐረሪ አሚሮች ጥበቃ ያደርጉላቸው ነበር። . እኤአ በ 1902 የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ድሬ ዳዋ መድረስ፣ እንዲሁም ከጣሊያን ወረራ በኋላ የተሻለ የትራንፖርት መንገድ መኖርና የከተሞች መስፋፋት፣ በተጨማሪም አካባቢው ብዙ የአገር ውስጥ ምርትና በፋብሪካ የተመረቱ የዉጭ አገር ሸቀጦች የሚጓጓዙበት መስመር መሆኑ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል። በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ጠንካራ የንግድ መስተጋብር መኖሩ ነጋዴዎችን፣ ደንበኞችን፣ ደላላዎችንና አጓጓዦችን ያስተሳሳረ ብቻም ሳይሆን ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲጓዙና አዲስ አካባቢን እንዲያውቁ፣ አዲስ ሐሳብን እንዲቀስሙ፣ አንዱ ሕዝብ ከሌላዉ ጋር እንዲቀላቀልና የሌላውን ባህል፣ እምነትና ቋንቋ እንዲያውቅ፤ በአጠቃላይም መግባባት በመፍጠር በጉርብትናና በጋብቻ በመጣመር በመካከላቸው ጠንካራ ቁርኝት እንዲኖር አድርጓል። 2. አገር በቀል ተቋማትና ማኅበራዊ መስተጋብር 2.1. የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት፣ ጉዲፈቻና ሞጋሳ የኦሮሞ ኅብረተሰብ ማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳው ሥርዓት ዘርግቷል። ከጎረቤት ወይም ውስጡ ከሚኖረዉ ሕዝብ ጋር በሞጋሳና ጉዲፈቻ የራሱ አካል አድርጎ አብሮ ይኖራል። በዚሁም መሠረት ሐረርጌ ውስጥ ብዙ የጊሪና ሃዊያ ሶማሊ ጎሳዎች በጃርሶ እና ባቢሌ ኦሮሞ ጎሳዎች በመታቀፍ አብረው ይኖራሉ። የአኒያ ኦሮሞ አማርካ፣ ጫማ፣ ወረ ፉታ፣ አገይ እና አደ የሚባሉ የሱማሊ ጎሳዎችን ጨፌ ትርትራና ወልዲያ የሚባሉ ሥፍራ መኖሪያ ቦታ ሰጥተዋቸዉ አብረው ኖረዋል። በተጨማሪም የኖሌ ኦሮሞ የጉርጉራ ሶማሊ ጎሳን፤ የሐረሪ ጎሳዎች እንደነ ወረ አቦኞ፣ ሳምቴ፣ ይማጅ፣ አምበር፣ወረ አሊ ያሉትን ጎሳዎች በማቀፍ የራሱ አካል አድርጎ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ትስስር በመፍጠር አብረው ለዘመናት ኖረዋል። እንደዚሁም በሐረርጌ የሚኖሩ አማራና ሌሎች ሕዝቦች በያሉበት ሥፍራ የተለያዩ የኦሮሞ ጎሳዎች አባል በመሆን ከኦሮሞ ጋር በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዉስጥ በመሳተፍ ለብዙ ዘመን አብረው ኖረዋል። 2.2. የሐረሪ ጌይ ለመደ የሐረሪ ሕዝብም እንደሌላዉ የአቃፊነት ልምድ ያለው ሲሆን ጌይ ለመደ ማለት የሐረሪን የከተማ አኗኗር ዘይቤ የለመደ፣ የሐረሪ ቋንቋን ( ጌይ ሲናን ) ያወቀ፣ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነ፣ የሐረሪን ባህልና ወግ ( ጌይ አዳ ) የሚያውቅና በሐረሪ ማኅበራዊ አፎቻ ዉስጥ የሚሳተፍ፣ በአጭሩ የሐረሪ ሕዝብ አካል የሆነ ማለት ነው። ሲድኒ ዋልድሮን በ 1960 ዎቹ ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ ሐረር ከተማ የሚኖሩ ብዙ ኦሮሞና ሱማሊ የከተማን የአኗኗር ዘይቤ፣ የሐረሪን ባህል፣ ወግና ቋንቋ በመማር በአፎቻ ማኅበር ውስጥ በመሳተፍ ከሐረሪ ሕዝብ ጋር አብረው ይኖሩ እንደነበር አመልክቷል። በጀጎል ግንብ ውስጥ ብዙ አማሮች ከ 1948 ጀምሮ፣ በተለይም ከ 1965 ዓ . ም . በኋላ፣ በብዛት መኖር ሲጀምሩ ሐረሪና አማራ የአንድ አፎሻ አባል በመሆን በበዓላት ቀን፣ በሠርግም በሀዘንም ጊዜ አብረው ያሳልፉ ነበር። 2.3. የሱማሊ ሰድቆ ማኅበር እንደሌላዉ የአካባቢው ሕዝብ የሱማሊ ሕዝብ በሰድቆ ተቋም አማካኝነት የአቃፊነት ባህል አለው። ብዙ የአክቹ ኦሮሞ ንዑስ ጎሳዎች በጅጅጋ፣ በኦጋዴንና በሶማሊላንድ ( ቦሮማና ሃርገይሳ ) ከሚገኘዉ የሶማሊ ሕዝብ ጋር ሲኖር፤ በዳሮድ ወይም በድር ጎሳ በመታቀፍ የደም ካሳ ከፋይ አባል ሆኖ አብረዋቸው ይኖሩ ነበር። ሱማሊ መገን በሚባለዉ ሥርዓት መሠረት ሶማሊ ዉስጥ ለሚኖር ለየትኛዉም አናሳ ሕዝብ ጥላ ከላላ ሆነዉ ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። ሶማሊ ዉስጥ የሚኖሩትም አማራዎች የሱማሊ ሳድቆ ማኅበር አባል በመሆን ከሶማሊ ሕዝብ ጋር መልካም ጉርብትና መሥርተዋል። የሳድቆ ማኅበር አባል የሆኑ የአማራ ተወላጆች ከተቆራኙት ጎሳ መሬት ይሰጣቸዋል። አማራውም ከብቱን እንዲጠብቁለት ኃላፊነቱን ለሶማሊ ጎሳ ይሰጣል። አማራም ሱማሊ ወደ ከተማ ለሕክምና፣ ለንግድና የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ ማረፊያ ቦታ በመስጠት ጥሩ መስተንግዶ ያደርግለታል። በመገን ሥርዓት የሱማሊ ጎሳ ለአማራው ጥበቃ ያደርግለታል፤ አማራዉም የጎሳዉ የደም ከፋይ አባል በመሆን በማኅበራዊ ጉዳዮች ዉስጥ አብሯቸዉ ይሳተፋል። 3. የሙስሊምና ክርስቲያን መስተጋብር በቅዱሳን አድባራት ሥፍራዎች 3.1. የሙስሊሙ ቅዱሳን አድባራት ዚያራ። በሐረር ጀጎል ግንብ ውስጥና ዙርያው ከ 200 በላይ የሚሆኑ የሙስሊም አድባራት የሚገኙ ሲሆን፤ ከነዚህም መከካል አው አባድር፤ አው ሶፊ፤ አው ዚን፤አው ንጉሥ ወዘተ ይገኛሉ። ዋልድሮን እንደተመለከተዉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሐረሪ፣ ኦሮሞ፣ አርጎባ፣ ሶማሊ እንዲሁም አፋርንም ጨምሮ በነዚህ ቅዱሳን ስፍራ ፈጣሪያቸዉን ያመሰግናሉ፣ ያወድሳሉ፣ እንደዚሁም ጤናና ሰላም እንዲሰጣቸዉ ይለምናሉ። ወደ እነዚህ ሥፍራዎች የሚደረገዉ ጉዞ ዚያራ ሲባል እነዚህ የቅዱሳን ሥፍራዎች ክርስቲያኑም ጭምር ፈውስን ለማግኘት የሚታደምበትና ለየትኛዉም የእምነት ተከታይ ክፍት የሆነ ሥፍራ ነዉ። . 3.2. የቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል። ከ 1941 ዓ . ም . በኋላ ብዙ የአከባቢው የሙስሊም ኅብረተሰብ አባላት ዓመታዊ በዓሉን ይታደሙ ነበር። በ 1953 ዓ . ም . አቡነ ቴዎፍሎስ የሐረር ጠቅላይ ግዛት ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የአፄ ኃይለ ሥላሴና ቤተሰቡ፣ መሳፍንት፣ መኳንንትና ሹማምንት በበዓሉ ላይ መታደም ብዙ ሕዝብ በዓሉን እንዲያከብር አድርጎታል።በታኅሣሥ ወር 1966 ዓ . ም . ብዙ ሙስሊምና ክርስቲያን ከድሬ ዳዋ፣ ሐረር፣ ጋራሙለታ፣ ጨርጨር እና ኦቦራ አውራጃዎች በጠዋት ወደ ቁልቢ ገብርኤል በመሄድ ያከብሩ ነበር። ፓውል ሄንዘ በ 1971 ከታዳሚዎቹ መካከል አንድ ሶስተኛው የአካባቢው ሙስሊም ማኅብረሰብ መሆኑን ይገልጻል። በበዓሉ ዋዜማ ላይ ኦሮሞ፣ ሐረሪና ሶማሊ ሸማ ለብሰዉ በመገኘት ከክርስቲያኑ ጋር አብሮነታቸዉን በማሳየት እንደተካፈሉ ይናገራል። ሙስሊሙም እንደ ክርስቲያኑ የጤና፣ የመውለድ፣ የኢኮኖሚ ወዘተ ችግር ያለባቸው ስለት ተስለው ሲፈጻምላቸዉ የተለያዩ ስጦታ ለቅዱስ ገብርኤል በተክርስቲያን ያስገቡ ነበር። በመውሊድ፣ በረመዳን ጾም፣ በጥምቀትና በፋሲካ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ፍራፍሬ፣ እንቁላል፣ ሙዝ፣ ወተት፣ ስኳር፣ ዘይት ወዘተ በማምጣት በዓሉን አብረው ያከብራሉ። በተጨማሪም በበዓላቸው ጊዜ አንዱ ለሌላዉ የእርድ ከብት ወጭን በመሸፈን ደስታቸውን ይካፈላሉ። በጥምቀት በዓል ታቦቱ ጫፌ ተብሎ በሚጠራበት ቦታ በሚቆይበት ጊዜ ክርስቲያንና ሙስሊም ጎረቤቶች፣ አብሮ አደግ ልጆቻቸው ጭምር፣ ጫፌ ቡሊ ( የጨፌ አዳር ) ብለው አብረው ያከብሩ ነበር። 4. አፎሻ ማህበር በ 1975 ዓ . ም . የደርግ መንግሥት ሙስሊሙና ክርስቲያኑን በከተማም በገጠርም በአንድ የአፎሻ ማህበር ሥር እንዲታቀፉ በማድረግ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሰዎች ውስጥ አብረው እንዲሳተፉና እንዲተጋገዙ አድርጓቸዋል። በአጨዳ ጊዜ ጉዛ ወይንም ደቦ ሲጠራ ገጠር የሚኖሩ አማራና ኦሮሞ አብረው እህል በማጨድ ይሰበስባሉ። በዚህን ወቅት ኦሮሞም አማራዉም ባህላዊ ምግባቸዉን በማቅረብ አብረው ይመገባሉ። 5. የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ኅብረተሰብ መፈጠር። በምሥራቅ ኢትዮጵያ ጠንካራ የንግድና ማኅበራዊ መስተጋብር መኖር በንግዱ የሚሳተፉት ሐረሪ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሊ፣ አማራ፣ ጉራጌና ሌሎችም አንዱ የሌላውን ቋንቋ በተወሰነ ደረጃ እንዲናገሩ አስችሏቸዋል። በድሬ ዳዋ፣ በሐረርና ሌሎች ከተሞች የተለያዩ ብሔር፣ ቋንቋና ባህል ያላቸው ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች መኖር የአካባቢውን ሰው የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሆም ረድቶታል። . ድሬ ዳዋ ከተማ ውስጥ ብዙ ሰዎች ከአገራቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛና ጣልያንኛ ይናገራሉ። ድሬ ዳዋ አምስተኛ ሰፈር የሚኖር ሰው ሐረሪኛ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛና ሶማሊኛን መናገር ይችላል። ከሱማሊ ጋር የሚነግዱ ነጋዴዎች የሶማሊኛ ቋንቋ መናገር ይችላሉ። በደርግ ዘመን ብዙ ኦሮሞ፣ አማራና ጉራጌ በጀጎል ግንብ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌ ቤቶች ሲኖሩ የነበሩ አብዛኞቹ ሐረሪኛ ቋንቋን መናገር ችለዋል። በደርግ ዘመን በአንጻሩ ብዙ ኦሮሞ የትምህርት ዕድል በማግኘት አማርኛን መናገር ሲችሉ አማራም ከኦሮሞ ጋር በተለያዩ ማኅበራት ውስጥ አብሮ በመሳተፍ የበለጠ ኦሮምኛን እንዲናገሩ አስችሏቸዋል። ስለዚህ ብዙ ቋንቋ የሚናገር ኅብረተሰብ መፈጠሩ ማኅበራዊ ትስስሩ እንዲጠናከር፣ መቻቻል እንዲኖር፣ ቤተሰባዊ ቅርርብና መተባባር እንዲኖር፤ አንዱ የሌላውን ባህል፣ ወግና ልማድ በትክክል እንዲያውቅና የአኗኗር ዘይቤን አንዱ ከሌላው እንዲማር አስችሏቸዋል። ይህም የአብሮነት መንፈስን የበለጠ እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። 6. የሐረር ልጅ እንደ አዲስ ማንነት መፈጠር። በሐረርጌ ተወልደው ያደጉ የትኛዉም ብሔር አባላት አንድ የሚታወቁበት ማንነት አላቸው። የሐረርጌ ተወላጅ ብዙ ቋንቋ የሚችል፣ ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ እምነት፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሀብታምና ደሃ ሳይል ከሁሉም ጋር ተቀላቅሎ በቀላሉ የመግባባት ባህል ያለው ነው። ሁለተኛው ባሕሪ ለሰው የሚሰጡት ፍቅርና እንግዳን የመቀበል ልማዱ ነው። የሐረር ልጅ ሌላወ መገለጫው ከግለኝነት ሕይወት ይልቅ አብሮነትን የሚፈልግ፤ የስግብግብነት ባህሪ የሌለበት፤ አብሮ ተካፍሎ መብላት፣ አብሮ መቃም፣ መጫወት፣ በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽ የመወያየት ልማድ ያለው ነዉ። የሐረር ልጅ ሌላው ባህሪው ጨዋታ አዋቂ፣ አብዝቶ አለመጨናነቅና ዘና የማለት ባህሪ ያለው፣ ለመቅረብ የማይከብድና ዝምተኛውን ሰው እንኳን በማቅረብ ነፃነት እንዲሰማው በማድረግ ጨዋታውን እንዲቀላቀል የሚያደርግ ነው። ለዚህም ይመስላል ብዙ የኢትዮጵያ ድምፃውያን በቆይታቸዉ ጊዜ ያዩትን በአጠቃላይ ስለ ሐረር ሕዝብ በተለይም ስለ ድሬ ዳዋ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነት፣ ለሰው ያላቸውን ፍቅር፣ የመቻቻል፣ የአብሮነትና የመተጋገዝ ባህል በዘፈን የሚያወድሱት። የቃል መረጃ የሰጡኝ አዋቂ አባቶች እንደነገሩኝ፤ በድኅረ -1983 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ድባብ ሕዝቡ ካዳበረው የአብሮነት መልካም እሴቶች በተቃራኒ ልዩነቶችን በማጉላት፤ አንዱ በሌላ ክልል ውስጥ መብቱ የተገደበ እንደሆነ፤ በማንኛዉም ነገር መሳተፍ እንደማይችልና የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማው አድርጓል። የድምበር ግጭቶችን በመቀስቀስ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት የጠላትነት ስሜት በሕዝቦች መካካል አስፋፍቷል። የሕዝቦችን የገቢ ምንጭንም በማዳከም አብረው እንዳይካፈሉና እንዳይረዳዱ አድርጓቸዋል። ሰው ሠራሽ ኢኮኖሚያዊ እጥረትን በመፍጠር ስግብግብነት እንዲሰፍንና በሕዝቦች መካካል ለዘመናት የነበረው የአብሮነት ማኅበራዊ ሕይወቱ እንዲዳከም ተሠርቷል። ይህም ሆኖ የሕዝቡን የአብሮነት እሴቶች ሥረ መሠረት ሙሉ በሙሉ መናድ አልቻለም ይላሉ። ስለዚህ መንግሥትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሕዝቡ ለዘመናት ያዳበረውን የአብሮነት እሴት ከግንዛቤ በማስገባት አገር ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የውጭ አገራትን ልምድ ብቻ ሳይሆን ሕዝባችን ዘንድ ያለውንም ትልቅ አቅም በአግባቡ በማጤንና በመረዳት ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይገባል። በዘመናት መካከል የሚለዋወጥ የሕዝቦች ግንኙነትና ማኅበራዊ መስተጋብር በምሥራቅ ወለጋ ዶ / ር ዘላለም ተፈራ መግቢያ የዚህ ጥናት ትኩረት በዘመናት መካከል ሲነሱና ሲወድቁ፣ ሲጠብቁና ሲላሉ፣ እንዲሁም ሲሞቁና ሲቀዘቅዙ በነበሩ የሕዝቦች ማኅበረ ባህላዊ ግንኙነቶችና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ላይ ነው። ምርምሩ የተካሄደዉ በዐባይና በአንገር ወንዞች መካከል በሚገኙ ሁለት የቀድሞው የሆሮ ጉድሩ አውራጃ አካል በነበሩና አሁን በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሥር በተጠቃለሉ ጊዳ አያናና ኪረሙ በሚባሉ ወረዳዎች ነው። ምርምሩ በእነኚህ ሁለት ወረዳዎች ይወሰን እንጂ ታሪካዊ ዳራው ሰፊውን የቀድሞ ሆሮ ጉድሩ አዉራጃን ያጠቃልላል። ጥናቱ የረጅም ጊዜ የመስክ ቆይታ የጠየቀ Longitudinal Research የሚሰኝ ሲሆን በይነ ዲስፕሊናዊ ( interdisciplinary ) የመረጃ ማሰባሰብ ሥነ ዘዴን የተከተለ ነው :: የጥናቱ ግኝቶች ጥናቱ ካሳያቸው ኩነቶች መካከል የመጀመሪያው ዛሬ ምሥራቅ ወለጋ በመባል በሚታወቀው የአገራችን ክፍል፣ በተለይም በሆሮ ጉድሩ፣ የተፈጠሩ ታሪካዊ ትስስሮችና ማኅበራዊ መስተጋብሮች መነሻቸው የሕዝቦች ፍልሰትና ሰፈራዎች መሆኑን ነው። አከባቢው ለረጅም ዘመናት ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ መስተጋብርን ያስተናገደ ሲሆን፤ የተለያየ ቋንቋ፣ እምነት፣ ወግና ልማድ እንዲሁም በእነኚህ ዘውጎች ዙሪያ የተገነቡ የተለያየ ማንነት ያሏቸው ሕዝቦች የተገናኙበትና አብሮ የኖሩበት፣ የባህል፣ የቋንቋ፤ የሃይማኖትና የኑሮ ዘይቤዎችን የተጋሩበት፣ የተማማሩበትና በደምና በጋብቻ የተሳሰሩበት መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል። እንደዚያም ሆኖ በቀደምት የአከባቢ ነዋሪዎች፣ ማለትም የኦሞአዊና የናይሎ ሰሐራዊ የቋንቋ ቤተሰብ ተናጋሪ በሆኑ በተለይም በሽናሻና በጉሙዝ ሕዝቦችና፣ እንዲሁም ከ 17 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አከባቢውን በተቆጣጠሩ የኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የነበረው መስተጋብርና ከ 19 ኛዉ ክፍለ ዘመን የመጨረሻዎቹ ዐሠርት ዓመታት ጀምሮ እስከ ዘውዳዊ ሥርዓት ማብቂያ (1966 ዓ . ም .) ድረስ የአከባቢው ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር መዘውር ለመሆን በበቃው የአማራ ሕዝብ መካከል የነበረው ግንኙነት የየቅል መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል። የኦሮሞና የቀደምት ነዋሪዎች ግንኙነት የኦሮሞና የቀደምት ነዋሪዎች ግንኙነትን በተመለከተ ጥናቱ ያሳየው ነገር ቢኖር፤ በመጀመሪያ ግንኙነት ወቅት የተደረጉ ውጊያዎችና ወረራዎች ካስከተሏቸው ጉዳቶችና ቁርሾዎች በስተቀር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጥሩ የሚባል ማኅበረ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ይታይባቸዋል። ሆኖም ግን በኦሮሞና በጉሙዝ እንዲሁም በኦሮሞና በሽናሻ መካከል የተደረጉ ማኅበረ ባህላዊ መስተጋብሮች የተለያዩ እነደነበሩ ጥናቱ አሳይቷል፤ ግንኙነቶቹም ባመዛኙ የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረጉ ይመስላሉ። በኦሮሞና በጉሙዝ መካከል የተፈጠረው ግንኙነት ሁለት መልክ ነበረው። በአንድ በኩል በመጀመሪያዎቹ የኦሮሞ ዘመቻዎች ወቅት የተማረኩ ጉሙዞች በማኅበራዊ ደረጃቸው ወደ ባርነት ዝቅ ብለው የአገልጋይነት ደረጃ የተሰጣቸዉ ሲሆን፤ በዘር ሐረግ መቁጠሪያ ግን የማረኳቸውንና የሚያስተዳድሯቸውን ኦሮሞዎች የዘር ግንድ እንደ መጠሪያነት እንዲጠቀሙ ተደርጓል። የጋብቻ ሥርዓታቸውም የእርስ በርሰ እንጂ ከቦረና ( ንፁህ ) ኦሮሞ ጋር እንዳይሆን ተደርጓል። አብዛኛዎቹ ጉሙዞች ግን ፊት ለፊት ከመፋለም ይልቅ ራቅ ወዳሉ ቆላማ ሥፍራዎች በመሸሽ ከኦሮሞዎች ጋር የሚደረገውን አካላዊም ሆነ ባህላዊ መስተጋብር በአመዛኙ ቀንሰዋል። ይህ ባንድ በኩል ማንነታቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ሲረዳ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ መሬታቸውን እንዲያጡ እንዳደረጋችው በመስክ ጉብኝት ጊዜ የጠየቅኳቸው የብሔሩ ተወላጆች ነግረውኛል። በሂደት ግን ሚቹ ( Michu) በሚባል የኦሮሞ ባህላዊ የወዳጅነት መመሥረቻ ሥርዓት አማካይነት የሁለቱ ማኅበረሰቦች መስተጋብር መሻሻል አሳይቶ በሰላም አብረው ለመኖር በቅተዋል። በኦሮሞና በሽናሻ ሕዝቦች መካከል የተደረገው ማኅበረ ባህላዊ ግንኙነት ግን ትንሽ ለየት ያለ ሲሆን፤ “ ሉባ ባሳ ” በሚባል ኦሮሞ ያልሆኑ ማኅበረሰቦችን የማካተት የኦሮሞ ባህላዊ የሆነ ሥርዓት የተቃኘ ነው። ይሄውም በመጀመሪያዎቹ የኦሮሞ ዘመቻዎች ወቅት የተማረኩ ሽናሻዎች የሉባ ባሳ ከበራዎችን ( Luba bassa rituals ) በመፈፀም ስንቾ የሚባል የጎሳ ስም ተሰጥቷቸው ሙሉ በሙሉ ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር የተቀላቀሉበት ሥርዓት ነው። ከሉባ ባሳ ሥርዓት በኋላ ስንቾዎች ከጉሙዞች በተለየ መልኩ ከማንኛውም የኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር ጋብቻ የመፈፀም ዕድል የተሰጣቸው ሲሆን እኩል የመሬት ይዞታ መብትም ተጎናጽፈዋል። በመሆኑም ዛሬ በአኗኗር፣ በቋንቋና በለሎችም የባህል ዘውጎች ስንቾዎች ከኦሮሞ ጋር በጥብቅ የተቆራኙና የአንድነትና የበጎ ማኅበራዊ ውህደት ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዳሉ። የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች ግንኙነት በጥናቱ እንደታየው በአከባቢው ከተፈጠሩት የሕዝቦች ግንኙነቶች ውስጥ በጣም ውስብስብና ተለዋዋጭ የነበረው የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ግንኙነት ነው። የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት ግንኙነቶቹ የተፈጠሩት ከ 16 ኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻዎቹ ዐሠርት ዓመታት ጀምሮ ሲሆን በጣም ተለዋዋጭም ነበሩ። የመጀመሪያዎቹ ግንኙነቶች አካባቢን ለመቆጣጠር ከተደረጉ ወረራዎችና የመልስ ወረራዎች ( raids and counter raids ) የተነሳ ፍጹም በግጭት የተሞሉ ነበሩ። የመጫ ኦሮሞ ጎሳዎች የሆኑት ዐሥራ አራቱ የሆሮ ልጆች ( ኩዳ አርፋን ሆሮ ) ፤ ሰባቱ የጉድሩ ልጆች ( ቶርባን ጉድሩ ) እና አራቱ የጂማ ልጆች ( አርፋን ጂማ ) በመባል በታሪክ የሚታወቁ የጎሳ መሪዎች ሆሮ ጉድሩ ይባል የነበረውን አካባቢ በምሥራቅ በኩል ከላይኛው የጊቤ ወንዝ ተፋሰስና ከጮመን ረግረጋማ አከባቢዎች ጀምሮ በስተምሥራቅ በኩል ደግሞ በአንገርና በዐባይ ወንዞች መካከል የሚገኙ የዛሬዎቹን ጊዳ፣ ኪረሙ፣ ሊሙና ኢባንቱ ወረዳዎችን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል። በተለይም ታላቁ የምዕራብ ኢትዮጵያ የሲራራ ንግድ ማዕከል ከነበረው ከጎጃሙ የባሶ ገበያ ተነስተዉ ሆሮ ጉድሩን አቋርጠው ወደ ጊቤ አከባቢዎች የሚዘልቁ የንግድ መሥመሮች መጠናከር ጋር ተያይዞ የሁለቱ ማኅበረሰብ ግንኙነቶች በንግድ ላይ የተመሠረተ መልካም ጉርብትና የታየበት ሆኗል። ይህ የሚያሳየው ሁለቱ ሕዝቦች ከግጭት ይልቅ በንግድ ትስስርና ትብብር የበለጠ መጠቀም እንደሚችሉ ነው። ከጥቅም አንፃር የሆሮና የጉድሩ ኦሮሞዎች ከንግድ ኬላዎች ከሚገኙ የቀረጥ ገቢዎች በሰፊው ይጠቀሙ እንደነበር አካባቢውን በ 1840 ዎቹና በ 1850 ዎቹ የጎበኙ የአውሮፓ ተጓዦች፣ እነ ፕላውደን ( Plowden ) ፤ ማሳያ ( Massaja ) እና ዳባዲ ( d’Abbadie ) ፣ በሰፊው የመሰከሩ ሲሆን፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ሲራራ ነጋዴዎችም ከዚህ ንግድ በእጅጉ ተጠቃሚ እንደነበሩ ድርሳናቱ በሰፊው ያትታሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ በንግድ ላይ የተመሠረተ የሕዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና መልካም ጉርብትና ተመልሶ መበላሸት የጀመረው እ . ኤ . አ . ከ 1872 ጀምሮ ነው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው የጎጃም ኃይሎች በጉድሩ ኦሮሞ መሪዎች የእርስ በርስ ፀብና ሽኩቻ ውስጥ አንዱን ወግነው ጣልቃ መግባትና ሁኔታውን ተጠቅመው አከባቢውን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቆጣጠራቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከ 1882 ቱ የእምባቦ ጦርነት በኋላ የያኔው የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ የጎጃሙን መሪ ንጉሥ ተክለ ኃይማኖትን አሸንፈው በአከባቢው ላይ የጫኑት የጭሰኛ ሥርዓትና የአካባቢውን ሕዝብ ያገለለ ኢ ፍትሐዊ የፖለቲካ አስተዳደር ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ምናልባትም መልኩን ቀይሮ እንደሆን እንጂ በፖለቲካ ሥልጣንና በሀብት ክፍፍል፣ በተለይም በመሬት ይዞታ፣ ዙሪያ የሚደረጉ ትግሎች የአካባቢውን ማኅበረ ፖለቲካዊና ማኅበረ ባህላዊ ግንኙነት በአሉታዊ መልኩ ቀይረውታል። ለዛሬዎቹ የእርስ በርስ መቆራቆዝም እንደመነሻ ተደርገው ይወሰዳሉ። በቀዳማዊ ኃይሌሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ግንኙነቶች ተመሳሳይ ቢመስሉም የሕዝቦች ፍልሰት መበራከት ነገሩን አወሳስቦታል። ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ ዘመን ድረስ በአካባቢው የተከሰቱት ፈርጀ ብዙ የሕዝቦች ፍልሰትና ሰፈራዎች ( ማለትም መጀመሪያ በአካባቢው ባላባቶች ግብዣና ፈቃድ የተካሄዱ ሰፈራዎች፣ በደርግ ዘመን በሕዝብ ማስፈር ፕሮግራሞች የተከናወኑ ሰፈራዎች እና ከደርግ ዘመን በኋላ በራስ ተነሳሽነት የተፈፀሙ ፍልሰቶች ) ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ በተለይም ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከወሎና ከትግራይ ጭምር፣ የሚመጡ ሕዝቦችን ቁጥር በመጨመር በአንድ በኩል በአካባቢው ሥነ ምኅዳር ላይ ያለውን ጫና በማባባስ በሌላ በኩል ደግሞ በእርሻ መሬት ዙሪያ ያለውን ፉክክርና ፀብ በመጨመር በሕዝቦች መካከል ያለውን ሁለንተናዊ መስተጋብር በአዎንታዊውም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ቀይረውታል። በአዎንታዊ መልኩ በሰፋሪዎችና በአከባቢው ማኅበረሰብ መካከል አዳዲስ የኢኮኖሚ ትስስሮችን ፈጥረዋል። ለምሳሌ ሠፋሪዎቹና ጉልበት ፈላጊ የሆኑ የአካባቢው ገበሬዎች በመሬት ኪራይ፣ በእኩል እርሻ፣ በሲሶ ሽርክናዎችና እንዲሁም በጉልበት ሠራተኝነት የጥቅም ትስስር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉ ሲሆን፤ በአሉታዊ መልኩ ደግሞ የሠፋሪው መብዛት የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር በማራቆት በተለይም ደኖችን በመመንጠርና የመሬት ወረራ በማስከተል ጉዳት አድርሰዋል የሚሉ ድምፆችን አበራክቷል። እነኚህን ክስተቶች የብሔር ቅርፅ በማስያዝ ለራሳቸዉ ዓላማ ማስፈጸሚያ የተጠቀሙ ልሂቃን በሕዝቦች መካከል ክፍፍልና ግጭትን ለመፍጠር በሰፊው ተጠቅመውበታል። ማጠቃለያ በሚገርም ሁኔታ ከላይ የተጠቀሱት ውጣ ውረዶች እንዳሉ ሆነው፤ የማኅበረሰብ ግንኙነቶችና መስተጋብሮች በሁለት ጉልህ ኩነቶች መካከል፣ ማለትም በግጭትና በሠላም፣ የሚመላለሱ ክስተቶች ናቸው በሚያስብል መልኩ፤ የደፈረሱ ሰላሞችና መልካም ግንኙነቶች በእርቅ ተመልሰው ሲጠገኑና ሲጠብቁ፤ በግጭት ምትክ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች፣ በተለይም የንግድ ልውውጦችና ትስስሮች፣ ሲጠነክሩ፤ ኩታ ገጠም በሆኑ ነዋሪዎች መካከል በማምረት ተግባር ውስጥ ማኅበራዊ መደጋገፎች በደቦ፣ በወንፈልና በመሳሰሉ የጉልበት ትብብሮች ሲደምቁ፤ በባህልና በጋብቻ በሚፈጠሩ የደም ግንኙነቶች ሲጋመዱና ሲሰናሰሉ፤ የኢኮኖሚ ጥቅሞችና ፍላጎቶች የሚያጣሉም የሚያስተሳስሩም ሆነው ታይተዋል። በአጠቃላይ እነኚህ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ለፖለቲካ ሥልጣንና ለኢኮኖሚ በረከቶች የሚደረገውን ፉክክር ከማባባሳቸው በተጨማሪ ለሕዝቦች ሁለንተናዊ ትብብርና ትስስርም መሠረት መሆን ችለዋል። ይህ የሚያሳየን የሕዝቦች ግንኙነት የሚገነባው የጎሳ ፖለቲካ ነጋዴዎች እንደሚሉት በዘውግ፣ በደምና በማንነት ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው በጥቅምና በፍላጎት በተለይም በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና በእኩል የሥልጣን ባለቤትነት ዙሪያ መሆኑን ነው። ሆኖም ግን ማዕከላዊው መንግሥት በሚፈጥራቸው ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች በእኩልነት በማያስተናግዱ መዋቅሮች የተነሳ ( ለምሳሌ በዘውድ አገዛዙ ዘመን በሕዝቡ ላይ በተጫነው የጭሰኛና የመሬት ከበርቴ ሥርዓት፣ በኢሕአዴግ ጊዜ ደግሞ ዘውግን ( ዘርን ) መሠረት ያደረገ አግላይ ሥርዓት ምክንያት ) የሕዘቦች ግንኙነት ተግዳሮት ገጥሞት ቆይቷል። በመሆኑም ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች በእኩልነት ተከባብረውና ሠላማዊ መስተጋብር ፈጥረው እንዲኖሩ ከተፈለገ አካታች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምኅዳር መገንባት ከመንግሥት የሚጠበቅ መሆኑን ጥናቱ አፅንዖት ይሰጣል። IV. ሃይማኖታዊ መቻቻልና ባህላዊ ተዛምዶ የሃይማኖቶች አብሮነትና ብዝኃ ሃይማኖተኝነት በኢትዮጵያ ከ 19 ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ ዶ / ር አህመድ ሐሰን የዚህ ጥናት ዋና ትኩረት ከ 19 ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖቶች አብሮነትና ብዝኃ ሃይማኖተኝነቶች በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩና ከዘመን ዘመን ምን ዓይነት መልክ ይዘው እንደተጓዙ ማሳየት ነው። አብሮነቱም ሆነ ብዝኃ ሃይማኖተኝነቱ አሁን ከተወሰደው የጊዜ ቀመር በፊትም ነበሩ። ወደፊትም ይኖራሉ። ዋናው ትኩረታችን ግን ከ 19 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁኑ ጊዜያችን ድረስ ያለውን ብቻ በመውሰድ ታሪካዊ እውነታዎችን አንጥሮ ማውጣት ነው። አቀራረባችን የሃይማኖትን ምንነት በመግለፅ ይጀምራል። ሃይማኖት ሲባል ለአመኑበት ፈጣሪ እራስን አሳልፎ በመስጠት ማመን ነው። ሕጎቹንም በጥንቃቄ ተገንዝቦ መተግበር ነው። በየትኛውም አገር፣ በማንኛውም ስፍራ፣ ባህላዊ እና ሞራላዊ እሴቶች ጋር ተጣጥሞ የሰውን ልጅ ወሰን የለሽ የአስተሳሰብ ጥልቀትን ይዞ ቅዱሳን ስፍራዎችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና ካለንበት እውነታ እስከ ትንበያ በማካተት የሰውን ልጅ በእምነት በመያዝ በእምነቱም እንዲፀና የሚያደርግ ሃይማኖት ይባላል። የሃይማኖት አብሮነትም የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች በሰላምና በመተሳሰብ መኖር ማለት ነው። በመቻቻል ሂደት ሁሉ ወደተሻለ ደረጃ የመሄዱ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከሁለትና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሃይማኖቶችን የሚከተል የአንድ አገር ማኅበረሰብ በየትኛውም ስፍራ እና በየትኛውም ወቅት በብዝኃ ሃይማኖተኝነት ይታወቃል። ይህ ጥናት ሲዘጋጅ በተለያዩ ሃይማኖቶች ላይ በተከናወኑት የምርምር ውጤቶች ላይ በቂ ዳሰሳ ተደርጓል። የሃይማኖቶች አብሮነትና ብዝኃ ኃይማኖተኝነቱ በምን መልኩ እየተከናወኑ በታሪክ ሂደት ውስጥ እንዳለፉና አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳሉም ለማወቅ ቅኝት ተደርጓል። በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ላይ በመንተራስም የመካከለኛው ዘመን የሃይማኖቶችና የአብሮነታቸው እንዲሁም የብዝኃ ሃይማኖተኝነቱ ሁኔታ ተገምግሟል። የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ለምሳሌ ያህል ሐረር፣ ይፋት፣ ባሌ፣ አውሳና ወሎ፣ ከብዙ በጥቂቱ በምሳሌነት ተነስተው መጠነኛ የሆነ ቅኝት ተደርጎባቸዋል። በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት መካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍለ ዘመን የሃይማኖቶች መገፋፋት የታየበት ረዥም ዘመን ነበር ። በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ፣ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት በፈላሻና በአገው ማኅበረሰብ ዘንድ የተስፋፋበት ነበር። በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖትም ውስጥ በቤተ ኢዎስጣጢዎስ እና በቤተ ተክለ ሃይማኖት ተከታዮች መሃል መገፋፋቱ እንጂ መቻቻሉ አልታየም ነበር። እስጢፋኖሳዊያን ተብለው በመፈረጅ ከኢትዮጵያ የተሳደዱትን ብንወስድ የሰባተኛው ቀን ( Seventh Day ) ተከታይ ናችሁ ስለተባሉ በስደት እንጂ በመቻቻል አብሮ የዘለቁበት ዘመንና ወቅት አልነበረም። ዋናው ቁምነገሩ ከዚያ ዘመን ምን መማር እንችላለን የሚለው ጥያቄ ነው። የክርስትና ሃይማኖት የማዕከላዊ መንግሥት ተቀፅላ ሆኖ የመቆየት፣ የብዝኃ ሃይማኖት መቻቻል ያልታየበትና የዚያ ዓይነቱ ሂደት የተንሰራፋበት መሆኑን መገንዘብ ነው። የዚያ ሂደት ፋይዳውስ ምን ነበር ወይንስ ፋይዳቢስ አካሄድ ነበር ብሎ መጠየቅ ነው። የዚህ ጥናት ዋናው ትኩረት ከ 19 ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እስከ አሁኑ ወቅት ባለው ሁኔታ ላይ አጭር ዳሰሳ ማድረግ ነው። 19 ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ አዎንታዊ ጥልቀት የነበራቸውን የአብሮነትና ብዝኃ ሃይማኖተኝነቱ ሂደት በስፋት የተስተናገደበት መሆኑን የተለያዩ የታሪክ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ኢትዮጵያን በዘመኑ የጎበኙት የውጭ ሀገር ዜጎች በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የየራሳቸውን ትዝብት አስቀምጠዋል። ተአማኒነት ያላቸው ሌሎች የታሪክ መረጃዎችም የነበረውን ሁኔታ እንደዚሁ አካፍለውናል። የተለያዩ የውጭ አገር ጎብኚዎች የሰሙትን ብቻ ሳይሆን ያዩትንም በመዘገባቸው ግንዛቤያቸው ተአማኒነት አለው። ፈረንሳያዊው ጎብኚ ሮሼ ዴሪኩር ( Rochet D ’ Héricourt) እ . ኤ . አ . በ 1840 ዎቹ ሸዋን በጎበኘበት ወቅት በጨኖ፣ በፋሬና በሌሎች የወቅቱ ትላልቅ መንደሮችና አነስተኛ የሸዋ ከተሞች የሃይማኖቶች አብሮነትን እና ሰላምና የአብሮ መኖር ጥበብ የተሞላበትን ሁኔታ አስተውሏል። ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በጋራ ጉዳዮች ላይ እጅግ የሚስማሙና የሚተባበሩ መሆናቸውንም ተረድቷል። ቻርልስ ጆንስተን ( Charles Johnston ) የተባለው እንግሊዛዊ ጎብኚ ደግሞ በዚያኑ ወቅት የሸዋው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ለክርስቲያኑና ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ ትኩረቱን ከመሳቡ የተነሳ ይህንን ዓይነቱን ተግባር እኔ በንጉሡ ቦታ ሆኜ አድርግ ብባል የማላደርገው ነው ብሏል። በሐረርና በመሳሰሉት አካባቢዎች ይኸው ዓይነቱ ሁኔታ በሌሎች ጎብኚዎችም በሚገባ ተስተውሏል። ሪቻርድ ባርተን ( Richard Burton ) በሐረርና አካባቢዋ፣ ለፈብቭር ( Lefebvre ) የተባለውም ፈረንሳዊ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች፣ በተለይም በወሎ አካባቢ፣ ያየውን ሂደት የዘገበው በዚሁ ዓይነት መልክ ነው። በጥቅሉ ከጎብኚዎች ትዝብት ምን እንማራለን የሚለውን ጥያቄ መመለሱ አስፈላጊ ነው። የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች የሆኑት ኢትዮጵያውያን ለአብሮ መኖሩ ጉዳይ እንግዶች እንዳልሆኑ፣ ለብዝኃ ሃይማኖቶችና ሃይማኖተኝነቱም ቢሆን ነገሥታቱም ሆኑ የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ጉዳዩን በጥንቃቄና በመግባባት ላይ በመመርኮዝ የማክበር አካሄድ እንደነበራቸው ነው። ለምሳሌ ያህል እንደ አይዘንበርግና ክራፕፍ ( Isenberg and Krapf) የመሳሰሉ ጎብኚዎች በ 19 ኛው ክፍለ ዘመን፣ በተለይ በ 1830 ዎቹና በ 1840 ዎቹ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ማን የትኛውን ሃይማኖት ይከተላል ብሎ መለየቱ ሁሉ አስቸጋሪ እስከሆነባቸው ድረስ የኢትዮጵያውያንን የሃይማኖት አብሮነትና ብዝኃ ሃይማኖተኝነት በእጅጉ አድንቀዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የእስልምና ኃይማኖትን ታሪካዊ ሂደት የዘገበው ትሪሚንግሃም ( Trimingham ) ስለ እስልምና ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ሃይማኖቶች ( በክርስትናና በተለያዩ አማልክት በሚያምኑት አገር በቀል ኃይማኖቶች ጭምር ) ላይ ትኩረት አድርጎ አጥንቷል። ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድም ከትሪሚንግሃም የበለጠ ጥልቀት በመስጠት ወሎን እንደ ቤተ ሙከራ በመውሰድ ጠቃሚ የምርምር ሥራውን አከናውኗል። ከፕሮፌሰር ሁሴንም ሥራዎች የምንረዳው በሃይማኖቶች መካከል ችግር እንዳልነበረ፣ አብሮነታቸውም የጠበቀ መሆኑንና በምዕመናኑ አካባቢ ችግሮች ሲከሰቱም በሃይማኖቶች ጉዳይ ይሁን ከዚያ ውጪ የሆነ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንጂ ሌላ ችግር እንዳልነበረ ነው። በ 20 ኛው ክፍለ ዘመን፣ በተለይም ከ 1928 እስከ 1933 ዓ . ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር፣ ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያውያንን በሃይማኖት ለመከፋፈል ቢጥሩም አልተሳካላቸውም ነበር። በተለያዩ ስፍራዎች፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በተለያዩ ሃይማኖቶች ላይ የሃይማኖቶችን አብሮነትና ብዝኃ ሃይማኖተኝነቱን የተፈታተኑ ጉዳዮች እየተከሰቱ የመጡበት ሁኔታ አለ። ይሁን እንጂ መሠረታቸውና መድረሻቸው በአንዱ ወይንም በሌላው ሃይማኖት ችግር የተነሳ ጉዳይ ሳይሆን ሃይማኖትን በመሣሪያነት ለመጠቀም በሚፈልጉት አካላት የተነሳ ችግር መሆኑ በግልፅ ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ቢሆኑም አገራቸውን የሚወዱ፣ ለችግር ጊዜ ደራሽና ለእርስ በርሳቸውም ጉዳዮች ቀናኢ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሃይማኖቶቻቸውን አጥብቀው በመያዝ በጋራ የሚኖሩ ስለመሆናቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የሌላም ዓለም አገሮች ሕዝቦች መስካሪዎቹ ናቸው። የዚህ ዓይነቱን ታሪካዊ መስተጋብር በጥንቃቄና በጥልቀት አጥንቶ ለንባብ በማብቃት፣ በዚህና በመሳሰሉት ጉዳይ ላይ በውይይት የዳበሩ ሐሳቦችን ለአንባቢያኑ በማድረስ የታሪክ ምርምር ለአገር ደህንነትና ለሰላም መስፈን ሊጫወት የሚችለውን ሚና አጉልቶ ያሳያል። ወሎ፡ የአብሮነት፣ የሠላም እና የእምነቶች ተግባቦት ቀንዲል ዶ / ር አሰፋ ባልቻ በታሪክ ቤተ አማራ ተብሎ የሚታወቀው ግዛት የአሁኑን አብዛኛውን የወሎ አካባቢዎችን ያካተተ አቃፊ ስያሜ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና መስጊዶች የተመሠረቱት በ 9 ኛው እና በ 13 ኛው ክፍለ ዘመን መካከል እንደነበረ ከታሪካቸው መረዳት ይቻላል። የእስልምና እምነት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችና ልምዶች በመጀመሪያ ከቀይ ባሕር ዳርቻ የጠረፍ ግዛቶች ከኤደን ባሕረ ሰላጤ ጠረፍ አካባቢ እንዲሁም የክርስትና እምነት አስተምሮቶች ከአገራችን ሰሜን ክፍል ተነስቶ ወደ ወሎ ዘልቆ በተመሳሳይ ጊዜ በመግባትና በመጨረሻም በስፋት በመሰራጨት በክልሉ ዉስጥ ተመሳሳይ ውጤቶች ነበሯቸው። በ 9 ኛው እና 13 ኛው ክፍለ ዘመን መካከል የነበረው የመጀመሪያው የእስልምና እምነት ስርጭት ሂደት የተካሄደው በአብዛኛው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነበር። የዚህም ውጤት በርከት ያሉ እስላማዊ ማኅበረሰቦች በ 16 ኛው ክፍለ ዘመን የሙስሊም ክርስትና ጦርነቶች ከመካሄዱ በፊት በአካባቢው ይኖሩ እንደነበር በ 12 ኛው ክፍለ ዘመን የተሰራው መስጊድ ትልቅ ማሳያ ነው። በአህመድ ግራኝ ጦርነት ወቅት የእስልምና እምነት ለአጭር ጊዜ የበላይነት በተቀዳጀበት ጊዜ በወሎ የእስልምና የመስፋፋት እና መጠናከር ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ከአጭር ጊዜ በኋላ፣ የእስላማዊ እና እስላማዊ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች የሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትስስር / ግንኙነት እንደገና ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር። የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ጎሣ / ነገድ ቋንቋ ያለው ሕዝብ መቀላቀል ወሎን ልዩ የማኅበራዊና ባህል ውህድ ማቅለጫ ማሰሮ (melting pot) አድርጎታል። በወሎ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ( ማለትም የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የአገው፣ የአፋርና የአርጎባ ማህበረሰቦች ) መካከል ያለው የእምነትና የቋንቋ መሰባጠር በግዛቱ የፍቅር፣ የመከባበርና የመረዳዳት እሴቶች እንዲጎለብቱ በእጅጉ አግዘውታል። ኦሮሞዎች፣ በተለይ ዛሬ ወሎ በሚባለው አካባቢ በሚኖሩ ነዋሪዎች ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እምነቶችና ልምዶች ላይ ትልቅ ተፅእኖ አሳርፈዋል። ከ 16 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአማራ ክልል የኦሮሞ መስፈር በክልሉ ውስጥ የነገድና የባህል ድብልቅ / ቅልቅል ያለው ትውልድ እንዲፈጠር መንስኤ ሆኗል። ይህ የጅን / የዘረመል ውህደት እስከ 19 ነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቀጥሏል። ኦሮሞ ከአማራ ጋር ልክ እንደ አንድ ማኅበረሰብ የተዋሃዱ በመሆናቸው በአማራና በኦሮሞ መካከል ያለውን ልዩነት ለመናገር እንኳን አስቸጋሪ አድርጎታል። ይህ ድብልቅ / የተዋሃደ ማንነት መላውን የወሎ ማኅበራዊ ሕይወት ቀይሮታል። ምንም እንኳን የአማርኛ ቋንቋ እጅግ በጣም አስፈላጊ ቋንቋ ሆኖ ቢቆይም፤ ሌሎች የክልሉ ባህላዊ ሁኔታዎች በኦሮሞ ተፅእኖ ሥር ወድቀዋል። የኦሮሞ ባህላዊ አሻራዎች በወሎ ውስጥ አሁንም በጉልህ ይታያሉ። ሁለቱም ሃይማኖቶች ( ክርስትና እና እስልምና ) የማኅበራዊና ባህላዊ ልምዶችን ወሎ ውስጥ መካበበር በማስቀጠል በኩል ከፍተኛ አስተዋዕፆ አበርክተዋል። የእርስ በርስ መወራረስ ሂደቱ እስከ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እና አፄ ዮሐንስ አራተኛ መምጣት ድረስ ቀጥሎ ነበር። አፄ ዮሐንስ ይከተሉት በነበረዉ ሃይማኖታዊ ፖሊሲ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ተፈጥሮ የነበረው ብጥብጥ እና አለመረጋጋት አደጋ የጋረጠበት ቢመስልም፤ ነዋሪዎቹ ይህን በመቋቋም በአለፉት ክፍለ ዘመናት በአክብሮት ዋጋ ከሚሰጡት ማህበራዊ ካፒታል መካከል አንዱ የሆነውን የክርስትና ሙስሊም መዋሃድ ልምድ ንጉሠ ነገሥቱ ከአረፉ በኋላ በአዲስ መንፈስና በብርታት አይሎ እንደገና መከሰት እና ማደግ ጀመረ። በአጭሩ፣ የአካባቢው ሕዝብ በክፍለ ዘመናት መካከል በብዛት የሃይማኖት መለወጥና እንደገና ቅየራ ድግግሞሽ ማድረጉ ለአክራሪነት መሠረት በማሳጣቱ፣ ውህደቱን ለማቆየት ወሳኝ ምክንያት ነበር። በዚህ ምክንያት ነዋሪው ሰው መሆንን ብቻ መሠረት ወደ አደረገ መቀራረብ በማጎልበቱ ሃይማኖታዊና ልማዳዊ አጥሮችን ጥሶ ለመሻገር የሚያስችሉ ማኅበራዊ እሴቶችን ለማሳደግ አስችሎታል። ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፣ የእምነት ልዩነት የሌሉባቸው ዕድሮችን በጋራ መገልገል፣ የሃይማኖት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ወይም አንዱ የሌላዉን እምነት በመቀበል ትዳር መመሥረት፣ እና ከመገበያየት ባለፈ ፍልውሃዎችንና ፀበሎችን በኅብረት መጠቀምን ማንሳት ይቻላል። ይህ መስተጋብር የአካባቢውን ሕዝብ የነገድ / ዘውግ ብዝሃነት፣ የባህል መደባለቅ፣ የእምነት እና የእሴት እርስ በርስ ውህደት ተጠብቆ እንዲኖር አድርጓል። የክርስትና እና የእስልምና አቃፊነት ተፈጥሮ እና የአገር በቀል የእምነት ሥርዓት ክልሉን የሃይማኖትና የአካባቢ ልማዶች ማቅለጫ / ማዋሃጃ አድርጎታል። ይህም በበኩሉ ማኅበራዊና ባህላዊ ውህዶችን፣ ተግባራዊ መከባበርን እና ብዝሃነትን አቅፎ ለማራመድ እገዛ አድርጓል። ይህ የተደባለቀ ድባብ፣ ክፍት የወሰኖች ሞዴል / ቅርፅ በመፍጠሩ፣ የተለያዩ ልማዶችን የመጋራት እና የማኅበራዊ ልምዶችን አቃፊነት ለማልማት አስችሏል። ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ዘወትር እርስ በርስ ይጋባሉ፣ ማህበራዊ ግንኙነት ያካሂዳሉ፣ አንዱ በሌላው በዓላት ላይ ይገኛል፣ በንግድ ሥራ ይሳተፋሉ፤ እንዲሁም ሌሎች የሥራ እንቅስቃሴዎችን በጋራ ያከናውናሉ። በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ትብብር በመምራት ለእርስ በርስ መተማመን፣ ለማኅበራዊ ትስስር አና ኅብረት እንዲሁም ወደ ክርስቲያን እና ሙስሊም ቅዱስ ቦታዎች የሚደረጉ ሃይማኖታዊ ጉዞዎች ዋጋ ያለው የመሠረት ድንጋይ ሆነው ቆይተዋል። እናም እነዚህ አስፈላጊ ኹነቶች አንድ አድራጊ እና አዋሃጅ ኃይል በመሆን የነገድ ቋንቋ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ድንበሮችን ተሻግረዋል። እነዚህ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ደግሞ ዋና ማኅበራዊ ባህላዊ እሴቶችን ለመንከባከብና ለማጠናከር፣ በሰላም አብሮ መኖርን ለማስጠበቅ፣ የማኅበረሰቡን ደህንነት መጠበቅ፣ ለጋራ ትብብር እንዲሁም ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት ጠቃሚ መሣሪያዎች ናቸው። የወዳጃ ሥነ ሥርዓትን በመጠቀም በአብዛኛው በእምነቶቹ መካከል መጣጣም እንዲቀጥል፣ እርስ በርስ መተማመን እንዲጎለብት አግዟል። ይህም ለማኅበራዊ አንድነት እና ለሥነ ውበታዊ ዕድገት ያበረከተዉ አስተዋእፆ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሥነ ውበታዊ አስተዋዕፆ ወሎ የአራቱ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ባቲ፣ አምባሰል፣ አንቺሆየ እና ትዝታ - ‹‹ የትውልድ ቦታ ›› የሚል ስያሜ እንዲያገኝ አስችሎታል። ለማጠቃለል፣ እነዚህ ሕዝብን ወደ ፍቅር የሚመሩና የሚያስተሳስሩ እሴቶች የወሎን ማኅበረሰብ ብሔር፣ ቋንቋ እና ማንነት ሳይለይ በአንድነት ተቀብሎ የማስተናገድ ባህል እንዲያዳብር በመርዳቱ ወሎ የበርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች መኖሪያ እንድትሆን አስችሏት እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። V. ከተሜነትና የንግድ ልውውጥ ከተሞች፣ ከተሜነትና፣ የብዝሃ አገር ግንባታ በኢትዮጵያ ዶ / ር ሽመልስ ቦንሳ እንደ መግቢያ እንደሚታወቀው ሀገሮች ተፈጥሯዊ ሳይሆኑ ሰዎች የሰሯቸው፣ ዘላለማዊ ያልሆኑ፣ በቅርጽም በይዘትም እየተለዋወጡ የሚሄዱ ናቸው። የብዙ አገሮች የሀገር ግንባታ ታሪክ የሚያሳየን ከተሞች፣ በተለይ ደግሞ ዋና ከተሞች፣ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ ሀገርና ሀገራዊ ማንነትን ለመፍጠር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ነው። በአንድ በኩል ከተሞች የሀገር፣ በተለይም የዘመናዊ ሀገር፣ መገንቢያ የሆኑት መሠረቶች የሚተከሉባቸውና የሚዳብሩባቸው ሥፍራዎች ናቸው። ለምሳሌ አንድ ሀገርን ከሕዝቡ፣ ሕዝቡንም ከሌላው ዓለም ጋር የሚያስተሳስሩት የመገናኛና የትራንስፖርት ተቋማት መነሻቸው ወይንም ዋና መቀመጫቸው በከተማ ነው። የተራራቀውንና የማይተዋወቀውን የሀገሪቱን ሕዝብ እንዲተሳሰሩና፣ የአንድ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን አውቀው በሰላምም በችግርም ጊዜ አብረው እንዲቆሙ ከሚያደርጉት ውስጥ ከተሞችና ከተሜነት በዋናነት ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል ከተሞች የብዝሃነት እንዲሁም የተለያዩ አመለካከቶች መገኛ ሥፍራም በመሆናቸው ከሌሎች ቦታዎች በበለጠ ለፉክክር የተጋለጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። በማንነት፣ በመደብ፣ በጾታ፣ በዕድሜና በመሳሰሉት የተዋቀሩ የማኅበረሰብ አባላት የሚኖሩባቸው ከተሞች የተለያዩ፣ አንዳንዴም የተጋጩ፣ አስተሳሰቦችንና ትርክቶችን ያስተናግዳሉ። እነኝህን የማንነትና የአመለካከት ብዝሃነቶችን መሸከም የማይችል ወይንም የማይፈቅድ የፖለቲካ ሥርዓት ባለባቸው ሃገሮች ልዩነቶችና ግጭቶች፣ ሲብስም ሕዝባዊ ትርምሶች፣ በከተሞቻቸው ገነው ይታያሉ። ለዚህም ነው የብዝሃነት ዋና ተምሳሌት የሆኑት ከተሞች ሁሉን ያቀፈ፣ ለማንም ያላዳላ፣ ፍትሕንና እኩልነትን ያስቀደመ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያስፈልጋቸው። በዚህ ባሕርያቸው ምክንያትም የተነሳ ነው ከተሞች የተሻለ ሀገርና ነገን ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም ሆነው የሚገኙት። እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ታዳጊ ሀገሮች ከተሞችና ከተሜነት አዲስና ሁሉን አቀፍ የሆነ ዘመናዊና ብሔራዊ ማንነትንና በዛም ላይ የቆመ ሀገርን በመገንባቱ ሥራ ቀዳሚና ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ከተሞች በተለይም ዋና ከተሞች፣ የአንድን አገር ሕዝብ የሚያገናኙ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ትርክቶችን፣ ተቋማትንና መዋቅሮችን በመገንባት የሁሉም፣ በሁሉም፣ ለሁሉም የሆነ ዜግነትንና ሀገርን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ትግል ያግዛሉ፤ ተምሳሌትም በመሆን ያገለግላሉ። ይህንን ብዝሃነትን የተቀበለ፣ ሁሉንም ያማከለ፣ ለሁሉም የሆነ ሀገርና ዜግነትን ለመገንባት ብዝሃነትን መሠረት ያደረጉ፣ ያከበሩ ከተሞችና ከተሜነትን ማስፋፋትና ማሳደግ ያስፈልጋል። ከተሞች፣ ከተሜነትና፣ አገር ግንባታ በኢትዮጵያ ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ውስጥ ብዛት ያላቸው ከተሞች ተመሥርተዋል፤ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በነኝህ ጊዜያትም ከተማንና ከተሜነትን መሠረት በማድረግ የዘመነችና ብሔራዊ የሆነች ሀገርን ለመፍጠር ተሞክሯል። ከተሞች የሀገርነት፣ የዘመናዊነት፣ የአንድ ዓይነት ሳይሆን የአንድነት ተምሳሌት ሆነው እንዲያድጉ ተጥሯል። አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች አፈጣጠራቸውና ዕድገታቸው ከችግር የተላቀቀ ባይሆንም ከፍተኛ የሆነ ብዝሃነት፣ የረጅም ጊዜ አብሮነትና፣ ጥልቅ የሆነ ንብርብርነት መገለጫቸው የሆኑ ቦታዎች እየሆኑ አድገዋል። በከተሞች ያለው ንብርብር ሕይወትና አብሮነት ባህል፣ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበው ቀጥሏል። የመደብ ልዩነቱ እየሰፋ ቢመጣም፣ የታጠሩ የሀብታም መንደሮች ቢፈጠሩም፣ አሁንም ድረስ ድሃና ሀብታም ተቀራርበውና ተሰባጥረው ከሚኖሩባቸው የአፍሪካ ከተሞች ውስጥ እንደ አዲስ አበባ ያሉ የኢትዮጵያ ከተሞች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ነገር ግን ይህ አብሮነትና ከተማንና ከተሜነትን መሠረት ያደረገ የዘመናዊ ሀገር ግንባታ ሥራ በሁሉም መልኩ የተሳካ ነበር ማለት አይቻልም። በዘውዳዊው ሥርዓት ብዙ ከተሞች በተወሰኑ ሰዎች የመሬት ባለቤትነት ተይዘው፣ ብዙኃኑ ነዋሪዎቻቸውም ከፖለቲካ ዓለም ተገለው፣ በድህነትና በከተማ ጭሰኝነት የሚኖሩባቸው ቦታዎች ሆነው ነበር። በዘውዳዊውም ሆነ ተከትለው በመጡት “ አብዮታዊ “ ነን ባሉ ሥርዓቶች በከተሞች ውስጥ፣ እንዲሁም በከተሞችና ዙሪያቸውን በከበቧቸው የገጠር አካባቢዎች መካከል፣ እኩል ያልሆኑ፣ ብዝበዛን መሠረት ያደረጉ ግኑኝነቶች ስር ሰደው ነበር። እነኝህም ኢፍትሓዊ የጭቆና መዋቅሮች ለሕዝባዊ ዓመጾች፣ ከፍ ብሎም ለሥርዓት ለውጦች፣ መምጣት ቁልፍ ምክንያት ሆነዋል። በቅርቡ የሀገሪቱ ታሪክም ገጠርን፣ ግብርናንና ገበሬውን ያገለለና ለድህነት የዳረገ በኒዎሊበራሊዝም የታቀኘ የከተማና “ የልማት “ መስፋፋት ገጠርና ገበሬውን በከተማና ከተማ ውስጥ በተንሰራፋው ኢፍትሓዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ላይ እንዲያምጽ በማድረግ የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ለማስገደድ ሁሉ በቅቷል። እንግዲህ ያለፈው የአንድ መቶ ዓመት የከተማና የሀገር ግንባታ ታሪክ እንደሚያሳየን ሀገሪቷም ሆነ ከተሞቿ ከአብሮነትና አንድነት ታሪካቸው ጎን ለጎን መለያየቶችና መገፋቶች የሰፈነባቸው እንደነበሩና እንደሆኑ ነው። በተለይ ደግሞ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ብሔርን ማዕከል ያደረጉ የክልል መንግሥታትን በመፍጠር የብዝሃነት ተምሳሌት የሆኑትን ከተሞችን አግልሏል። ብዝሃነት ገዥ መመሪያዬ ነው ያለው ሥርዓት ኅብረ ብሔራዊ የሆኑ ከተሞችንና የብዝሃነት መገለጫ የሆኑ ተቋማትንና መዋቅሮችን አዳክሟል። የማንነት ፖለቲካው ከሕዝበኝነት ጋር በተጋባ ቁጥርም “ መጤ ” ና “ ነባር ” የሚሉ ልዩነቶችን በመፍጠር፣ በከተማና በገጠር ያለውን ክፍተት በማስፋት፣ “ መጤ ” ዎች፣ ከተሞችና ከተሜዎች በጥርጣሬ፣ ሲብስም በጠላትነት፣ እንዲታዩ ምክንያት ሆኗል። መፈናቀል፣ ንብረት መውደምና ሕይወት ማጣት የተለመደ ክስተት ለመሆን በቅቷል። በዚህ ሁሉ ውስጥም ኅብረ ብሔራዊ ከተሞች፣ በተለይም አዲስ አበባ፣ ዋነኛ የፉክክርና የመታገያ ቦታዎች እየሆኑ መጥተዋል። ወደፊትም ከተሞች ማንነትን፣ ባለቤትነትንና ውክልናን መሠረት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ትግሎች የሚካሄዱባቸው ዋነኛ ስፍራዎች ሆነው ይቀጥላሉ። በጥንቃቄ ተይዞ መፍትኄ ካልተፈለገላቸውም እነኝህ ከተማን መሠረት በማድረግ ታሪክና ትርክትን መጠቀሚያ ያደረጉ፣ ከፍትሕና እኩልነት ጥያቄ በተጨማሪ በዋነኝነት ሀብትና ሥልጣንን ለመያዝ የሚደረጉ ትግሎች ደም አፋሳሽ፣ ሕዝብ ጨራሽና ሀገር አፍራሽ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ከተሞችን እንደ አንድ ቁልፍ መሠረት ያደረገው የሀገር ግንባታ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የተሻለ በሁሉም የሚሠሩ፣ የሁሉምና ለሁሉም የሆኑ ከተሞችና ሀገር እንዲመጣ ምን ማድረግ ያስፈልጋል ? ከተሞች የሚያስተምሩት፣ ለተሻለ ሀገር ግንባታ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ልምዶች ምንድን ናቸው ? ምን ይደረግ ? ዜጋውስ ምን ያድርግ ? እንደ ማጠቃለያ ከተሞች ለአዲሲቷ ኢትዮጵያና ለአዲስ ዓይነት ኢትዮጵያዊነት መፈጠር ምክንያት እንዲሆኑ በመጀመሪያ እነሱን የአዲስ ዓይነት ብዝሃነት፣ ሀገራዊ ብሔርተኝነትና ዜግነት መሠረት እንዲሆኑ አድርጎ ማደራጀት ተገቢ ነው። መልካም የሆነ፣ ለሁሉም እኩል የሚሆን ሀገር ለመገንባት መልካምና ፍትሓዊነትን መሠረት ያደረጉ ከተሞችን መገንባት ያስፈልጋል። መልካም ከተሞች ማለት መልካም ሀገር ማለት ነውና። ከተሞች የእኩልነት፣ የብዝሃነት፣ የዲሞክራሲ በእነዚህም ላይም የተመሠረተ ዜግነትና ኢትዮጵያዊነት ተላብሰው ከተገነቡ ሀገሪቷንም በነኝህ ምሰሶዎች ላይ ለማደራጀት ይቀላል። በአዲስ አበባ፣ ከዛም በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የሚገነባ እኩልነትን፣ ብዝሃነትን፣ መቻቻልን መሠረት ያደረግ ዜግነትና ኢትዮጵያዊነት ወደሰፊው የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋትና ስር እንዲሰድ ለማድረግም ይቻላል። ታላቂቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት በየቦታው በሀገሪቷ ባሉ ገጠሮች፣ በተለይ ደግሞ በከተሞች፣ ትንንሽ ኢትዮጵያዎችን መፍጠርና ኮትኩቶም ማሳደግ ያስፈልጋል። በተለይ ከተሞች ካላቸው የብዝሃነት ስፋት፣ ቁልፍ የፖለቲካ ሚናና ሰፊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የተነሳ፤ አዲሲቷ ኢትዮጵያና አዲሱ ኢትዮጵያዊነት የሚደራጅባቸውና የሚያድግባቸው ዋና ቦታዎች ናቸውና ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ሊደረግላችው ያስፈልጋል። ከተሞች የሀገሪቷ ምንነትና ማንነት ዋና ፈጣሪ፣ ነጸብራቅና ተምሳሌት ናቸውና ይህንን ድርብርብ ሚናቸውን በስኬት እንዲወጡ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ተቋማዊና መዋቅራዊ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል። እንግዲህ ከተሞችና ከተሜዎች የሚኖሩትን የተጋመደ ሕይወት፣ የተሰባጠረና የተሳሰረ ብዝሃነትን መሠረት በማድረግ ለሁሉም፣ የሁሉም የምትሆን ፍትሕን፣ እኩልነትንና ኅብረ ብሔራዊነትን ያስቀደመች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ሁሉም ሊነሳ ይገባል። አዲስ አበባ፡ የመቻቻልና የመከባበር ኅብረ ብሔራዊ የአብሮነት ከተማ ዶ / ር አልማው ክፍሌ አዲስ አበባ በ 2010 ዓ . ም እንደተደረገ ግምት ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ከተማ ስትሆን በ 11 ክፍለ ከተማና በ 121 ወረዳዎች የተዋቀረች ናት። ነዋሪው ሕዝብም በነዚህ የአስተዳደር ወሰኖች ተደራጅቶ የሚኖር ነው። በታሪክ አጋጣሚ የመንግሥታት መናገሻ ከተሞች ከሆኑት ከአክሱም፣ ከላሊበላ እና ከጐንደር ቀጥላ የተመሠረተች አራተኛዋ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ናት። የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የርእሰ ብሔሩ መቀመጫ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም መዲናና የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ አማካሪዎች መኖሪያ ናት። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የዕውቀት፣ የሳይንስ፣ የሚሊታሪና የሃይማኖት ዋና ማዕከል ናት። ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት፣ ሁሉም ቋንቋዎች የሚነገርባት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ችሎታውና እንደ አቅሙ የሚስተናገድባት ከተማ ናት። የአዲስ አበባ አመሠራረትና እድገት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና መዲና ሆና ከመቆርቆሯ በፊት በአካባቢው በጥንትና የመካከለኛው ዘመን የነገሥታት የጦር ካምፖችና የተለያዩ ሕዝቦች መኖሪያ የሆኑ ብዙ መንደሮች እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የአዲስ አበባ በ 1879 ዓ / ም አመሠራረት እንደ አብዛኞቹ ዋና ከተሞች በቅኝ ገዥዎች አመራር ሳይሆን የራሱ የሆነ ምክንያት ነበረው። አዲስ አበባ ከሌሎች ቀደምት የኢትዮጵያ መናገሻ ከተሞች የምትለየው በአገሪቱ እምብርትና ማዕከል ላይ መገኘቷ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቋንቋዎችን፣ እምነቶችን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን፣ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ያማከለች የሰፊ ግዛትና የብዙ ፍላጎቶች መዳረሻ በመሆኗም ነው። በእቴጌ ጣይቱ ብጡል መሪነት የከተማ ማስፋቱ ሂደት ከደጋማውና ቀዝቃዛው የእንጦጦ ተራራ ወደ ሜዳማውና ደቡባዊው ክፍል እንዲሆን ተወስኖ ቤተ መንግሥቱ ከእንጦጦ ወደ ፍልውሃ ( ፊንፊኔ ) አካባቢ ተዛወረ። የአዲስ አበባ ግንባታ የተከናወነው ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተጠርተው በመጡ ባለሙያዎች፣ በትዕዛዝ በተሰበሰቡ ልዩ ልዩ ግብአቶችና መዋጮዎች ነው። ከኢትዮጵያ ውጪ ማለትም ከሕንድ፣ ከጣሊያን፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከእንግሊዝ፣ ከቱርክ፣ ከፖርቱጋል የመጡ የግንባታ ሥራ ጠበብቶችና አማካሪዎችም በከተማው የግንባታ ማስፋፊያ ሥራ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ እንደነበር የሚያሳዩ ሰነዶችና ሕንፃዎች እስከዛሬም በብዛት ይገኛሉ። በእቴጌ ጣይቱ የበላይ አመራር የአዲስ አበባ ኮረብታዎችና ሜዳዎች ለተለያዩ የአገሪቱ ሹማምንትና የጦር መሪዎች አከፋፍሎ በመስጠት ቤተ መንግሥቱን ከበው የየራሳቸውን ሰፈሮች እዲመሠርቱና ደብሮች እንዲገነቡ ተደረገ። ይህ ክስተት ለአብዛኛው ሹማምንት ከትውልድ አካባቢያቸው አገልጋዮችንና ዘመዶቻቸዉን አምጥተው እዲያሰፍሩ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይነገራል። ለምሳሌ የራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ሰፈርን፣ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ሰፈርን፣ የደጃች ውቤ ሰፈርን መጥቀስ ይቻላል። በአንፃሩ፣ ከቤተ መንግሥት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሠራተኛ ሰፈር፣ ዘበኛ ሰፈር ተብለው የሚጠሩ ሰፈሮች ተፈጠሩ። ሌሎች አዲስ አበባ ከተማ እንድትስፋፋና እንድታድግ፣ የሕዝቦች ግንኙነትና ትስስርም የበለጠ እንዲጠናከር ያደረጉ ዋና ዋና ክሰተቶች የአድዋ ድል፣ እሱንም ተከትሎ የሌጋሲዮኖች መከፈት፣ የ 1899 ዓ . ም የመሬት ይዞታ ማረጋጫ፣ በ 1909 ዓ . ም የጂቡቲ አዲስ አበባ የምድር ባቡር መስመር አዲስ አበባ መድረስ፣ በ 1898 ዓ . ም . የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መዋቅር መጀመር፣ የ 19281933 ዓ . ም የጣሊያን አገዛዝ እና በ 1955 ዓም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ናቸው። ሕዝባዊ ውክልናን አመላካች የሰፈሮች ስያሜ አዲስ አበባ የሌሎች አካባቢዎችን ሀብትና ዕውቀት በተለያየ መልኩ የምትወስድና የምታጋብስ ብቻ ሳትሆን የሌሎችን እህት ከተሞችና ክልሎች ችግር የምትጋራ መፍትሄም የምታፈላልግ ከተማ ናት። በችግርም ይሁን ምቾት ፍለጋ ከየትኛውም የኢትዮጵያ አከባቢ ለሚመጣ ሰው መጠለያ፣ የዕለት ጉርስ ማግኛና እንደ አቅምና ችሎታው ሥራ የማትነፍግ ከመሆኗም ባሻገር ለየአንዳንዱ ክፍለሀገር ወይም ብሔረሰብ የውክልና የሚባል ሰፈር ሰይማለች። ለምሳሌ፡ ወሎ ሰፈር፣ ወለጋ ሰፈር፣ ጎጃም በረንዳ፣ ሲዳሞ ተራ፣ ሶማሌ ተራ፣ ጎንደሬ ሰፈር፣ ጅማ በር፣ አስመራ መንገድ፣ ሸጎሌ፤ ገጃ ሰፈር፣ አባ ኮራን ሰፈር፣ ሐረር በር። እርግጥ ነው ሁሉም እነዚህ መጠሪያዎች ሙሉ በሙሉ የተጠቃሹን ብሔረሰብ ወይም ማኅበረሰብ ያመለክታሉ ማለት አይደለም። በጊዜ ሂደትም አንዳንዶቹ ከመጀመሪያ መጠሪያቸው የተለየ የማኅበረሰብ ስብጥር ማንፀባረቅ ችለዋል። ነገር ግን ሥረ መሠረታቸው በአብዛኛው የብሔረሰብ ወይም የማኅበረሰብ አሰፋፈርን አመልካች ነበር። ከከተማይቱ እድገትና መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሙያን፣ የአገልግሎት አሰጣጥንና የሃይማኖት ተቋማትን መሠረት ያደረጉ የሰፈር ስያሜዎች ሊፈጠሩ ችለዋል። ለምሳሌ፣ የሃይማኖት ተቋማትን መሰረት ያደረጉ እንደ ዮሐንስ፣ ብሥራተ ገብርኤል፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ ተክለሃይማኖት፣ መሳለሚያ እና መስጊድ ያሉትን የሰፈር ስያሜዎች መጥቀስ ይቻላል። በሚሰጡት አገልግሎትና በአካባቢው በሚገኘዉ ሸቀጥ ዓይነት ተሰይመው ከሚጠሩት መካከል በርበሬ ተራን፣ ሚስማር ተራን፣ አትክልት ተራን፣ ጌሾ ተራን፣ ጨው ተራን፣ አውቶቢስ ተራን እና ቄራን መጥቀስ ይቻላል። ከነዚህ በተለየ መንገድ በውጭ አገር ወይም ድርጅት ስም የሚጠሩ ሰፈሮችም አሉ። ሜክሲኮ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ፣ ለገሀር፣ ባምቢስ፣ ካዛንችስ፣ ኦሎምፒያ፣ ፖፓላሬ፣ ፈረንሳይ ( ለጋሲዮን ) ፣ ላንቻ፣ ቤላ። በነባሩና ማዕከላዊዉ የከተማዋ ክፍል ዙሪያ ደግሞ በአብዛኛው የኦሮሞ መጠሪያ ያላቸው ሰፈሮች አሉ ( ለምሳሌ ጉለሌ፣ ቦሌ፣ ላፍቶ፣ ገርጂ፣ ኮተቤ፣ የካ፣ ቡራዩ፣ ካራ ) ። እነዚህ አካባቢዎች ለከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል የተለያዩ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎችንና ልዩ ልዩ ግብአቶችን የሚያቀርቡ ናቸው። ይህ በከተማዋ እምብርትና በዙሪያዋ ባሉት ነዋሪዎች መካከል የሚታየው ግንኙነትና ትስስር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለውና ኅብረ ብሔራዊ የሆነ ነው። በመከባባርና በመቻቻል የተመሠረተዉን የሕዝቦች ትስስርም አጠናክሮታል። ይህ ዘመን ተሻጋሪ ዘርፈ ብዙ የሕዝቦች መስተጋብር ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት የራሱ የሆነ አሰተዋጽኦ ከማበርከትም አልፎ ለአገር ግንባታው ሂደትም ትልቅ ግብአት ሊሆን ችሏል። አዲስ አበባ ከተማና የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቶች ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ከተመሠረተችበት ከ 1847 ዓ . ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አራት ሕገ መንግሥቶቸና አንድ የሽግግር ጊዜ ቻርተር ሊኖራት ችሏል። የ 1923 ዓ . ም እና የ 1948 ዓ . ም ሕገ መንግሥቶች አዲስ አበባን በተመለከተ የንጉሠ ነገሥቱ መቀመጫ፣ የአገሪቱ ዋና ከተማ፣ ከየጠቅላይ ግዛቱ የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች መኖሪያ እና የመንግሥት የፖለቲካ ማዕከል አድርገው በመደንገግ የከተማዋን ኅብረ ብሔራዊነትና ብዝኃነት አጠናክረውታል። ሰነዶቹ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አዲስ አበባ ለአገር ግንባታ የምትጫወተውን ሚናም እንዲጎለብት አድርገዋል :: የ 1979 ዓ . ም የኢሕዴሪ ሕገ መንግሥት አዲስ አበባን የአገሪቱ ዋና ከተማ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና የዕውቀት ማዕከል አድርጎ በመደንገግ ከሌሎች የክፍለ ሀገር ከተሞች አንፃር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የባህል መሪነቷን ከፍ ከማድረጉም ባሻገር ለአገር ግንባታ የምትጫወተውን ሚና ጨምሮላታል :: ይህም የሕዝቦች መዳረሻ እንድትሆን ስላደረጋት ኅብረ ብሔራዊ መሠረቷን በማጠናከሩ የሕዝቦች ትስስርና አብሮነትን አዳብሯል :: የ 1983 ዓ . ም . የሽግግር መንግሥቱ ቻርተርና የ 1987 ዓ . ም . የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ( በተለይም የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ 4 ፣ አንቀፅ 49 ፣ ቁ .1) አዲስ አበባን የአገሪቱ ዋና መዲና አድርጎ ደንግጓል :: ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፓርላማው አባላት ከየክልላቸዉ መጥተው በከተማዋ መኖራቸው የአዲስ አበባን ሥልጣን፣ አቅምና ተጽእኖ በመጨመር ከተማዋ በአገር ግንባታው የምትጫወተውን ሚና ከፍ አድርጎታል። በአጠቃላይ አራቱም የአገሪቷ ዐቢይ የመተዳደሪያ ሰነዶች ( ሕገ መንግሥቶችና ቻርተሩ ) ምንም እንኳ የተለያየ ፍልስፍና እና ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ ቢሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ለአገር ግንባታው የምትጫወተዉን ሚና አሳድገውታል :: አራቱም ሰነዶች ከተማዋ የአገራችን የፖለቲካ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የሃይማኖት እና የወታደራዊ ማዕከል አድርገው መደንገጋቸው የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መዳረሻ እንድትሆን አመቺ አጋጣሚን ፈጥረውላታል። እነዚህ ገዢ ሰነዶች የፈጠሩላት መልካም አጋጣሚዎችም የአዲስ አበባን ኅብረ ብሔራዊነት የበለጠ እንዲጎላ አድርጎታል :: አዎንታዊ የአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮዎችና የሌሎች ከተሞች ጭብጦች አዲስ አበባ ከሌሎች የዓለም ከተሞች ጋር ስትነጻጸር ብዙ አዎንታዊ ተሞክሮዎች አሏት :: የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ስትቆረቆር በቅኝ ገዢዎች እዝና ተጽእኖ ሳይሆን በአገር በቀል ዕውቀት፣ ውሳኔና፣ ምርጫ ነው። ይህም አገራዊ እሴቶችን ጠብቆ ከማቆየትና ከማንጸባረቅ አንጻር ከተማዋን ከየትኛውም የአፍሪካ፣ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ አገራት ለየት ያደርጋታል። አዲስ አበባ ከአብዛኞቹ የዓለም ከተሞች በተለየ መንገድ ደሃና ሀብታም፣ ሙስሊምና ክርስቲያን በአንድ መንደር ተጎራብቶ የሚኖርባት፣ በአንድ ጎዳና የሚጓዝባት፣ አብሮ የሚያመልክባት፣ አብሮ በእቁብ፣ በእድር፣ በቀብር፣ በንግሥ፣ በሠርግ እና በለቅሶ እና በመሳሰሉት አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተቋማትና ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚሳተፍባት የመቻቻል ከተማ ስለመሆኗ ብዙዎች የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። ከብዙ የዓለም ከተሞች ጋር ስትነፃፀር አዲስ አበባ የሰላምና የመቻቻል ከተማ እንደሆነች ብዙዎች ይስማማሉ :: ዜጎች ያለ ስጋት ወጥተው የሚገቡባት፣ ነግደው የሚያተርፉባት፣ ሠርተው የሚኖሩባት ከተማ ናት። ዜጎች ውድ ጌጣ ጌጦችን ለብሰው ያለስጋት በጎዳና ላይ የሚንቀሳቀሱባት፣ የውድ ጌጣጌጥ ነጋዴዎች ( የወርቅና የብር ) ያለምንም ስጋት በመስታወት ከልለውና ዘርግተው የሚሸጡባት፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት ( ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ት / ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ) በመለስተኛ ጥበቃ ደህንነታቸው ተጠብቆ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑባት ከተማ ናት :: እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትላልቅ ሕዝባዊ በዓላትን ሰላማዊ በሆነ መልኩ በማስተናገድ ዓለም አቀፍ ዝናንና አድናቆትን ለማግኘት የቻሉ ሁለት ከተሞች አዲስ አበባና ሪዮ ዴጃኔሮ ናቸዉ፤ በመጀመሪያው ደመራ፣ ጥምቀትና ዒድ፣ በሁለተኛው ካርኒቫል። አዲስ አበባ የብዙዎች ማኩረፊያ፣ መሸሺያ፣ ተስፋና ህልም ናት። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ዘመድ የሌለው የክልል ተወላጅ እጅግ ጥቂት ነው :: ለአቤቱታ፣ ለንግድ፣ ለትምህርት፣ ለሕክምና፣ ለሥራ ፍለጋ፣ ለስፖርት ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ሰው መጀመሪያ ዘመዱ ቤት አርፎ ነው ጉዳዩን የሚያስፈጽመው :: የአፍሪካ ገበያዎች ለተግባቦትና ለፖለቲካ መስተጋብር፤ ከአንዳንድ ጥንታዊ 5 የኢትዮጵያ ገበያዎች የተገኙ ዕይታዎች * ዶ / ር ግርማ ነጋሽ የዚሁ ጽሑፍ ዐቢይ ትኩረት የአፍሪካ፣ በተለይም የኢትዮጵያ፣ ገበያዎች ማኅበራዊና መስተጋብራዊ ጠቀሜታ ማሳየት ሆኖ የጥናቱ የትንተና ማዕከል ደግሞ የገበያ ቦታዎች ( market places ) ናቸው። የጥናቱ ዋና ዓላማ ከሀገራዊ ተቋሞቻችን፣ በዚህ ጥናት መሠረት ደግሞ ከገበያ ቦታዎቻችን፣ የምናገኛቸውን የአብሮነት፣ የኅብረ ብሔራዊነት፣የመደጋገፍና የመቻቻል ተሞክሮዎች / ትሩፋቶች መለየት፣ ማሳየትና ማድነቅ ነው። ለዚህም ስል አንዳንድ የተመረጡ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ገበያዎችን፣ ለምሳሌ ባቲን፣ ሰንበቴንና አልዩ አምባን ከሰሜን፤ ሼሎ፤ ሻመና፤ አሌሉ ሻሸመኔ እና አላባን የመሳሰሉ ገበያዎችን ከደቡብ በመጠቀም፤ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ አገራዊ ተቋሞቻችን ለአሁኑ አኗኗራችንና ለምናደራጃቸው ሥርዓቶች የሚበጁ በጎ አሰተምህሮዎችን ( insights ) ነቅሶ ማሳየትን መርጫለሁ። እንደ መንደርደሪያ ገበያን የተመለከቱ የሌሎች ተመራማሪዎች ጥናቶች ላይ መጠነኛ ዳሰሳ ማድረግ ጠቃሚ ነው። ብዙዎቹ የገበያ ትርጉሞች ከኢኮኖሚያዊ ተግባሩ / አገልግሎቱ ጋር የሚያያዙ ናቸው። በዚህ ጽሑፍ አጠቃቀም የገበያ ቦታ ( market place ) ማለት ገዢና ሻጭ የሚሸጧቸውንም ሆነ የሚገዟቸውን ነገሮች የሚለዋወጡበት በአንድ ወይም ከዛ በበለጠ ቀን በአንድ በተወሰነ ቦታ የሚቆም ወይም የሚገኝ ተቋም ነው። በአፍሪካ፣በተለይ የናይጄሪያ፣ የጋና፣ የዳሆሜ ገበያዎች በተለይ በአንትሮፖሎጂሰቶች በተሻለ ደረጃ ተጠንተዋል። በአትየጵያም በተለይ በታሪክ ተመራማሪዎች የተጠኑ ገበያን የተመለከቱ የተወሰኑ ጽሑፎችን መጥቀስ ይቻላል። እንዲሁም ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በዝነኛ ግጥሙ መርካቶን ሕያው አድርጓታል። የብዙዎቹ ጥናቶች ትኩረት በገብያዎች የተለያዩ ባህሪያት፣ አደረጃጃት፣ ቦታና ቀን አሰያየም እና ኢኪኖሚያዊ ሚና ላይ ነው። ከዚያም አልፎ መገናኛ፣ መጨዋወቻ፤ መዝናኛና መተጫጫን የመሳሰሉ የማኅበራዊ ግንኙነት ሚናቸውን የሚዳስሱና የሚተነትኑም አሉ። አንዳንድ ጥናቶች የኢትዮጵያ ከተሞች ባብዛኛው ኅብረ ብሔራዊ ( cosmopolitan space ) መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እንዲያውም የብዙ ከተሞች መነሻ ከገበያነት ነው ይላሉ :: እኔ ደግሞ የዚህን እውነትነት በማስረገጥ ሻሸመኔን፣ እንዲሁም ( ስማቸውን በማየት ) እነሐሙሲትን፣ ማክሰኚትን እና ዐርብ ገበያን በአብነት መውሰድ ይቻላል እላለሁ። እንዲያውም የኢትዮጵያ ከተሞች የኅበረ ብሔራዊነት ባህሪያቸውን የወረሱት / የተማሩት ከገበያዎቻችን ነው እላለሁ። የጥናቱ ዋና ማጠንጠኛ ሐሳብ ደግሞ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ዓይነቶቹ ክፍት የገበያ ቦታዎች፣ , በምዕራቡ ዓለም ከተለመዱት እንደ ሱፕር ማርኬትና ሀይፐር ማርኬት ከመሳሰሉ የገበያ ዓይነቶችና የገበያ ሥርዓቶች በተለየ፣ ለብዝሀ ባህል ሀገሮች፣ ማንነቶችና ልዩነቶች እንደተጠበቁ የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት የሆኑ ተቋማት ናቸው የሚል ነው። በተለይም ደግሞ አንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኅብረ ብሔር ሀገራት፣ ሆን ተብሎም ሆነ በአጋጣሚ በሁለትና ከዚያ በላይ ብሔረ ሰቦች አዋሳኝ ላይ በቆሙ የድንበር ገበያዎች ምክንያት፣ በተዋሳኞቹ ወይም ከዚያም ራቅ ካለ ቦታ በሚመጡ ገበያተኞች መካከል ዘመን የተሻገረ የማያቋርጥ የአብሮነት፣ የመደጋጋፍና የመቻቻል ባህልና ልምድ ይቀጥል ዘንድ ያስቻሉ የራሳችን ተቋማት መሆናቸውን ማወደስና ማጉላት ያሰፈልጋል ባይ ነኝ። ከዚህ በታች የማነሳቸው ገበያዎች እነዚህን በዝርዝር የማነሳቸውን የትኩረት ነጥቦች እንደማሳያ የምጠቀምባቸው እንጂ የእያንዳንዳቸው የተሟላ ታሪክና ባህሪያት ትንተና እንዳልሆነ ላሳስብ እወዳለሁ። የባቲ ገበያ በቀድሞው ወሎ ክ / ሀገር፣ በአሁኑ የአማራ ክልላዊ መንግሥት፣ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምሥራቅ 437 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ነው። በዚህ ጥናት እንዲካተት የመረጥኩበት ምክንያት በዚህ ጥናት ከሚዳሰሰው ዘመን ቀደም ብሎ ጀምሮ ዐረቦችንና ጣሊያኖችን ጨምሮ ሦስት ዋና ዋና ብሔረ ሰቦች፣ ማለትም አፋሮች፣ ኦሮሞዎችና አማሮች፣ የሚገናኙበት መናኸሪያ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ነው። * የተጠቀሱት ቀናት በሙሉ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር መሆኑ ይታወቅ። የዝነኛው የባቲ ሰኞ ገበያ መነሻ በ 1880 ዎቹ መቆም እንደጀመረ የሚነገርለት የገነዳ ዳዬ ገበያ ነው። ባቲ የብዙ ብሔረሰቦች አዋሳኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በተለያየ ዘመን የአሰተዳደር ማዕከልም የነበረ ነው። የሰንበቴ ገበያ ይህ ገበያ በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር፣ በአሁኑ አማራ ክልላዊ መንግሥት የኦሮምያ ልዩ ዞን ውስጥ፣ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 245 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ ጥንታዊ ገበያ ነው። ከ 18 ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ ጸንቶ የቆየ ገበያ ከመሆኑም በላይ አራት ዋና ዋና ብሔረሰቦችን ( ማለትም አማራን፣ ኦሮሞን፣ አርጎባን እና አፋርን ) የሚያገናኝ መናኸሪያ ነው። ከልጅ ኢያሱ ተደጋጋሚ ጉብኝትና ለየት ያለ ቁርኝት ጋር ተያይዞም ከ 1912 ጀምሮ የኢያሱን የፈረስ ስም (“ አባ ጤና ”) በመውሰድ “ ጤናዬ ” እየተባለ ሲጠራም ቆይቷል። ሼሎ ገበያ፣ ሻመና ገበያ፣ ሰንበታ ገበያ፣ ጋዮ ገበያ፣ ሃጨቀቴ ገበያና አዳሬ ገበያ ከሻመና በስተቀር እነዚህ ገበያዎች በሙሉ ከጣልያን ጊዜ ቀደም ብለው ለረጅም ጊዜ በገበያነት ያገለግሉ የነበሩ ናቸው። ሁሉም በተለያዩ ብሔረ ሰቦች ድንበር ላይ የሚገኙ የድንበር ላይ ገበያ ( border markets ) ናቸው። ቢያንስ የሦስት ማኅበረሰቦች ( የሲዳማ፣ አርሲና ወላይታ ) ቋሚ መገናኛና መናኸሪያ ናቸው። ሻመና ሕዝባዊ ይህ ገበያ በ 1960 የተመሠረተ፣ ከሰፈራ (settlement) ተነስቶ ወደ ገበያነት አድጎ ከተማ የሆነ ነው። ሆን ተብሎና ታስቦበት በአርሲ፣ በሲዳማና የወላይታ ሕዝቦች አዋሳኝ ድንበር ላይ የቆመ ገበያ ነበር። አካባቢው በታሪኩ ግጭት የሚበዛበት ( c onflict-prone) ስለነበረ፤ ያንን ለማርገብ በቀድሞው ሕዝባዊ ኑሮ እድገት ታቅዶ የተመሠረተ ሰፈራና ገበያ ነበር። አሌሉ አሌሉ ከሻሸመኔ በስተሰሜን ምዕራብ 13 ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል። ከ 19 ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የብዙ ሲራራ ( ካራቫን ) የንግድ መስመሮች የሚተላለፉበትና በርካታ የአካባቢው ብሔረሰቦችን ( አርሲ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ፣ ጉራጌ ) ሲያሰተናግድ የኖረ መናኸሪያ ነበር። በኋላም የነፍጠኛ ሠፈራ ( settlement ) የነበረ ነው። ከ 1915 ጀምሮ አሌሉ የገበያ መናኸሪያነቱንም ሆነ ዋና የነፍጠኛ ሰፈርነቱን ለሻሸመኔ አሰረክቧል። ሻሻመኔ ሻሸመኔ ከአሌሉ በላቀ ሁኔታ እጅግ በርካታ ብሔረ ሰቦች የሚገናኙበት ገበያ የነበረ ከመሆኑም አልፎ፤ ወደ ሼክ ሁሴን የሚያመሩ የሃይማኖት ተጓዦች ማረፊያም ነበር። ብዙ ጸሐፊዎች የሻሸመኔ ከተማ ምሥረታን ከገበያነቱና ከንግድ መናኸሪያነቱ ጋር ያያይዙታል። በአንፃሩ፣ ለሻሸመኔ መቆርቆር ዋናው ምክንያት የነፍጠኛ መስፈሪያ መሆኑ ነው የሚሉም አልታጡም። የአላባ ገበያ ይህ ገበያ በተለይ በ 19 ኛው መቶ ዓመት ማለፊያ፣ ማረፊያና መናኸሪያ ገበያ እነደነበረ የመረጃ ምንጮች ያሳያሉ። በአመቺ አማካይነቱ እና የተሻለ የጸጥታ ሁኔታም ስለነበረው ከአሌሉ የበለጠ ገበያተኛ የሚሄድበት ነበር ይባላል። ከ 1915 ጀምሮ በሻሸመኔ መነሳትና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የገበያ ተመራጭነቱ እየተዳከመ ሄዷል። ከነዚህ የድንበር ገበያዎች እናስተውላቸው ዘንድ ነቅሼ ያወጣኋቸውን ዘመን ተሻጋሪና የተፈተኑ ማኅበራዊ ልምዶች ከዚህ እነደሚከተለው አቀርባለሁ። 1 ኛ ) በዚህ ጥናት ላይ ያየናቸውና ወደፊትም ሊጠኑ የሚገባቸው ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው የኢትዮጵያ ገበያዎች አዋሐጅና ደፍጣጭ ሳይሆኑ ቀላቃይ ተቋማት ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ ገበያዎች በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም ሆነ በኢትዮጵያ በእርግጥም የተለያየ ማንንት ያላቸው ሰዎች ማንነታቸውንም ሆነ ዕቃቸውን ይዘው ገብተው አካፍለው / ገዝተው ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንደጠበቁ ይወጣሉ። አንዳንድ ሥርዓቶች የሚተቹበት መደፍጠጥና ማዋሐድ ( homogenization, acculturation ) የሚሰኙ የትላልቅ ብሔሮች ጫናዎች የማይኖሩባቸው ናቸው። ስለዚህም አማራጭ የፌደራሊዝም ሞዴል ስናስብ ምልከታ ( insight ) ልናገኝባቸው እንችል ይሆን የሚል ጥያቄን ያጭራሉ። 2 ኛ ) በአጠቃላይ የአፍሪካ የገበያ ቦታዎች የቱንም ያሀል የማይመቹ ቦታዎች ቢሆኑም ( የንጽሕና ጉድለት ያላቸው፣ ማስነጠሱ፣ የተለያዩ ጠረኖች፣ መገፋፋቱና መተሻሸቱ ) ሰዎች ትኅትናን የመሰሉ መልካም ሥነ ምግባሮችን የሚለማመዱበት መድረክ ነው። በዚህ ጥናት ትኩረት የተደረገባቸው ገበያዎች ደግሞ በተለይ ለአብሮ መኖር አስፈላጊ፣ ግን ደግሞ አሁን አሁን እየቸገረን የመጣውን የመቻቻልና የመታገስ ( tolerance ) መልካም ባሕሪ ማዳበርን ይጠይቃሉ። 3 ኛ ) አካታችነት። እነዚህ ገበያዎች ብቸኛ ባለቤት የላቸውም። የሁሉም ናቸው። ይህ ገበያ የኛ ስለሆነ አትምጡብን ወይም ደግሞ ውጡልን ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም። በአስተዳደር አከላለልም ሆነ በጂኦግራፊ አቀማመጥ የትኛውም ክልል ውስጥ ቢገኙ ሁሉም ተጠቃሚዎች ገበያችን እያሉ ይጠሯቸዋል። 4 ኛ ) የቋንቋ ሽግግር። በገበያዎች፣ በተለይም የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚያዘወትሯቸው ገበያዎች፣ ብዝሀ ቋንቋነት የግድ ብቻ ሳይሆን የተለመደም ነው። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው። ይሁን እንጂ ይህ ከገበያዎች፣ በተለይም በዚህ ጥናት እንደተዳሰሱት ካሉ የገበያ ዓይነቶች፣ የሚገኝ ትሩፋት መሆኑ ትኩረት አላገኘም፤ አላወደስነውም። እንዲህ ዓይነቱ የቋንቋና የባህል ሽግግር ብዙ አንድምታዎች አሉት። ስለ ሌሎች ያለንን የተዛባ አመለካከት ( prejudice ) ይቀርፋል፤ የእርስ በርስ ተግባቦትንም ይጨምራል። VI. ማንነትና የፖለቲካ ሥልጣን በኢትዮጵያ የሕዝቦች መስተጋብርና ትስስር ልምድ የኦሮሞ ሕዝብን የሚመለከቱ አንዳንድ ጉዳዮች ዶ / ር አውግቸው አማረ አጎናፍር በኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ታሪክ ምርምር አንጓዎች ውስጥ የመስተጋብርና ትስስር ታሪክ አንዱ ነው። የታሪክ መረጃዎችን በሳይንሳዊና ሙያዊ መንገድ የተገነዘቡና የተጠቀሙ ምሁራን የሚያስረዱት የኢትዮጵያውያን ታሪክ የግንኙነት፣ የመሰናሰን እና የመስተጋብር መሆኑን ነው። የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች የፈጠሩት መሰናሰን ኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሠረት ላለው አሰባሳቢ ማንነት አስረጂ መሆኑን ነው። ይህ የልውውጥ ታሪክ ለረጅም ዘመናት የተደረገ፣ የተለያዩ ተዋናዮች የተሳተፉበትና እጅግ ውስብስብ መልኮች፣ ሂደቶችና ውጤቶች ያሉት ነው። የአስተዳደር መዋቅሮችን በመዘርጋት ዘለግ ያለ የመንግሥት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ፣ የተመዘገበ፣ የግዛት አንድነትን እና የሕዝብን ህልውና የጠበቀና ያስቀጠለ የመስተጋብር ታሪክ አላት። የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህል፣ እምነት፣ አካባቢ፣ እና የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ሕዝቦች በሥርዓት በማስተዳደርና በማስተሳሰር በሺህ ዓመታት የሚቆጠር ታሪክ አላት። የመስተጋብርና ትስስር ታሪክን ለማጥናት የታሪክ ምርምሩን ሳይንሳዊ ወዝ እና ይዘት የሚሰጡና የትንተና፣ ትርጓሜንና ብያኔን አቅም የሚያዳብሩ ንድፈ ሐሳባዊ ውይይቶችንና ክርክሮችን መረዳት አሁን ያሉበትን የሙግት ደረጃ ለመለየት ይረዳል። በኅብረተሰብ እና ባህል ጥናት ዘለግ ላሉ ዓመታት የተደረጉ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶች እንደሚያስረዱት የሕዝቦችና የባህላቸው ትስስር ዘርፈ ብዙ ሂደቶችንና ውጤቶችን ያስከትላል። አንዱ ሕዝብ የሌላውን ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት የመውረስ፣ የመለዋወጥ፣ የግንኙነት ውጤት የሆነ የባህልና የደም ቅልቅል መፈጠር፣ አንዱ በሌላው ውስጥ የመዋጥ እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። በእርግጥ ንድፈ ሐሳባዊ ክርክሮቹን በዝርዝር ማቅረብ የማይቻል መሆኑ እሙን ነው። ይሁንና በዚህ ጽሑፍ የሚሞከረው የታሪክ ምሁራን ሳይንሳዊ ምርምሮች በሌሎች የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎች የበለፀጉ የንድፈ ሐሳብ ግኝቶችን እንደ ግብአት ሊጠቀሙ ይገባል የሚለውን ዘመኑን የዋጀ ምልከታ ለማጋራት ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ የመስተጋብርና ግንኙነት ታሪክ በሁለት ግዙፍ ታሪካዊ ኩነቶች ይገለፃል። የመጀመሪያው መንግሥት ወደ ሕዝብ ሰብሮ መግባት የሚፈጠረው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሕዝብ ወደ ነባሩ የመንግሥት ግዛት፤ ሥርዓትና ተቋማት ሰብሮ መግባት ነው። የግዛት ማስፋፋት፣ ሀገር ማቅናት ወይም መቆርቆር እንዲሁም የሕዝቦች እንቅስቃሴን ከግምት ማስገባት እጅግ ውስብስብ የሆኑትን የታሪካችን ምዕራፎች አሰባሳቢ መልክ ይሰጣል። የትስስር ሂደቶችን ለመተለም፤ ሥርዓት ለማበጀትና ተቋማዊ ለማድረግ ጉልህ ሚና የነበራቸው የተለያዩ ግን የተቆራኙ ዘውዳዊ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ወ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ወታደራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አደረጃጀቶችና ስልቶች ነበሩ። እነዚህ የግንኙነት መረቦች መንግሥት መር የሆኑ፣ በየተቋማቱ የሚከወኑትን ሕዝብንና ማንነቶችን የማጎዳኘት አካሂዶችን እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማትና በማኅበረሰቡ የሚፈጠሩና የሚመሩ ሕዝባዊ የመስተጋብር ማእቀፎችን ያጠቃልላሉ። ከመንግሥትም ሆነ ከሕዝቡ የሚፈልቁ የትስስር ድሮች ዓላማቸው በተለዋዋጩ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ሊያስባስቡ የሚችሉ የመስተጋብር መረቦችን በመዘርጋት የጋራ ማንነትን እና የአንድ ሀገር ልጅነትን ማዕከል ያደረገ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነበር። በዚህ ረገድ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና የማኅበረሰቡ ሀገር በቀል አደረጃጀቶች በግልና በትብብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያን የትስስር ታሪክ በፓሊቲካ ልሂቃን፣ ካህናት፣ የእስልምና መምህራን፣ በነጋዴው፣ በወታደሩ፣ እና በማኅበረሰቡ በተፈጠሩ ሥርዓታዊ የግኙነት መረቦች የተደረጉ መስተጋብሮች ውጤት ያደርገዋል። የሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ንጉሠ ነገሥታት መንግሥት እንዲረጋ፣ ሥልጣናቸው እንዲፀና እና በቀውስ እንዳይታመስ በሕዝብና ባህል መስተጋብር ላይ አጥብቀው ይሠሩበት ነበር። ዙፋኑ የሕዝብና የግዛት የበላይ ጠባቂ፣ የአንድነትና የሰላም ምልክት ተደርጎ ይታያል። አፄአዊ ሥርዓቱ ሕዝብን የማጎዳኘትና የመጠበቅ ኃላፊነትን እንዲወጣ ይጠበቅበታል። ወደ ሥልጣን የሚመጣው ንጉሠ ነገሥት ጤናማና ወታደራዊ ልምምድ ያለው መሆኑ ግዛትን ለማስፋፋት፣ በግዛተ አፄው የተጠቃለሉ ሕዝቦችንና ግዛቶችን አንድነት ማስጠበቅ ለመቻሉ ዋነኛ መመዘኛም ነበር። ንጉሠ ነገሥታቱ በአመዛኙ የባህልና የሃይማኖትን ልዩነቶችን የሚገነዘቡ ሲሆኑ የመጠቅለልና የማቻቻል ዘዴን አፈራርቀው ይተገብሩ ነበር። ባቀኑት ግዛት ውስጥ የሚኖረውንም ሕዝብ ሆነ ሊያቀኑት በሚፈልጉት ግዛት ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ ‹‹ ሕዝቤ ›› ብለው ይጠሩታል። የባህል፤ የቋንቋ፤ የአካባቢና የሃይማኖት ልዩነትን ተንተርሰው ሕዝብን አያበላልጡም፤ ከአንዱ ወገን ጋር አያብሩም። መርጠው አይወዱም፤ በጠላትነትም አይፈርጁም። ይሁንና በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች እንደታየው በሚተረከው መጠን ሕዝቡን ከአደጋ ሲጠብቁት አልታየም። የጥቅም ግጭት እና የሥልጣን ፉክክር በወለደው ሽኩቻ የተነሳ የልሂቃኑ ግጭት ለሕዝቡ ተርፎ ሰላማዊ ግንኙነቶች ተረብሸዋል። ግዛተ አፄው በሰላም እጦት ያልታመሰበት ጊዜ አልነበረም ለማለት ያስደፍራል። ፖለቲካዊ / ርዕዮተ ዓለማዊ የመስተጋብር መረቦች መልክ መያዝ የጀመሩት ከሰለሞናውያን መምጣት ጋር ተያይዞ ነው። የዛጉዌ ሥርወ መንግሥትን በፕሮፓጋንዳና በኃይል የረቱት የ 13 ኛው መቶ ዓመትየኢትዮጵያ መሪዎች ለሚመሠርቱት ‹‹ ሕጋዊ ›› መንግሥት፣ ለሚመሩት ሕዝብና ሀገር መነሻ ተረክ ይዘው መምጣታቸው የተለየ የመንግሥትና ተቋማዊ ሥርዓት ዝርጋታ ዕውቀታቸውን ያሳያል። ይህንንም ዕውቀት በክብረ ነገሥት የመቅረፅና ተረኩን የማባዛት ተግባር ከ 13 ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ ተሠርቶበታል። ክብረ ነገሥት ስለ ሰለሞናዊያን ሀገር መሪነት ቅቡልነት፣ የተመሠረተው ሥርወ መንግሥትም ግዛትን የማስፋፋትንና የሃይማኖትና የባህል ብዝኀነትን በአንድ ጣሪያ ስር የማስተዳደርና የማስተሳሰር ሕጋዊ መሰረትን ይሰጣቸዋል። ሕዝቡን በተመለከተም በኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነት ላይ ያተኩራል። የማንነት ልዩነትን እንደ ፖለቲካዊ ሀብት አልቆጠሩትም። በግዛት መስፋፋት ወቅት የተፈጠሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ተፃራሪ ትርክቶች ወቅቱ የፈጠራቸው ሕዝብን ከዓላማው ጀርባ የማሰባሰቢያ ስልቶች ነበሩ። መታየትም ያለባቸው በወቅቱ ከነበረው ሁለንተናዊ ግንዛቤ በመነሳት ነው። በመሆኑም በሕዝብና ልሂቃን መስተጋብር የተነሳ ከብዝሀ ማንነት የተውጣጡ ጉልሃን ከፖለቲካዊና ወታደራዊ መሪነት እስከ ንጉሠ ነገሥትነት ደርሰዋል። ኢትዮጵያም የእስራኤል ነገዶች የፈለሱበትና ዘራቸውን ከንጉሥ ሰለሞን የሚመዙ መሪዎች የሚመሯት የተመረጠች ምድር ተደርጋ ተስላለች። ማርና ወተት የሚፈስባት የተስፋይቱ ምድር ሁሉም ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለሚጠቃለል ግዛትና ሕዝብ የተሰጠ ምስል ነው። እሳቤዎችንና የተቋማቱ አደረጃጀት ትርክት ከንግሥተ ሳባ እና ንጉሥ ሰለሞን ትርክት የመምዘዝ ዝንባሌ እየተሠራበት ዕውቀት ይሆን ዘንድ በቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት፣ በሥነ ጽሑፍና በሥነ ጥበብ ሊስፋፋ ችሏል። ወታደራዊ አደረጃቶች የግንኙነት መረብ መሆን የጀመሩት ከአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ። ይሁንና መሠረታዊ ለውጥ መስተናገድ የጀመረው ከ ‹‹ ሰለሞናውያን ›› መምጣት ( ማለትም ከ 13 ኛው መቶ ዓመት ) በኋላ ነው። የታሪክ ሰነዶች፣ በተለይም ዜና መዋዕሎች፣ ገድላት፣ የአውሮፓውያን ካቶሊክ ሚሲዮኖች ጥናቶችና ሌሎች ሳይንሳዊ የታሪክ ምርምሮች እንደሚያሳዩት፤ ከ 14 ኛዉ መቶ ዓመት ጀምሮ የጨዋ ሠራዊት ግንባታ ተከናውኗል። በዚህ ዘመንም የነበረው የጨዋ ሠራዊት ሦስት መሠረታዊ ለውጦችን አስተናግዷል። ከብዝሀ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና የትውልድ ቦታ የተውጣጣ የጨዋ ሠራዊት መገንባት፣ አዲስ በተቆረቆሩ ግዛቶችና ድንበሮች የጨዋ ሠራዊት መስፈሩ፣ ከሰፈረበት ማኅበረሰብ ጋር መተሳሰሩ እና የእነዚህ ውጤት የሆነዉ የትስስር ሂደቱ እየሰፋ የመጣው የሀገሪቷ ዳር ድንበርና ግዛት መስፋፋት ውጤቶች ናቸው። ግዛትን በማስፋፋት ላይ የተመሠረተ የመንግሥት አቅም እና የጨዋ ሠራዊቱ የአስተዳደራዊ ሥርዓቱ አስፈፃሚ መሆን ርዕዮተ ዓለም፣ ርስተ ጉልት፣ ክርስትና፣ ባህልና እና የመንግሥትን ቋንቋ የማስፋፋት ሚና እንዲኖረው አስችሏል። የክርስትናና እስልምና መስፋፋት የአካባቢ ተወላጅነት፣ የቋንቋ፣ የብሔር እና የባህል ልዩነትን ለተሻገረ አሰባሳቢ ሃይማኖታዊ ማንነት መፈጠር ዋነኛ ምክንያት ነው። በሃይማኖታዊ ድርጊቶችም ውስጥ ሀገር በቀል እምነቶችና ባህሎች ተሰናስነው ሲቀጥሉ የባህላዊ እምነቶችና ድርጊቶች፣ ክርስትና እና እስልምናን ያቆራኘ ባህል በልፅጓል። በሂደትም ፉክክርን የሻሩ፣ በትብብር ላይ የተመሠረቱ፣ ሃይማኖት ተሻጋሪ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ደማዊ ትስስሮች ተፈጥረው ያለማቋረጥ ቀጥለዋል። ክርስቲያኑ እና ሙስሊሙ ማኅበረሰብም ከኢትዮጵያዊነት መሠረት ጋር የሚያስተሳስሩ ተረኮችና ማኅበራዊ አደረጃጀቶችን ጠብቆ አቆይቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ ሁኔታው በእጅጉ የሚመሳሰል ሲሆን ይህም ከምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብሩ ውጪ ሊቃኝ አይችልም። የታሪክ ድርሳናት በጥቅሉ የሚሰጡት ምስል እንደሚያሳየው፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ዘርፈ ብዙ መልኮች እንዳሉትና ከሌሎች የትስስር ክሮች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነው። ከብት አርቢና ተንቀሳቃሽ ማኅበረሰቦች በመሬት ስሪት ሥርዓት መሠረት መስፈርና የመሬት ባለቤት መሆን፤ በቋሚነት የኑሮ ሁኔታ በሰፈሩ ማኅበረሰቦች መካከል የኢኮኖሚ ትስስር መፈጠር፤ የጦር ካምፖች፣ ከተማዎች፣ ገበያዎች፣ የንግድ መስመሮች ወዘተ ለኢኮኖሚ ትስስርና ለባህል፣ ሃይማኖትና የምጣኔ ሐሳቦች ልውውጥ ምክንያት መሆን፤ እንዲሁም ንዑስ ማንነቶችን የተሻገሩ ማኅበረሰባዊ የሀብት ማፍሪያ፤ ማካበቻና ማስተዳደሪያ ባህላዊ ተቋሞች ማደግ ዋና ዋናዎቹ ዐምዶች ናቸው። ይህን የመስተጋብርና የትስስር ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተለት የ 16 ኛው መቶ ዓመት የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ የተከናወነበት ሂደትና ያስከተለው ውጤት ነው። ይህ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ ለመረዳትና ለመተንተን ብሎም ብያኔ ለመስጠት ከፍተኛ ምርምር የሚያስፈልገው እጅግ ወሳኝ የሆነ የታሪክ እጥፋት ነው። በክፍለ ዘመኑ ከተስተናገዱት ዐበይት ክስተቶች አንዱ የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ነው። ይህም በሁለት መልኮች የተካሄደ ነው። አንደኛው ሰላማዊ ግንኙነቶችን የያዘ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አደጋ አዘል መስፋፋቶችን ያካተተ ነው። በረጅም ጊዜ ሰሌዳ ውጤቱ ሲቃኝም ሰላማዊ መስተጋብሮች ሲቀጥሉ ጠላትነትን ያፈሩት ግንኙነቶች በሂደት ተለሳልሰዋል። የሕዝብ መስፋፋቱን ተከትሎ የተከሰተው ወሳኝ የታሪክ ክፍል የኦሮሞ ሕዝብ ሰፈራ ነው። ከአፄ ሰርፀ ድንግል ( እ . ኤ . አ 15631597) ዘመነ መንግሥት ማብቂያ ጀምሮ የኦሮሞ ሕዝብ አንድም በንጉሠ ነገሥቱ ይሁንታ፣ አንድም በኃይል በተደረጉ መስፋፋቶች የመሬት ባለቤት ሊሆን ችሏል። ከአፄ ሱስንዮስ የጀመረው ኦሮሞዎችን በለም እና ገዢ መሬቶች ላይ ሳይቀር የማስፈር ዕቅድ በስፋት የቀጠለ የሕዝቡን እንቅስቃሴ የመግቻ እና ሰላማዊ መስተጋብርን የመክፈቻ አንድ ብልሃት ነበር። ከ 17 ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ በተደረገው የኦሮሞ አሰፋፈር የተነሳ የባህል፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ትስስሮች በቋሚነት ቀጥለው ኦሮሞ ክርስትናን፤ እስልምናን እና ቋንቋን ከተቀላቀለው ማኅበረሰብ ተቀብሎ በተራው ቋንቋውንን እና ባህላዊ መገለጫዎቹን ሰጥቷል። ከዚህም የተነሳ የኦሮሞ ሕዝብ ከሰፈረበት ማኅበረሰብ ጋር ለዘመናት በባህል እና በደም መቀላቀል፣ በሁሉም ወገን የስም ለውጦችና ቅልቅሎች፣ የኦሮሞ ሕዝብ የርስት ጉልት ሥርዓትን መቀላቀልና የኑሮ ሁኔታ መሻሻል፤ የኦሮሞ ባህላዊ ተቋማት መዳከምን የመሳሰሉት ግዙፍ ለውጦች ተከስተዋል። በዚህም በኦሮሞ ሕዝብና በተቀላቀላቸው ሕዝቦች ላይ የማንነትና የሚና ለውጦች ተስተናግደዋል። ሶስተኛው የኦሮሞዎች የመስተጋብር ምዕራፍ ከሰፈራ ወደ መንግሥት ሥርዓትና ተቋማት የተደረገው ስርገት ነው። ውትድርና እና የጋብቻ ትስስር ሁለቱ ዋና የመስረጊያ በሮቹ ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮሞ ወታደሮችን ወደ ኢትዮጵያ የጨዋ ሠራዊት የቀላቀለው አፄ ሠርፀ ድንግል ነው። የኦሮሞ ተዋጊዎች ቱርክን እንዲዋጉ ተልእኮ ተቀብለው በ 1578 በእንቲጮ እና አዲ ቆሮ ጦርነቶች ላይ፣ እንዲሁም በ 1589 በደባርዋ ጦርነት የቱርክን ሠራዊት ድል ነስተው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጠባቂነታቸውን አሳይተዋል። ይህም በንጉሠ ነገሥቱ ዜና መዋዕልና በቱርክ ሰነዶች ተዘግቦ ይገኛል። ከዚህ ዘመን ጀምሮ የጎንደርና የሸዋ ንጉሠ ነገሥታት በኦሮሞ ተወላጅ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ እምነት አድሮባቸው በሠራዊትነት መልምለዋቸዋል። የኦሮሞ ሕዝብም በውትድርና መስክ በታሪክ የሚዘከርበትን ልህቀት ሊጎናፀፍ ችሏል። ወታደሮቹም በሂደት በየሰፈሩበት አካባቢ ካለ ማኅበረሰብ ጋር በመቀላቀል የመስተጋብሩ አካል ሆነው ተሳስረዋል። ከወታደራዊ አገልግሎት በተጨማሪም በግዛት አስተዳዳሪነትና በቤተ መንግሥት ሹምነት የተለያዩ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ ኦሮሞዎች የመጡት ከ 16 ኛው መቶ ዓመት ማብቂያ ላይ የአፄ ሱስንዮስ አማካሪ፣ የቅርብ ጓደኛና ፀሐፌ ትእዛዝ ከነበረው የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ሊቅ አዛዥ ጢኖ ፈይሳ ጀምሮ ነው። የሕዝቡ እንቅስቃሴ በተጀመረ እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ መሰል ከፍተኛ እርከን ያላቸው የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የኦሮሞ ተወላጆች መፈጠራቸው የኦሮሞ ሕዝብን እንግዳ የማድረግ ዝንባሌም ሆነ በጠላትነት የመፈረጅ አመለካከት እንዳልነበረና የኦሮሞ ሕዝብም ከሌላው ጋር አብሮ ለመኖር ማኅበራዊ ልምድና ለወዳጅነትም ቀናነት የነበረው መሆኑን ነው። በውትድርና ሚናቸው ኢትዮጵያን ያገለገሉና የላቀ ሚና የነበራቸው የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ፖለቲካዊ አመራርነትና የመሬት ከበርቴነት ለመሸጋገር ረጅም ጊዜ አልወሰደባቸውም። ከሌሎች ልሂቃን ቤተሰቦች ጋርም በጋብቻ በመተሳሰር ቅይጥ ማንነት ያላቸው አካባቢያዊ ሥርወ መንግሥታት በጎጃምና በአማራ ( በኋላ ወሎ ) ፤ እንዲሁም ቅይጥ ማንነት ያላቸው ንጉሠ ነገሥታት እና ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉምቱዎች በጎንደርና በሸዋ ሊፈጠሩ ችለዋል። ይህም ከ 17 ኛው እስከ 20 ኛው መቶ ዓመት በተደረጉ መስተጋብሮች የመጣ ውጤት መሆኑ እሙን ነው። ወደ ኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት እየተሳበ በኢትዮጵያዊነት እየተሳሰረ የመጣው የኦሮሞ ሕዝብ የፈጠራቸውና ያበለፀጋቸው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተቋማት በሂደት እየተዳከሙ መሄዳቸው የትስስሮች ተፈጥሮአዊ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ጊቤ ወንዝን ተንተርሰው የተመሰረቱትም የኦሮሞ መንግሥታት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት መቀላቀል የመንግሥት ሥርዓታቸውን ወደ አፄአዊ ሥርዓት ቀይረው እየተዳደሩ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ በተደረጉ ዘመቻዎችና ወዳጅነቶች ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ከሰሜኑ ክፍል ጋር የነበራቸውና ተቋርጦ የነበረው ትስስርና መስተጋብር በአንድ መንግሥት ሥርዓት ስር ተቃኝቶ መቀጠል ችሏል። የኦሮሞ ሕዝብ ያልደረሰበት የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረምና ያልተዛመደው የኢትዮጵያ ሕዝብም አልነበረም። ይህም በኢትዮጵያ የመስተጋብርና የትስስር ታሪክ የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ፤ ሰፈራና ትስስርን ያህል የቀየረ የታሪክ ኩነት የለም ለማለት ያስደፍራል። ይህ ግዙፍ የታሪክ አካል ግን በምሁራን በቂ ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። በታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ለመስተጋብር ታሪክ እና የአንድነት ዐምዶች የተሰጠው ትኩረት እምብዛም ሲሆን፤ የፖለቲካ ትስስሮች በአንፃራዊነት በተሻለ ስፋትና ጥልቀት ተጠንተዋል። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት የፈጠረው ዕውቀትና ተቋማት መኖር ነው። የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የታሪክ ምርምሮች ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት ትርክትን ሲፈጥሩ እና ገዢ ዕውቀት ወደመሆን ሲያድጉ፣ ኢትዮጵያን፣ የጋራ ማንነትና የጋራ ሚናን መሠረት ያደረጉ ጥናቶች እየደበዘዙና እየተገፉ ሊመጡ ችለዋል። ንጥል ንባብና ትውስታን የተንተራሰና ውስብስብ ምስሉን በእጅጉ ያቀለለ፣ ንጥል ሚናን እና ያልተነካካ ማንነትን የተንተራሱ የታሪክ ምርምር ሥራዎች በፖለቲካውና አካዳሚው ማዕቀፍ ውስጥ በመዝለቅ የትስስር መረቦችን የማስረሳት፤ የጋራ የሆኑ እሴቶችንና ማንነቶችና እንደ አደጋ የመፈረጅና የመበጣጠስ ዕቅድን በተባበረ ክንድ መተግበር ችለዋል። የኦሮሞን ሕዝብ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሰላማዊ ግንኙነቶችን በመዘንጋት አደጋ የጣሉ መስፋፋቶችን ለይቶ መዘከር፤ ጠላትነትን ያፈሩ ግንኙነቶች በማግነን የኦሮሞን የመስተጋብር ታሪክ በግጭት ታሪክ የመሻር / የማደብዘዝ ሥራ ተሠርቷል። የሰፈራና የባህል፤ የሃይማኖትና የቋንቋ መስተጋብሮችን በተመለከተ የነገሥታቱን ኦሮሞን የማስፈር ዕቅድ ዋጋ በማሳጣት የኦሮሞ ሕዝብና የኢትዮጵያ መሪዎችን የተቃርኖ ታሪክ የማግነን፣ እንዲሁም በኃይል የተደረጉ የመሬት ይዞታዎች ያስከተሉትን ውጤቶች መርጦ መዘንጋት በታሪክ እውነት ላይ ጉዳት አድርሷል። በውጤቱም የባህልና የሃይማኖት መወራረስን በመካድ ንጥል ማንነትና ልዩ መሆንን አግንኖ የማቅረብ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ከሰፈረበት ማኅበረሰብ ጋር ለዘመናት በባህል እና በደም መቀላቀሉን የመካድ አዝማሚያና አንዳንድ የኦሮሞ ባህላዊ ተቋማት በመስተጋብር ሂደት መክሰማቸውን ዕውቅና በመንፈግ ከታሪክ እውነት ጋር በተፃራሪነት የቆመ የታሪክ ዕውቀት ማምረት ተችሏል። የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የልሂቃኑ ሚና እና ማንነትን የሚገዳደር ትርክት በታሪክ ምርምሮች ላይ ጎልቶ ይታያል። ከሰፈራ ወደ መንግሥት ሥርዓት የተደረገው እድገት ላይ ትኩረት በማድረግ በውትድርና፣ አካባቢያዊ ገዢነት እና በቤተ መንግሥት የተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ የኦሮሞ ጉምቱዎችን ታሪክ መርጦ በማደብዘዝ ሚናቸውንና ማንነታቸቸውን ባልተገባ መልኩ መፈረጅ ተስተውሏል። የኦሮሞ የጦር ሜዳ ተጋድሎዎችንና ልሂቃን ታሪክ መርጦ የመዘንጋት፣ ከጦር አውራነት ወደ ፖለቲካዊ አመራርነትና የመሬት ከበርቴነት ያደጉ ኦሮሞዎች ልሂቃንን ለዚህ ካበቃቸው ታሪካዊ ኹነት ነጥሎ የማጀገን፣ ቅይጥ ማንነት ያላቸውን ልሂቃን ማንነታቸው ላይ የመዘባበት፣ እንዲሁም ኦሮሞ ከሌሎች ጋር ለመኖር ባደረገው የታሪክ ሂደት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተቋማቱ መዳከማቸውን የመካድ ወይም ያልተገባ ተጠያቂ አካል መፈለግ የዚህ ዓይነት ምልከታ እና ትንተና የወለደው ትርክት ነው። ስለሆነም የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ያለውን ሚና እና ማንነት በመስተጋብርና ትስስር መነፅር በመቃኘት በነበረበት የታሪክ እውነት ላይ የማስቀመጥ፣ የተንሸዋረረውን ዕይታ እና ከዚህም የሚመነጨውን ትንታኔ እና ብያኔ የማስተካከል ውስብስብና ግዙፍ ተግባር ከተመራማሪዎች የሚጠበቅ ሚና ነው። ትርክትን የማረቅና ታሪክን በመረጃዎች ላይ በመንተራስ በሳይንሳዊ መንገድ ማጥናት ተጨማሪ ኃይልና ሀብት ይጠይቃል። ይህም ለሀገር አንድነት እና መግባባት አስተዋጽኦ በማድረግ ለልማትና ሰላም ዋናውን መደላድል እንደመሥራት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የኦሮሞ አማራ ገበር ማህበረሰብ መፈጠር፤ ራስ ጎበና እንደ ተወላጅና እንደ አራማጅ 6 ዶ / ር ደቻሳ አበበ ራስ ጎበና በዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ዐሠርት ዓመታት፣ በዛሬው ሰሜን ሸዋ፣ ከኦሮሞ አባትና ከአማራ እናት የተወለደ፣ በኦሮሞ አማራ ባህልና ማንነት ውስጥ ያደገ የጦርና የፖለቲካ ሰው ነበር። በተለይም በወታደራዊ ዕውቀቱና ክህሎቱ ብርቱ ከነበረው አባቱ ዳጪ ዋዩ ታናሽ ልጅ ሆኖ የተወለደ፤ ነገር ግን በአባቱ ፈር ቀዳጅነትና በራሱ ታታሪነት ከታናሽነት ወደ ታላቅነት ደረጃ ያደገ ሰው ነበር። ጎበና ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት መመሥረት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱትን የሸዋ አማራና የቱለማ ኦሮሞን ኅብረት በመፍጠርና በማጠናከር፣ በአንጻራዊነት ከየየብቻ ነጠላ ማንነት በተሻገረ መልኩ የሁለቱንም ያጣመረ ድርብ ( ገበር ) ማንነት የተጎናጸፈ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ግንባር ቀደም ሚና ነበረው። ጎበና ዳጪ የተወለደበት ሰሜን ሸዋ እስከ ዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ በሦስት ዋና ዋና መልከዓ ምድራዊና የሕዝብ አሰፋፈር ክፍሎች የሚከፈል ነበር። አንደኛው በሰሜን እና በደቡብ የወንዞች ሸለቆ፣ ወጣ ገባ የመሬት አቀማመጥ ያለውና ‹‹ የአማራ ምድር ›› ተብሎ የሚጠራው ሲሆን፤ ሁለተኛው በምሥራቅ በኩል ያለው ‹‹ የከረዩ ምድር ››( ይፋት ) ይባል የነበረውና የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስና ኩታ ገጠም የሆነው ነው። ሦስተኛው ደግሞ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ያለው ‹‹ ሸዋ ሜዳ ›› የሚባለው የቱለማ ምድር ነው። በነዚህ ሦስት አካባቢዎች ከሚደረጉት የቱለማና የአማራ የቀድሞ መስተጋብር ውስጥ ዋነኛው አማራዎቹ በቱለማው ምድር ላይ እግራቸውን ለማሳረፍ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ነበር። የዚህም አንደኛው መገለጫ በኦሮሞው አካባቢ ጠንካራ ይዞታዎችን፣ ወይም የሰፈራ መንደሮችን መመሥረትና ኦሮሞዎች ክርስትናን እንዲቀበሉ ማድረግ ነበር። እነዚህ ሰፈሮች በተለምዶ የወታደር 6 ይህ ጽሁፍ ሙሉ በሙሉ በ 2012 በጸሐፊው ከተዘጋጀውና “ ጎበና፡ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ( ሎሳንጀለስ ማውንት ሎዮላ ሴንት ሜሪ ዩንቨርሲቲ፣ በፀሐይ አሳታሚ፣ መስከረም 2012 ዓ ም ) በሚል ርዕስ ከታተመው መጽሐፍ የተቀነጨበ ነው ። መኖርያ ብቻ ሳይሆኑ ቤተክርስቲያን የሚተከልባቸው ወይም ገዳም የሚገደምባቸው ነበሩ። ይህ ደግሞ በአቅራቢያቸው በርካታ ካህናት ስለሚያስፈልጉ የክርስቲያን መንደሮች እንዲመሠረቱ ምክንያት ይሆናቸዋል። ስለዚህ እነዚህ ምሽጎች የወታደርና የፖለቲካ ወይም የአስተዳደር ማዕከላት ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖትና የትምህርት ማዕከላትም ጭምር ነበሩ። በርካታ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት፣ ካህናትና ዲያቆናት ተማሪዎች ይሰፍሩባቸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአማራና በቱለማ ወሰን ላይ የነበሩ አንዳንድ ሰፈሮችና ገበያዎች ወደ ትልቅ የመስተጋብር ማዕከላት ለማደግም ችለዋል። ዋዩ ( ቦኪሳ ) የዛሬው እንጭቆረር፣ አጤሮ ገበያ ( በኋላ እነዋሪ ) ፣ አብደላ ( አማን ) ፣ ሰንከታ ( ሳያደብር ) እና የመሳሰሉት ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ከእነዚህ ማዕከላት አንዷ የሆነችው አብደላ ( አማን ) የጎበና የትውልድ መንደር ነበረች። ስለዚህ ጎበና የተወለደውና ያደገው በዚህ የቆለኛ አማራና የደገኛ ቱለማ መስተጋብር፣ በሰላሙም ሆነ በጦርነቱም ውስጥ እና የመስተጋብሩ ውጤት ነው። ይህን ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረውን የሸዋ አማራና የቱለማ ኦሮሞ ፍትጊያ / ግጭት ከጊዜ በኋላ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት መቀየር ጀመሩ። በዚህም ምክንያት በቆላው የመሬት ችግር የነበረባቸው የአማራ ወንዶች የቱለማ ኦሮሞ ሴቶችን ማግባት ጀመሩ። በተለይም የአማች ሎሌነት እየተለመደ እንደመጣ ይነገራል። ብዙ ወጣት ወንዶች ለኦሮሞ ባለመሬቶች ሎሌነት ይገቡና ከጊዜ በኋላ ጉልማ መሬት ተሰጥቷቸው ከጌቶቻቸው ልጆች ጋራ ትዳር መሥርተው ጎጆ ይወጣሉ። ወደ አባታቸው ምድር ለመመለስ የመሬት እጥረት ስለሚገጥማቸው ደጋና ወይና ደጋውን ይመርጣሉ። ያም ካልሆነ ካገቡ በኋላ ሚስቶቻቸውን ተከትለው “ ሲገባ ” ይሆናሉ። እንዲሁም ብዙ አማሮች ሴት ልጆቻቸውን ለኦሮሞ በላመሬቶች መዳር ስለጀመሩ ብዙ ሴቶች ከቆላ ወደ ደጋ እያገቡ ይወጣሉ። እነዚህ ተጋቢዎች ወዲያው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ዘዬ ሁለተኛውን መናገር ይጀምራሉ፤ ቀጥሎም ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ተከታይ ትውልድ እየተኩ ይመጣሉ። በዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች፤ ከጊዜ ብዛት ይህ የሸዋ ሜዳ፣ በተለይም ሰሜናዊውና ምስራቃዊው ክፍል፣ ከኦሮሞነቱ ይልቅ በቋንቋ ደረጃ አማርኛ ተናጋሪነቱ እየጎላ ሲመጣ ሁለት ማንነት ያለው አፉን ሞልቶ ኦሮሞ ነኝም አማራ ነኝም የማይል ሕዝብ ተፈጠረ። በርግጥ ሌሎች “[ ኦሮሞ ] ገበር ” ነው ይሉታል። ከሜዳው የሸዋ ክፍል ሆኖ አማርኛን እንደዋንኛ መነጋገሪያ የሚጠቀመው ኦሮሞ ገበር የሚባለው ሕዝብ ከላይ ሲታይ አማራ ቢመስልም በውስጥ በገበሩ በኩል ( ቤት ለቤት ) አልያም በወላጆቹና በአያቶቹ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነው እንደማለት። አንዳንዶች አካባቢዎች እንዲያውም ከ ገበር ም በላይ በሁለቱም ፊት አንድ ዓይነት የሚመስሉም፣ የሁለቱንም የኑሮ ፈሊጥ የያዙ የሁለቱንም ቋንቋ እኩል የሚናገሩ አካባቢዎች ነበሩ፤ ዛሬም ናቸው። ስለዚህ ጎበና የተወለደው እንዲህ ካለው ማኅበረሰብ ሆኖ፤ የትውልድ ሥፍራውም የቱለማ ( የአብቹ ) የኦሮሞና የተጉለት ( ወግዳ ) አማራ አዋሳኝ ከሆነው አብደላ ልዩ ቦታው አማን የሚባለው ነው። ዘመኑም በ 1810/11 አካባቢ ነው። የጎበና አባት የቱለማ ( አብቹ ) ኦሮሞ ሲሆን እናቱ የወግዳ አማራ ናት። ዜና መዋዕል ጸሐፊው “ እናታቸው ….. ከወግዳ ገዥ ከአቤቶ ወልዴ፤ የደጃች ጋረደው ወልዴ አባት የአንድ አያት ልጆች ነበሩ። .... አቤቶ ወልዴም ከአማን እስከ ታላቅ አምባ መላ ወግዳን ይገዙ ነበር ....” ይላል። የጎበና አባት ዳጪ ዋዩ እራሱ በወታደራዊ ጥረቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃውን የቀየረ ቁጢሱ ( ታናሽ ) ሆኖ ተወልዶ ነገር ግን እንደ አንጋፋ የሚኖር ነበር። ልጆቹንም ውትድርና ሲያሠለጥናቸው ከልጆቹ መካከል ጎበና ፈጣን የሥልጠና አቀባበል ነበረው። በሥልጠናው የበላይነት ቢኖረውም የነገ ማንነቱን በሚመለከት በተለይ እናቱ እርግጠኛ መሆን ስላልቻለች በዘመኑ እንደነበረው ባህል በጉዲፈቻ ስም አቤቶ ወልዴ ለተባለው ዘመዷ እንዲሰጥ አደረገች። ጎበና ከእናትየውም ዘመድ ባለመስማማቱ በመኮብለል የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አማችና የቅምብቢት ገዥ ከነበረው ከአቶ አቦዬ፣ ቀጥሎም የቴዎድሮስ የሸዋ እንደራሴ ከነበረው አበጋዝ በዛብህ ዘንድ በመሄድ በተለያዩ ምክንያቶች አለቃና አሳዳሪ እየቀያየረ በመጨረሻም በ 1854 ዓ . ም . ከምኒልክ ዘንድ ደረሰ። ምኒልክም የተወለደው በቱለማ ኦሮሞ መካከልና ከጎበና የትውልድ ቦታ ብዙም እሩቅ ባልሆነው በአንጎለላ ቢሆንም በጎበና አንጋፋነት ሁለቱ ቢያንስ ወደ ሃያ ሰባት ዓመት የሚጠጋ የዕድሜ ልዩነት ነበራቸው። ምኒልክ እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ያደገው በዚህ በአንጎለላና በአንኮበር መካከል እየተመላለሰ እንደሚሆን ስለሚገመት የኦሮምኛ ቋንቋን አይሰማም ብሎ ማመን ያዳግታል። ከላይ እንደተባለው በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ እንደየቤተሰቡ ከሁለቱ ቋንቋዎች ወደ አንዱ የሚያደላ ይሁን እንጂ አማርኛ ተናጋሪው ኦሮምኛ ይሰማል፣ ኦሮምኛ ተናጋሪው አማርኛ ይሰማል። አንዳንዱማ ሁለቱንም ያለ ምንም ግድፈት አቀላጥፎ ይናገራል። ምኒልክና ጎበና የተወለዱትና ያደጉት በእንደዚህ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ስለነበር ሁለቱን ማኅበረሰብ በማስተባበር ትልቅ ሀገረ መንግሥት መመሥረት እንደሚችሉ ተረድተዋል ብሎ መገመት ይቻላል። ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ ጎበና በዚሁ በሸዋ ቤተመንግሥት ቋሚ ሹመት እንዲያገኝ የምኒልክ እንደራሴ በነበረው በደጃች ገርማሜ ወልደ ሐዋርያት እንደተጠቆመም ይገለጻል። “ በእግዚአብሄር ቸርነት አልጋችን ገባ። እንግዲህ መጀመሪያ የደጅ አጋፋሪ ነገር እንምከር ’ ……‘ የ [ ኦሮሞ ] አፍ የማያውቅ አጋፋሪ አለን አይባልም። እኛ ጥቂቶች ነን ስንት ባላባት እየመጣ በስማ በለው ሲያነጋግሩኝ ተቸግሬአለሁ። ግዛታችንን ለማስፋት የምናስበው ወደ [ ኦሮሞ ] ቤት ነው። የሚመጣ ሁሉ በደስታ እንዲገናኝ …. ። እንደኔ አሳብ በእናቱ አማራ ባባቱ [ ኦሮሞ ] ነው። ጎበና ይሁን …. ። ” ከዚህ ጥቅስ ውስጥ በርካታ የዘመኑን ዓላማዎች መገንዘብ ይቻላል። አንደኛ የጎበና ሹመት የአንድ ግለሰብ ሹመት እንዳልነበርና እንዲያውም የሸዋ ቤተ መንግሥት ከኦሮሞ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ወይም ትብብር ጎበናን እንደ ዋነኛ አጋርና ድልድይ ለመጠቀም መታሰቡ ነው። ሁለተኛ ሰፊ ግዛት ለመመሥረት ከተፈለገ የኦሮሞን አጋርነት መያዝ የግድ መሆኑን ከገርማሜ ንግግር መረዳት ይቻላል፤ ‹‹ እኛ ጥቂቶች ነን ›› የሚለውን ያጤኗል። ሰፊ ግዛት ለመመሥረት የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ለዚያ ደግሞ ከቅርባቸው ያለው ሰፊ ህዝብ ኦሮሞ ነው። እንዳሰቡትም የዐሥራ ዘጠነኛውና የሃያኛውን ክፍለ ዘመን ሰፊ ኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ለመመሥረት የቱለማ ኦሮሞ ፈረሰኛ ዋና የሠራዊት ምንጭ እንደነበር ግልጽ ነው። ሦስተኛ የግዛት ወይም የመሬት ጉዳይ ነበር። ከአሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ጀምሮ በአማራውና በኦሮሞው መካከል የነበረው መቆራቆስ በመሬት ምክንያት ሲሆን ሰፊና ለም መሬት ደግሞ ያለው በኦሮሞው እጅ ነበር። ለቀደሙት ሁለት መቶ ዓመታት አካባቢ በአማራው በኩል መሬቱን ለመንጠቅ የተደረጉት ሙከራዎች ከሞላ ጎደል የተሳኩት በጣም ትንሽ በሆኑ ቦታዎች፣ ለምሳሌ በይፋትና በተጉለት፣ ከአንኮበር እስከ በሬሳ ወንዝ ድረስ፣ ብቻ ነበር። በተረፈ ቱለማን ከመሬቱ ለማስለቀቅ አልቻሉም። በመሆኑም ለዚህ ዓላማ ሌላ ዘዴ መቀየስ ነበረባቸው። ይኸውም ቱለማን ቀርቦ የኅብረት ስምምነት አድርጎ ሌሎችን በማስማማትም ይሁን በመውጋት ግዛቱን ማስፋት። አራተኛው ነገር ደግሞ የቋንቋ ጉዳይ ነው። የኦሮምኛ ቋንቋ የማያውቅ አጋፋሪ አይጠቅመንም ብለው አስበው ቋንቋቸውን በቁጥር ብዙ በሆነው ኦሮሞ ላይ በግድ ለመጫን ሙከራ ከማድረግ ይልቅ ሁለቱንም ቋንቋዎች የሚናገር ሰው መፈለጋቸው ነበር። ጎበና የተሾመበት ቦታም ልክ እንደዘመኑ የሕዝብ ግንኙነት የሚያገለግል ስለሆነ ሁለቱንም ቋንቋ መቻል ከሁለቱም ህዝቦች ጋር ወይም ተወካይ ባላባቶች ጋር ለመነጋገር አስፈላጊ ነበር። ስለሆነም ጎበና አብዛኞቹን የቱለማን ኦሮሞ ንዑስ የጎሳ መሪዎች በኦሮሞ ባህልና ወግ በመቅረብ ከሱ ጋር እንዲተባበሩ በማስማማት ያለውጊያ እንዲገቡና የሚጠበቅባቸውን ግብርም ይሁን የዘመቻ አገልግሎት እንዲያበረክቱ አደረጋቸው። እርስ በርሳቸውም በሰላም እንዲኖሩ፣ ከአማራውም ጋር የበለጠ እንዲዛመዱ መንገድ ቀደደላቸው። በዚሁ ምክንያት በተደራቢነት ይሠራ ከነበረበት ከተጠባባቂ የጦር አበጋዝነት ወደ ሙሉ የጦር አበጋዝነት በነጋሪት በሽልማት ደጃዝማች ጎበና ተብሎ እኤአ በ 1875 ተሾመ። በጥቅሉ ጎበና በቱለማዎች ዘንድ በግንባር ቀደምትነት የሠራው ሥራ ከተከታታይ ግጭትና ጦርነት ወይም በዝርፊያ ግብር ከመገበር ይልቅ ማሳመንና ሕጋዊ የመንግሥቱ አካል አድርጎ ግብር መቀበልን ነበር። የቱለማ በዚህ ሁኔታ መግባት ከዚያም በላይ ሌላ ተጨማሪ ጠቀሜታም ነበረው፤ እነሱን እንደመነሻ እና የሰው ኃይልም አድርጎ ቀጥሎ ያሉትን ኦሮሞዎች ( መጫዎችን ) እና ጉራጌዎችን ማስገበር ነበር። እነሱም በጎበና ስልት የምኒልክ መንግሥት አካል ሆነዋል። ጎበና ደጃዝማች ተብሎ የጦር አበጋዝ ከሆነ በኋላ የሸዋ መሳፍንት መኳንንት ተስማምተው አገር የማስገበር ዕቅዳቸውን እንደሚከተለው ተከፋፈሉ፡ • ደጃች ወልደ ገብርኤል ምሥራቁን ( ጨርጨር፣ ሐረር እስከ ቻለ ድረስ ) ፣  ደጃዝማች ዳርጌ ጃርሶን እስከ ዓባይ ሙገር በውል ካስገበረ በኋላ አርሲ ባሌን ምሥራቁን እስከቻለ ድረስ፣  ደጃዘማች ገርማሜ አዋሽን ተሻግሮ ያለውን ግራ መሬት ጉራጌን ይዞ እስከ ቦረና እስከቻለ ድረስ፣  ደጃዝማች ጎበና ምዕራቡን ከሶዶ ከጉራጌ ባሻገር፣ በዚህም ከሙገር ባሻገር፣ እስከቻለ ድረስ፣  ምኒልክ ራሱ ደግሞ በፊቱን በተደጋጋሚ የተዘመተበትን ወሎን። ወሎን በተመለከተ ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ ብዙ ውዝግብ ነበረበት። ወሎን መክፈት የለብንም፤ በራችን ነው በሚሉ ወገኖችና ወሎ ተከፍቶ ከአውሮፓ ሰዎች በተለይም የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ጋር መገናኘት፣ ከተቻለም ጎንደር ላይ መንገሥ በሚሉ ወገኖች መካከል ነበር። በመጨረሻም የመክፈቱ ሐሳብ በምኒልክ ግፊትም ቢሆን ተቀባይነት አገኘ። በዚህ በተጠቀሰው ዕቅድ መሠረት እንደለመደው በንግግርና በድርድር የተሰጠውን አካባቢ በማስገበር ጎበናን የቀደመው አልነበረም። የመጫ አሮሞን በሙሉ በዚሁ መልክ ካስገበረ በኋላ ጎበና ጦርነት ያደረገው ለሌሎቹ የተደለደሉትን ግዛቶች በማስገበር ሂደት እገዛ በሚመስል መልኩ ገብቶ ነበር። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በተለምዶ የጉራጌ ዘመቻ የሚባለው ሐሰን እንጃሞን እና የወሎ ገዥዎችን ለማስገበር ያደረገው መጠነ ሰፊ ውጊያ ነበር። ጎበና ደጃዝማች ተብሎ ብዙም ሳይቆይ ከሦስት ዓመት በኋላ እኤአ በ 1878 ዓ . ም ራስ ተብሎ ተሾመ። ምኒልክም ይህንን የጎበናን አበርክቶ እውቅና በመስጠት “ የሀገር ንጉሥ እኔ የጦር ንጉሥ አንተ ” ብሎታል ይባላል። ጎበና ጎበና ጎበናዬ የኔ፣ የጦር ንጉሥ አንተ የሀገር ንጉሥ እኔ ፤ እንዲሉ። ጎበና በግል ሕይወቱም ቢሆን ሕዝብን ከሕዝብ ወይም ጎሳን ከጎሳ የማዛመድ መርህን የተከተለ ነበር። የጎበናን ጋብቻ በሚመለከት የሕግ ባለቤቱ ስሟ በተደጋጋሚ የሚነሳው ወይዘሮ አየለች አባ ሪሳ ነች። ዘመዶቹ “ ራስ ጎበና በየአቀኑት አገር ብዙ ሚስቶችና ዕቁባቶች ስለነበሯቸው ከነዚህ በጣም በርካታ ልጆችን ወልደዋል ” ይላሉ። ከልጆቹ አስካለ፣ ተናኜ፣ ጸዳለ፣ ዘውዴ፣ ታሲሳ ( ወልደ ሩፋኤል ) ፣ ቱሉ፣ ደለንሶ፣ መርዕድ፣ አብዲ፣ ወዳጆ፣ መና፣ ብርቄና የመሳሰሉት በስም የተጠቀሱ ናቸው። መርዕድ የተወለደው የምኒልክ ዘመድ ከሆነችው ጌጤ በድሉ ከምትባል ሴት ነበር። ቀጣይ ተወላጆቹ ገበር እንደሆኑም ይገመታል። ለማሳያ ያክል የወልደ ሩፋኤል ልጅ ጽጌማርያም የምትባለው ለራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ተድራ የዚሁ ጋብቻ ፍሬ የሆነው ልጅ ሚካኤል እምሩ ልጁን ጎበና ብሎ እንደሰየመው ይነገራል። ከአስካለ ጎበና በተወለደው አበበ አረጋይ በኩልም አንዱ የአበበ ልጅ፣ ዳንኤል፣ ልጁን ጎበና ብሎ ሰይሟል። ለማንኛውም ጎበና ለራሱ በሁለቱም መካከል ቢኖርም ( ማለትም በአማራውና በኦሮሞው ) ልጆቹን በኦሮሞው ባህልና ሥርዓት ውስጥ ሳይሆን በክርስትናውና በቤተመንግሥት ሥርዓት ለማሳደግ ጥረት ያደረገ ይመስላል። በዚያ ብቻም እንዳይባል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዘመናዊ ነው ብሎ ያሰበውን ባህልና ሥርዓት ለማስጨበጥ ከሚሲዮኖች ጋርም ቢሆን እንደወግ አጥባቂዎቹ የሸዋ ሰዎች ሳይሆን አቅርቦ ልጆቹ እንዲማሩ ፍላጎት አሳይቶ እንደነበር መረዳት ይቻላል። የቀለም ትምህርትና ዘመናዊነትን ብቻ ሳይሆን በዘመኑ የተለመደውን የመሳፍንትና የመኳንንት ልጆች የሚማሩትን የአካል ማጎልመሻና የጦር ስልት በተለይ ወንዶቹ እንዲማሩ አድርጓል። በጋብቻም ልጆቹን ሴቶቹንም ወንዶቹንም በዘመኑ ባህል መሠረት ከጎበዝ ተዋጊዎች፣ ከሊቃውንት ከዚያም አልፎ ከሸዋ መሳፍንትና መኳንንት ጋር አጋብቷል። ለምሳሌ በአጭሩ ቢቀጭም የወዳጆ ጎበናና ሸዋረጋ ምኒልክን ጋብቻና ፍሬውን መመልከት ይቻላል። በሃይማኖቱ ( በእምነቱ ) ፣ በጎበና የትውልድ አካባቢ ክርስትና የአጠቃላይ ሕዝቡ እምነት የነበረው የአማራ ወረዳዎች በሚባሉት ውስጥ ነበር። በቱለማ ኦሮሞ አካባቢዎች የነበረው የክርስትና ታሪክ ከሸዋ ሥርወ መንግሥት መመሥረት፣ ከአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ነው። ከመንዝ የተነሱት የሸዋ መሪዎች በሰፈሩበት መሬት ላይ ሁሉ ቤተክርስቲያን እየተከሉ ከአንጋቻ ጀምሮ ዐይኔ፣ ዶቃቂት፣ ሃራምባ፣ አንኮበር፣ አንጎለላ፣ ልቼ፣ እነዋሪ በመጨረሻም እንጦጦ ደረሱ። በጥቅሉ ክርስትናው በቱለማዎቹ አኗኗር ዘንድ ሁለት ዋነኛ ለውጦችን ብቻ ነው ይዞ የመጣው፣ ጾም እና የመቃብር ቦታ። በተረፈ ተቀዳሚ የሕይወት መመርያቻው አልነበረም። ከዚህ በተጓዳኝ በቱለማ ኦሮሞዎች ሕይወትና ታሪክ የሁለት ጻድቃን አባቶች ( አቡዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ) ያላቸው ቦታ ከመደበኛው የክርስትና ኑሯቸዉ በተለየ መልኩ በጣም ጠንካራ ነበር። አባ ተክሌ እና አቦ የሁለቱም አባቶች ዐቢይ ገዳማት የሚገኙት በቱለማ ኦሮሞ ምድር ስለሆነ የማንኛውም የሸዋ ሰው ቱለማን ጨምሮ የጉብኝት ማዕከላት ነበሩ፤ ናቸውም። እነዚሁ ቱለማዎች በአቅራቢያቸውም ሰፊ የእሬቻ ሥርዓት መከወኛ ቦታዎች ነበሯቸው። የቱለማ ኦሮሞዎች ክርስትናን ከአገር በቀሉ የኦሮሞ እምነት ሙሉ በሙሉ ነጥለው የሚያመልኩ አልነበሩም። ጎበናም ከዚህ ወጥቶ ለብቻው ፍጹም ክርስቲያን ሊሆን የሚችል ሰው አልነበረም። በእርግጥ እንደሌሎቹ አማራ ባልደረቦቹ በአማራ አካባቢዎች ላሉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ካህናት እና መነኮሳት ‹‹ አስቡኝ ›› በሚል ስልትና ለክብርም ሲባል ቀለብና ልብስ በእርዳታ መላክ የተለመደ ነበር። ስለዚህ የክርስትናና እስልምና ጠንካራ መሠረት ባልነበረበት የቱለማ አካባቢ ጎበናና ምኒልክ ክርስትናን በማስፋፋት ሂደት ኦሮሞ የራሱን ያገር በቀሉን እምነት እንዲተው ጥረት ያደረጉት በድርበቡ ነበር። ደጃዝማች ቱሉ እና ደጃዝማች ወሬኛ ዋሾ፤ አጭር ታሪካዊ ዳሰሳ ( ከ 1690 ዎቹ እስከ 1760 ዎቹ ) ዶ / ር ገረመው እስከዚያ የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በ 17 ኛው መቶ ዓመት መጨረሻ እና በ 18 ኛው መቶ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ጎጃም ዉስጥ በጣም ታዋቂ የነበሩትን ደጃዝማች ቱሉ እና ደጃዝማች ወሬኛ ዋሾ የተባሉ የቡሬ ዳሞት ገዥዎችን የተመለከተ አጭር ታሪካዊ ዳሰሳ ማድረግ ነው። የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሁለቱም ከዐባይ ወንዝ በስተደቡብ በአፄ ኢያሱ ቀዳማዊ ( እ . ኤ . አ 1682-1706) አማካኝነት ወደ ጎጃም ከተሻገሩት ጃዊ ተብለው ከሚጠሩት የኦሮሞ ጎሳ የወጡ ናቸው። የሁለቱ ደጃዝማቾች ታሪክ ምንም እንኳ ሁሉንም የኦሮሞ እና የጎጃም ነዋሪዎች ታሪካዊ ግንኙነት ባይገልፅም፤ በዘመኑ ለነበረው መስተጋብር እና ትስስር ማሳያ ይሆናል። ይህን ታሪክ ለመጻፍ የሚያገለግሉ ዋና ዋና የታሪክ ምንጮች የጎንደር ዘመን ነገሥታት ዜና መዋዕላት፣ ታሪከ ነገሥት፣ ጀምስ ብሩስ የተባለው ስኮትላንዳዊ ተጓዥ የጻፈው ባለ አምስት ቅጽ የጉዞ ማስታወሻ፣ አፈ ታሪኮች እና ልዩ ልዩ ሰነዶች ናቸው። የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎች የጻፏቸው መጻሕፍት እና ጥናቶችም በዋቢነት ያገለግላሉ። የደጃዝማች ቱሉ የትውልድ ሥፍራ ከዛሬዋ የቡሬ ከተማ በስተሰሜን የምትገኝ የድንግራ የምትባል ቦታ ናት። ይሁን እንጅ ስለ ቤተሰቦቹ ሁኔታ የሚያስረዳ ዝርዝር ታሪካዊ ማስረጃ የለንም። የታሪክ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቱሉ በአካባቢው ለነበሩ ባሶ፣ ሊበን፤ ቡሬ ዳሞት፤ እና ማቻከል አካባቢዎች ዋና ገዥ የነበረ ሰው ነው። ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ችሎታውን በማድነቅም አፄ ኢያሱ ከሴት ልጆቹ መካከል አንዷ የሆነችውን ወለተ ሥላሴን ስለዳረለት ከጎንደር ቤተ መንግሥት ጋር በጋብቻ መተሳሰር ችሏል። እንደ ደጃዝማች ቱሉ ያሉ የአካባቢ ገዥዎች ዋና የሥራ ድርሻ ግዛታቸውን ከዐባይ ወንዝ ማዶ ከሚመጣ የኦሮሞ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መከላከል፣ ሰላም እና ሥርዓት በግዛታቸው ውስጥ ማስፈን፣ ዓመታዊ ግብር መጫን እና ነገሥታቱ በሚያካሂዷቸው ዘመቻዎች መሳተፍ ነበሩ። በመሆኑም ደጃዝማች ቱሉ በአፄ ኢያሱ ዘመን እ . ኤ . አ . በ 1700 ፣ 1702 እና 1704 ለተካሄዱ የዐባይ ማዶ ዘመቻዎች ዕቅድ ከማውጣት አንስቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ግምባር ቀደም ተሳትፎ ነበረው። እነዚህ ዘመቻዎች፣ በተለይም የ 1704 ቱ የጉድሩ፣ እናርያ እና ጊቤ ዘመቻ፣ ምንም እንኳ የታሪክን አቅጣጫ በዘላቂነት የመቀየር አቅም ባይኖራቸውም የተሳካላቸዉ ዘመቻዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። ለዚህም የቱሉ ሚና ከፍተኛ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በ 18 ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን በቡሬ ዳሞት አካባቢ ዋና አባት ለመሆን የቻሉት እንደ ደጃች ወሌ ሕዝብን ( ወሎ ሕዝቦ ተብለውም ይታወቃሉ ) የመሳሰሉ በእቴጌ ምንትዋብ እና ዳግማዊ አፄ ኢያሱ (173055) ቤተ መንግሥት ዘንድ ታዋቂ የነበሩ ሰዎች በነዚህ ዘመቻዎች አማካይነት ወደ ጎጃም ከተሻገሩት ኦሮሞዎች መካከል ናቸው። ይሁን እንጂ አፄ ኢያሱ እ . ኤ . አ በጥቅምት 1706 በልጁ በተክለ ሃይማኖት በሚመራ የቤተ መንግሥት ሴራ ተገደለ። ቱሉም የንጉሥ ኢያሱ እኅት ከሆነችው ከእሌኒ ጋር በመሆን የቅባት ሃይማኖታዊ ጎራ መሪ ሆነ። የንጉሥ ኢያሱን መገደል ተከትሎ ከነገሠው አፄ ተክለ ሃይማኖት ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ቱሉ ወደ ሐማሴን፤ እሌኒም ሱዳን ድንበር ላይ ወደሚገኝ ተንከል ወደ ተባለ ቦታ ተጋዙ። ቱሉ ለጥቂት ዓመታት ሀብ ሥሉስ የተባለ መስፍን በሚያስተዳደረው ሐማሴን ግዛት ዉስጥ በግዞት ቆይቶ አፄ ቴዎፍሎስ (1708-11) ሲነግሥ በ 1708 ከግዞት ነጻ ወጥቶ ወደ ጎንደር ተመለሰ። ከዚያ በኋላ በምን ሁኔታ እንደቆየና በመጨረሻም እንዴት እንደሞተ የሚያሳይ የታሪክ ማስረጃ የለም። በዚህ ጥናት በሁለተኛነት የምናየው በአፄ በካፋ (1723-30) ፣ ዳግማዊ አፄ ኢያሱ ( ብርሃን ሰገድ ) እና አፄ ኢዮዓስ (1755-69) ዘመነ መንግሥታት ዝነኛ የጦር መሪ የነበረውን በተለምዶ ደጃዝማች ወሬኛ ተብሎ የሚጠራውን ሰው ይሆናል። ትክከለኛ ስሙ ዋሾ ነዉ። ወሬኛ የሚለው በዘመኑ በጣም ጀግና ለነበሩ ሰዎች የሚሰጥ ማዕረግ ነበር :: ደጃዝማች ወሬኛ ምናልባትም ደጃዝማች ቱሉ ከሕጋዊ ሚስቱ ውጭ የወለደው ልጁ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ታሪክ ጸሐፊዎች አሉ። ደጃዝማች ወሬኛን ከነጋዴነት ወደ ወታደርነት ያሸጋገረው አፄ በካፋ እንደ ነበር ጀምስ ብሩስ ጽፏል። በዘመኑም ላስታ አካባቢ እ . ኤ . አ . በ 1724 በአምኃ ኢየሱስ እና በ 1725 በልጁ ባል በጉባላ የሚመሩ ጠንካራ አመጾች ተቀስቅሰው ስለነበር እነዚህን አመጾች ለመቆጣጠር በካፋ ባካሄዳቸዉ ዘመቻዎች ደጃች ወሬኛ የሚመራቸው ጃዊ እና ባሶ ተብለው የሚጠሩ የቡሬ ዳሞት የሠራዊት ክፍሎች ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ የአፄ በካፋ ዜና መዋዕል ያብራራል። አፄ በካፋ እንደሞተ እቴጌ ምንትዋብ የነበራትን ፖለቲካዊ ችሎታ ካሳየችባቸው ነገሮች አንዱ ወሬኛን እ . ኤ . አ በ 1730 ዓ . ም በየጊዜው አመጽ ይከሄድባቸው ለነበሩት ለዳሞት፣ አገው ምድር እና ሜጫ አካባቢዎች ገዥ ( ደጃዝማች ) አድርጋ መሾሟ ነበር። ወሬኛም በእነዚህ አካባቢዎች የተነሱ አመጾችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር አደረጋቸው። በተለይም ደግሞ ወሬኛን በጎንደር ቤተ መንግሥት እጅግ ዝነኛና ተወዳጅ ያደረገው እ . ኤ . አ . ከ 17 ዲሴምበር ( ታኅሣሥ ) 1732 እስከ 1 ጃኑዋሪ ( ጥር ) 1733 ጎንደር ከተማ ዉስጥ የተካሄደውን አመጽ ካከሸፈ በኋላ ነበር። የአመጹ መሪ ተንሴ ማሞ የተባለ የዳሞት እና አገው ምድር ተወላጅ ሲሆን ዓላማውም ሕዝቅያስ የተባለውን የነገሥታት ዘር በማንገሥ በቋረኞች ተነጥቆ የነበረውን ሥልጣኑን በማስመለስ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ መሆን ነበር። ለዐሥራ አምስት ተከታታይ ቀናት ጎንደር ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዶ፣ በመጨረሻ ወሬኛ ሠራዊቱን ከቡሬ ዳሞት እና ጎጃም አሰባስቦ ጎንደር በመድረሱ አመጹ ሊከሽፍ ቻለ። ተንሴም ተይዞ በስቅላት ተቀጣ። ከዚህ በኋላ በነበረው ዘመን የጎንደር መንግሥት ይገዛው በነበረዉ ከጣና ሐይቅ በስተ ደቡብ በሚገኙት ግዛቶች ሁሉ የወሬኛ ስምና ዝና እጅግ ናኘ። የዳሞትና የአገው ምድር ግዛቶችን ከሸዋ እና ወለጋ አካባቢዎች የሚመጣ የኦሮሞ ጥቃት መከላከል ከቀዳሚ የሥራ ድርሻዎቹ አንዱ ነበር። ለዚህም ከጦርነት ይልቅ ድርድርን ያስቀድም ነበር። በተጨማሪም በግብር ክፍያ ይሁን በሌላ ምክንያት የሚነሳ አመጽን ለማክሸፍ ከአባይ ወንዝ በስተደቡብ ይኖሩ የነበሩትን ኦሮሞዎችን በማስፈራሪያነት ይጠቀምባቸው ነበር። የዳሞትና አገው ምድር ሰውም ኦሮሞ ከወንዝ ማዶ መጥቶ “ ከሚበላዉ ” የሚጣልበትን ግብር በመክፈል በሰላም መኖርን ይመርጥ ነበር። ይህም በተለይ በናና ጊዮርጊስ የሚመሩ የአንከሻ እና ባንጃ አካባቢ አገዎችን ይመለከታል። እ . ኤ . አ . በ 1742 እና 1744 የዳግማዊ አፄ ኢያሱ መንግሥት በስናር ( ፉንጅ ) መንግሥት ላይ ባካሄዳቸው “ የበለው ዘመቻዎች ” የወሬኛ ፈረሰኛና እግረኛ ሠራዊት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ነበረው። በመጨረሻም እ . ኤ . አ . በ 1763 ዓ . ም ደጃች ወሬኛ ከናና ጊዮርጊስ ጋር እየተዋጋ በነበረበት ሰዓት የጀግና ሞትን ሞተ። ሲጠቃለል፣ የሁለቱ ዝነኛ የቡሬ ዳሞት እና አካባቢው መሪዎች ታሪክ የሚያሳዩን ሁለት ቁም ነገሮች አሉ። አንደኛው ምንም እንኳ ያሰፈሯቸዉ ነገሥታቱ ቢሆኑም ቀደም ሲል ጎጃም ዉስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ከዐባይ ወንዝ ማዶ የሚኖሩ የተለያዩ የሜጫ እና ቱለማ ኦሮሞ ጎሳዎች ለረጅም ዘመናት ያካሄዱትን መስተጋብር እና ትስስር ያመለክታሉ። ሁለተኛ፣ ጎጃም ዉስጥ የሰፈሩ የኦሮሞ መሪዎች ጎንደር ማዕከሉ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ያህል ታማኝ እና ስኬታማ ገዥዎች እንደነበሩ እንረዳለን። እሰከ ዛሬ ድረስ ከምሥራቅ ጎጃም ባሶ ሊበን ወረዳ ጀምሮ በምዕራብ እስከ ሜጫ ወረዳ ድረስ የሁለቱ ዝነኛ ሰዎች ስም በቦታ፣ተራራ እና የሰው ስምነት በስፋት ያገለግላሉ። በነዚህ አካባቢዎች በሚነገሩ አፈ ታሪኮች ውስጥም የሁለቱ ሰዎች ድርሻ ሰፊ ነው። ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፤ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጉምቱ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መሪዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። የሕይወት ታሪካቸውን በተመለከተ ቀደም ሲል አንድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቴ ይታወሳል። 7 በዚህ አጭር ጽሑፍ ማድረግ የምፈልገው ይህን የሕይወት ታሪካቸውን “ ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ባዘጋጀው የሦስት ዙር ውይይት ዐውድ ውስጥ ማስቀመጥ ነው። ቀደም ሲል በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ለዚህ ጽሑፍ አግባብነት ያላቸው ቢያንስ ሦስት ርዕሰ ሐሳቦች ጎልተው ወጥተዋል። እነሱም የብሔረሰቦች መስተጋብር፣ ቅይጥ ወይም ውህድ ማንነት እና ማንነትና የፖለቲካ ሥልጣን ናቸው። እነዚህን ርዕሰ ሐሳቦች ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የሕይወት ታሪክ ጋር በማዛመድ አቀርባለሁ። የብሔረሰቦች መስተጋብር የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የትውልድ ሥፍራ ለምዕት ዓመታት በጉራጌና ኦሮሞ ብሔረሰቦች መካከል ከፍተኛ መስተጋብር የታየበት አካባቢ ነው። ይህ ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት፣ በግጭት የታጀበ ቢሆንም፤ እያደር ግን በአብዛኛው ሰላማዊ ግንኙነት የሰፈነበት ነበር። በተለይ የበይነ ብሔረ ሰቦች የጋብቻ ትስስር ጎልቶ የታየበት አካባቢ ነበር። እንደዚሁም የአካባቢው ሕዝብ ኑሮ በእንሰት ተክል ላይ የተመሠረተ ነው። በተለይም የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የትውልድ ሥፍራ የሆነው ጨቦ ምርጥ እንሰት የሚገኝበት አካባቢ ነው። የታሪክ ተመራማሪዎች ጨቦ በኦሮሞ የተዋጠ የጉራጌ ብሔረሰብ ቅሪት ነውም ይላሉ። ወይም በብዙ ኦሮሞዎች በሠፈሩበት አካባቢ ነባሩን ሕዝብ እንዳደረጉት ‹‹ ገባሮ ›› አድርገዋቸው ነበር ይባላል። ሌላው የብሔረሰቦቹን መስተጋብርና ትስስር የሚያመለክት ክስተት በተለይ ብዙ የክስታኔ ጉራጌዎች ስሞች የኦሮሞ መሆናቸው ነው። ለአብነትም በብዛት የሚያጋጥሙትን እንደ ኢብሣ፣ ኢላላ፣ ዋቅጅራ፣ ቱሉ የመሳሰሉትን ስሞች መጥቀስ ይቻላል። በክስታኔ ባህል በተለይ ሠርግ የሚያደምቀው ‹‹ የወረይ ሰመሌ ›› የተሰኘው ዘፈን በኦሮምኛም ሲቀነቀን ይስተዋላል። ‹‹ ሶዶ ›› የሚለው በመሠረቱ የኦሮሞ ጎሣ መጠሪያ የሆነው ስም ለክስታኔዎችም አማራጭ መጠሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ስለሆነም አንዳንድ የክስታኔ ጎሣዎችን ለይቶ ጉራጌ ወይም ኦሮሞ ናቸው ለማለት ያዳግታል። ይሁን እንጂ ከ 1983 ቱ የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ በኋላ ለአያሌ ዓመታት ተሳስረው የቆዩትብሔረሰቦች ‹‹ ሶዶ ጂዳ ›› እና ‹‹ ሶዶ ጎርደና ›› በሚል መጠሪያ ጎራ ለይተው የጎሪጥ መተያየት ጀመሩ። የመጀመሪያዎቹ ኦሮሞነታቸውን ሲያቀነቅኑ፣ ሁለተኞቹ ደግሞ በጉራጌነታቸው ጸንተው ቆዩ። ለጥቂት ዓመታት ሲናቆሩ ከቆዩ በኋላ ዕርቀ ሰላም ወርዶ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ግንኙነታቸው ሊመለሱ ችለዋል። ቅይጥ ማንነት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በአባታቸው በኩል የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ ሲሆኑ በእናታቸው በኩል ደግሞ የጉራጌ ተወላጅ መሆናቸው የታወቀ ነው። አባታቸው ዲነግዴ ሁንዱል የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል ሲሆኑ እናታቸው እመት አጆ አምድኖ ደግሞ በእናታቸው በኩል የጉራጌ ብሔረሰብ አባል ነበሩ። በዚህ ረገድ ሕይወታቸው በብዙ መልኩ ከተሳሰረው ከደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሕይወት ጋር ይመሳሰላል። በአገምጃ ( ሶዶ ) የተወለዱት ደጃዝማች ባልቻም በአባታችው በኩል ኦሮሞ ሲሆኑ በእናታቸው በኩል ደግሞ ጉራጌ ነበሩ። ይሁን እንጂ ሁለቱም የጦርና የፖለቲካ መሪዎች በታሪክ የሚታወቁት በብሔረሰባዊ ማንነታቸው ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታቸው ነው። ለኢትዮጵያ ተሟግተዋል፣ ተጋድለዋል። ባልቻ በአድዋ ላይ ጣልያኖችን በማሸነፍ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ ከማይጨው በኋላ ደግሞ የኢጣልያንን አገዛዝ በእምቢተኝነት ሲዋጉ ተሰውተዋል። ብዙውን ጊዜ በተለይ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስን የኦሮሞ ማንነት ለማሳየት ሲደክሙ የሚታዩት የውጭ አገር ዘጋቢዎች ነበሩ። 7 ሀብቴ አባ መላ፤ ከጦር ምርኮኛነት እስከ አገር መሪነት ( አዲስ አበባ፣ 2008) ። ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በተለይ የአማርኛ ቋንቋን አበጥረው እንደሚያውቁ በታሪክ ከሚታወቁባቸው ዝነኛ ፍርዶቻቸው መረዳት ይቻላል። በዚህ አጋጣሚ ሊጠቀስ የሚገባው ተመሳሳይ ጉዳይ ከአማራና ኦሮሞ የተወለደው የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን የአማርኛ ቋንቋ ጠቢብነት ነው። ፊታውራሪና ሎሬት ፀጋዬ ያደጉት ጎረቤት በሆኑ አካባቢዎች ነው፤ የመጀመሪያው በደንዲ፣ ሁለተኛው በቦዳ። ሁላችንም እንደምናውቀው በግጥሞቹና ተውኔቶቹ አማካይነት በሃያኛው መቶ ዓመት የአማርኛ ቋንቋንና ሥነ ጽሑፍን በማሳደግ ረገድ የሎሬት ፀጋዬን ያህል የተዋጣለት ደራሲ የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ማንነትና የፖለቲካ ሥልጣን በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ውስጥ ጉልህ የሆነ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሚና በመጫወት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የመጀመሪያው ኦሮሞ ተወላጅ አይደሉም። በዚሁ ስብስብ ውስጥ በገረመው እስከዚያው በቀረበው ጽሑፍ እንደተብራራው በጎንደር ዘመነ መንግሥት ደጃዝማች ተሉና ደጃዝማች ወሬኛ ዋሾ ነበሩ። እነሱም ለ 65 ዓመታት ያህል የጎንደርን መንገሥት በበላይነት ለመምራት የበቁ የየጁ ‹‹ ሥርወ መንግሥት ›› መሣፍንት ፈር ቀዳጆች ነበሩ ማለት ይቻላል። ወደ 19 ኛው መቶ ዓመት ስንመጣ ደግሞ በደቻሳ አባባ በቀረበው ጽሑፍ የሕይወት ታሪካቸው የተዘገበው የንጉሥ / አፄ ምኒልክ አውራ የጦር መሪ ራስ ጎበና ዳጬ እና ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ አሉ። ጎበናን ከባልቻና ሀብተ ጊዮርጊስ ጋር ስናነፃፅር ተመሳሳይነትም ልዩነትም እናያለን። ጎበና ለወታደራዊ ዝና ሊበቁ የቻሉት ከምኒልክ ጋር አጋርነት በመፍጠር ሲሆን፤ ባልቻና ሀብተ ጊዮርጊስ ለዕድገትና ሞገስ የበቁት በጦር ምርኮኝነት ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ከመጡ በኋላ ነው። የሕይወታቸው ፍፃሜም የተለየ ነው። ጎበና የምኒልክን ግዛት በተለይ በምዕራቡ በኩል በማስፋፋት ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ በኋላ የጌታቸውን ሥርዓተ ንግሥ ሳያዩ በሰኔ 1881 ዓ . ም . በበሽታ ሞቱ። ይሁን እንጂ አፄ ዮሐንስ ከወራት በፊት መተማ ላይ ሲሰዉ፤ የምኒልክ ንጉሠ ነገሥትነት የተረጋገጠ ነበር። ባልቻ በአድዋ ጦርነት የተዘመረላቸው ጀግና ከመሆናቸውም በላይ ከአርባ ዓመት በኋላ ጣልያን ቂም ቋጥሮ እንደገና ኢትዮጵያን ወሮ ሲይዝ፤ አላስቀምጥ ብለው ሲዋጉ ከሞቱት አርበኞች መካከል አንዱ ነበሩ። ሀብተ ጊዮርጊስ ሕይወታቸው ፍጻሜውን ያገኘው እንደ ባልቻ በጦር አውድማ ሳይሆን እንደ ጎበና በሕመም ነው። የፊታውራሪ የመንግሥት አገልግሎት በአራት ዘርፎች ይመደባሉ፡ ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ አስተዳደር፣ ድንበር ማስከበር እና የአፄ ምኒልክን ቅርስ ማስቀጠል። እነዚህን ዘርፎች በየተራው እንቃኛለን። ወታደራዊ ዘመቻዎች በውል የታወቀው ሀብተ ጊዮርጊስ የተሳተፉበት የጦር ዘመቻ የቀቤናውን መሪ ሐሰን እንጃሞን ለማስገበር በመጋቢት 1881 ዓ . ም . የተደረገውና ከሁለቱም ወገን ብዙ ተዋጊዎች ያለቁበት የጀብዱ ጦርነት ነው። በአድዋ ዘመቻ ወቅት ሀብተ ጊዮርጊስ ከአዋጊነት ይልቅ የአማካሪነት ሚና የነበራቸው ሲሆን፤ የጦር አበጋዙ ፊታውራሪ ገበየሁ አድዋ ላይ ሲሰዉ ሁሉንም ባስገረመ ሁኔታ ሀብተ ጊዮርጊስ ፊታውራሪ ተብለው የርሳቸውን ቦታ ያዙ። አግራሞቱ የመጣው በሕዝብ ዘንድ ለዚያ ማዕረግ ይታሰቡ የነበሩት በጦርነቱ ከፍተኛ ጀብዱ የፈፀሙት ራስ አባተና ደጃች ባልቻ ነበሩና ነው። ከዚያም በ 1900 ሚኒስትሮች ሲሾሙ ፊታውራሪው ‹‹ የጦር ሚኒስትር ›› ተብለው እስከ ዕለተ ሞታቸው ለ 19 ዓመታት በሹመታቸው ጸንተው ቆዩ። ብዙ መረጃ የምናገኝለት ፊታውራሪ በ 1889 ቦረናን ለማስገበር ያደረጉት ዘመቻ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደራጎን የተባለ ፈረንሣዊ አገር አሳሽ አብሯቸው ስለተጓዘ ነው። ፊታውራሪ በታሪክ በተለይ የታወቁበት ግን የጦር ዕቅድ ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦና ጥበብ ያሳዩበት የሰገሌ ጦርነት ነው። ማዕከላዊ መንግሥቱ በንጉሥ ሚካኤል በሚመራው ግዙፍ የወሎ ጦር ላይ ድል ለመቀዳጀት የቻለው ፊታውራሪ ንጉሡን በመሸንገል ለወገን ጦራቸው ጊዜ ለመግዛት በመቻላቸው ነው። አስተዳደር በአስተዳደር ረገድ፣ ምስሉ ጉግሣ ያደረገው ጥናት 8 እንደሚያሳየው፣ ፊታውራሪ በተለይ በጨቦ ግዛታቸው የዳበረ የአስተዳደርና ፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት ችለው ነበር። በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ፊታውራሪ ፈጣንና ፍትሓዊ ፍርድ 8 Mislu Gugsa,“Estate Administration in Part of Present Day Jibat& Mecha under Fitawrari Habte Giyorgis”, BA thesis(Haile Sellassie I University: Department of History, 1974). በመስጠት ይታወቁ ነበር። ከዚህም የተነሣ ‹‹ አባ ቁርጣ ›› የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቷቸው ነበር። ከፍተኛ የአስተዳደር ተግዳሮት ያጋጠማቸው ከርቀቱና ከሽፍቶች መበራከት የተነሳ በቦረና ግዛታቸው ነበር። ድንበር መከላከል የመሃል አገሩ እንደዚህ ሲሰምርላቸው፣ የዳር አገሩ ግን በብርቱ ፈትኗቸው ነበር። የቦረና አስተዳደራቸው በብዙ ምክንያቶች ፈተና የበዛበት ነበር። አንዱ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድንበሮች በምዕት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በተደረጉ ውሎች በካርታ ላይ ይሰመሩ እንጂ ምድር ላይ በቅጡ አለመካለላቸው ነው። የምኒልክን የጤና መታወክ ተከትሎ በማዕከላዊ መንግሥት ዙሪያ ረጅም ጊዜ የፈጀ የሥልጣን ፉክክር መፈጠሩና የፊታውራሪም የዚህ ፉክክር አካል መሆን ዳር አገር የሚገኘውን ግዛታቸውን ለመጎብኘት ፋታ አሳጥቷቸዋል። ከርቀቱ ጋር ተያይዞም አካባቢው የተለያዩ ሽፍቶች መፈንጫ ሆኖ ነበር። ኬንያን ይገዙ የነበሩት እንግሊዞች በቦረና ግዛት የሚገኙትን የቀዳዱማ ውሃ ጉድጓዶች ለከብት አርቢ ዜጎቻቸው መሻትም ሌላ የጭቅጭቅ መንስዔ ሆኖ ነበር። የአፄ ምኒልክን ቅርስ ማስከበር በመጨረሻም ፊታውራሪ በጣም የሚታወቁት እጅግ የሚወዷቸውንና የሚያከብሯቸውን የአፄ ምኒልክን ኑዛዜና ቅርስ ለማስከበር ባደረጉት ያላሠለሰ ጥረት ነው። ምኒልክ ከደከሙ በኋላ እቴጌ ጣይቱ በፖለቲካ ጣልቃ እየገቡ ሲያስቸግሩ፤ ሀብተ ጊዮርጊስ የአልጋ ወራሹ የልጅ ኢያሱ ሞግዚት ሆነው ከተሰየሙት ከቢትወደድ ራስ ተሰማ ናደው ጋር በማበር በመጋቢት 1902 ዓ . ም . ያስወገዷቸውም ለዚህ ነው። ቀጥሎም በመስከረም 1909 ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን በማውረዱ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት ኢያሱ የምኒልክን ግዝት አፍርሰዋል በማለት ነው። በሚቀጥሉት ዓመታትም ከአልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ ጋር ፍጥጫ የገቡት ተስማምተው ንግሥተ ነገሥት ያደረጓቸውን የምኒልክን ልጅ የንግሥት ዘውዲቱን ሥልጣን ሲገዘግዙ ዝም ብዬ አላይም በማለት ነው። ከሁሉም በላይ ለምኒልክ የነበራቸው ታማኝነት የተገለፀው ንጉሠ ነገሥቱ በ 1906 ዓ . ም . ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ አገር እንዳይናወጥ ተብሎ ጉዳዩ ለሦስት ዓመት በምስጢር ሲያዝ፣ የቃና ዘገሊላን በዓል አስታከው ተዝካራቸውን በየዓመቱ በምስጢር ማውጣታቸው ነው። ይህን ተዝካር ማውጣታቸውን ሞታቸው ይፋ ከሆነም በኋላም ቀጥለውበታል። የጽሑፍ አቅራቢዎች አጫጭር መረጃ ዶ / ር አህመድ ሐሰን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል፤ የዶክትሬት ዲግሪውን ደግሞ ፈረንሣይ አገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቴ ደ ፕሮቫንስ ኤክስ ማርሴይ አግኝቷል። በማኅበራዊ፣ አካባባዊና ኤኮኖሚክ ታሪክ ላይ ምርምር የሚያደርግ ሲሆን፤ አያሌ መጣጥፎችና አንድ መጽሐፍ አሳትሟል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ አስተዳደራዊ ኃላፊነቶች አገልግሏል፡ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር፣ የለውጥ ማኔጅሜንት ቢሮ ዳይሬክተር እና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር። ዶ / ር አልማው ክፍሌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ከባችለር እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በሕግ የማስትሬት ዲግሪ አግኝቷል። በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ የምርምር ጽሑፎችን አሳትሟል። በሐረማያና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲዎች ታሪክና ሕግ ከማስተማሩም ባሻገር፤ በግል የሕግ አማካሪና ጠበቃ በመሆን የሙያ ድጋፍ ለሚሹና መክፈል ለማይችሉ ወገኖች ነፃ የሕግና የማማከር አገልግሎት አበርክቷል። ዶ / ር አሰፋ ባልቻ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪከ ትምህርት ክፍል ካገኘ በኋላ፤ አትላንታ ከሚገኘው የኤሞሪ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪውን አግኝቷል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆኖም አገልግሏል። ዶ / ር አውግቸው አማረ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎቹን በታሪክ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። የምርምር መስኩን በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያደረገ ሲሆን፤ በተለይ ትኩረት የሚያደርገው በሕዝቦችና ባህሎች ትስስርና መስተጋብር ላይ ነው። ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የዶክትሬት ዲግሪውን ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ላይ አያሌ መጻሕፍትና መጣጥፎችን ለኅትመት አብቅቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበርና የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል። ከዩኒቨርሲቲ ውጭ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖም አገልግሏል። ዶ / ር ደቻሳ አበበ በትምህርት መስክ የባችለር ዲግሪውን ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ የማስትሬት ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ እና የዶክትሬት ዲግሪውን ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኤዥያ ጥናት ማዕከል የሪሰርችና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ሲሆን፤ በርካታ መጣጥፎችን እና ሁለት መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል። ዶ / ር ደረጀ ሂነው የዶክትሬት ዲግሪውን በታሪክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ በማስተማር ላይ ይገኛል። በምዕራብ ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያደረገውን የምርምር ውጤቶች ከማሳተሙም በላይ፤ በ 2011 በኦሮሞና ጉሙዝ መካከል በተደረጉ የሰላም ጉባዔዎችም ተሳትፏል። ዶ / ር ዴሬሳ ዴቡ የዶክትሬት ዲግሪውን በታሪክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከማስተማርና ምርምር ባሻገር በጂማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ዶ / ር ገረመው እስከዚያ የዶክትሬት ዲግሪውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን፤ አሁንም እዚያው ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማስተማር ላይ ይገኛል። ዶ / ር ግርማ ነጋሽ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የታሪክ ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበር ሲሆን፤ በታሪክ መምህርነት አያሌ ዓመታትን አሳልፏል። የምርምር ትኩረቱን በኤኮኖሚክ፣ የሥራና የትምህርት ታሪክ ላይ ያደረገ ሲሆን፤ የጫት ንግድ በልጆች ትምህርት ላይ ስለሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ መጽሐፍ አሳትሟል። ዶ / ር ከፍያለው ተሰማ በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆን፤ የዶክትሬት ጥናቱን ያደረገው በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሕዝቦች መስተጋብር ላይ ነው። ዶ / ር ሺመልስ ቦንሳ ኒው ዮርክ በሚገኘው ስቶኒብሩክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆን፤ የምርምር ትኩረቱን ያደረገው በአፍሪካ ዘመናዊና ወቅታዊ ታሪክ ላይ ነው። የዶከትሬት ዲግሪውን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ( ሎስ አንጀለስ ) ያገኘ ሲሆን፤ ለዚሁ በአዲስ አበባ የሃያኛው መቶ ዓመት ታሪክ ላይ ያቀረበውን ድርሳን በቅርቡ ለኅትመት እንደሚያበቃ ይጠበቃል። ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ምሩቅና ባልደረባ ሲሆን፤ የዶክትሬት ዲግሪውን ያገኘው ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢሊኖይ አት ኧርባና ሻምፔይን ነው። ከዚያም ለዐሥራ አምስት ዓመታት ቨርጂኒያ በሚገኘው ኒውፖርት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ከሠራ በኋላ፤ በ 2008 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ይገኛል። ካሳተማቸው ሥራዎቹ መካከል Unionists and Separatists, the Vagaries of EthioEritrean Relations የተሰኘው መጽሐፉ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛል። ዶ / ር ተካልኝ ወልደ ማርያም ዶ / ር ቴዎድሮስ ዘውዱ የዶክትሬት ዲግሪውን ካናዳ ከሚገኘው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን፤ የምርምር ትኩረቱም በማንነት ፖለቲካ ላይ ነው። በዚህም ረገድ ውህድ ማንነት ያላቸው ግለሰቦችን ዕጣ ፈንታ በመመርመርና አጉልቶ በማውጣት ፈር ቀዳጅ ሚና ተጫውቷል። ከአካዳሚክ ሥራው በአሻገርም በካናዳ የሚገኙትን የአፍሪካውያን ማኅበረሰቦች በማንቃትና በማሰባሰብ አገልግሎት አበርክቷል። ዶ / ር ዘላለም ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስዮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ደግሞ የምርምር ፌሎው ነው። ሠፈራን፣ መፈናቀልንና ድንበር ዘለል ፍልሰትን ጨምሮ በሕዝቦች እንቅስቃሴዎች ላይ ሰፊ ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም መስክ 20 የምርምር ውጤቶችን በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ መጽሔቶች ላይ አሳትሟል።